Saturday, January 22, 2022
Home Blog

ሰበር ዜና – ዛሬ ረፋድ ላይ አዲግራት ከተማ በትግራይ ሰራዊት እጅ ወድቃለች

0

ባለፉት አራት ቀናት ዘመቻ አሉላ አባነጋ በሚል ፀረ ማጥቃት የጀመረው በህወሃት የሚመራው የትግራይ ሰራዊት በርካታ ከተሞችን መቆጣጠሩን ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል። ታማኝ ምንጮች ለኢትዮኖሚክስ እንደገለፁት ዛሬ ረፋድ ላይ የኢትዮጵያና የኤርትራ ጥምር መከላከያ ሰራዊት አዲግራት ከተማን ለቆ የወጣ ሲሆን ከተማዋ ብዙ እንቅስቃሴ እንደማይታይባትና የትግራይ ሰራዊት ወደ ከተማዋ እየገባ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል። በአሁኑ ሰዓት ሰራዊቱ ሓዱሽ ዓዲ ወደሚባል የወታደር ካምፕ የገባ ሲሆን አዲግራት ከተማ ላይ ያሉት አብዛኛዎቹ የፌደራል ፖሊስ አባላት የትግራይ ተወላጅ በመሆናቸው ያለምንም ግጭት የፀጥታ ሰራ መስራታቸውን እንደቀጠሉ ምንጫችን አክሎ ገልጿል።

ብዙ ውዝግብን የፈጠረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በትላንትናው እለት በሰላም የተካሄደ ቢሆንም ከትግራይ እየተሰማ ያለው ዜና ግን የምርጫውን ድባብ የሚያደፈርስ ሆኗል። ከመቀሌ አየር ማረፍያ በአምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ያለውን የአሽጎዳ ራዳር ጣብያ ሳይቀር ጥለው ወደ መቀሌ ከተማ የሸሹት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት በትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀሌ ዙርያ  እየተሰባሰቡ ሲሆን እስካሁን እዳጋ ሃሙስ፣ ሰንቃጣ፣ ሃውዜን፣ ውቅሮ፣ አጉላዕ፣ ሂዋነ፣ አዲ ቀይኽ፣ ቦራ፣ የጭላ፣ አቢይ አዲ፣ ግጀትና ሌሎች በማዕከላዊና ምስራቃዊ ዞን የሚገኙ በርካታ ከተሞች ባለፉት ጥቂት ቀናት ብቻ በትግራይ ሰራዊት እጅ ወድቀዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ልዑካን ቡድን ሰሞኑን በቦስንያ መንግስት ግብዣ ወደ ሳራየቮ ከተማ የተጓዘ ሲሆን ቀጥሎም በሌላኛዋ የቀድሞ ዩጎዝላቭያ አካል ሰርብያ መንግስት ግብዣ ወደ ቤልግሬድ ተጉዞ ነበር። እነዚህ የመከላከያ ልዑካን በጉዟቸው የተለያዩ የጦር መሳርያዎችን ማለትም ፀረ ድሮን መሳርያ፣ የመገናኛ መሳርያዎችን፣ ፀረ ሽብር ማፈኛ መሳርያዎችን፣ እንዲሁም የመንግስት ባለስልጣናት ከቦታ ወደ ቦታ እንዲጓጓዙ የሚረዱ እንደ ብረት ለበስ ተሽከርካሪ ያሉትን በመሸመት ላይ እንደሆኑ የተገኘው መረጃ ያሳያል። በተጨማሪም ከሳምንት በፊት ጥቁር ባህርን አቋርጣ ወደ ዩክሬኗ ኦዴሳ ወደብ አቅንታ የነበረችው ጅጅጋ የተሰኘች የኢትዮጵያ መርከብ በርካታ ስሪታቸው የቀድሞዋ ሶቭየት ሕብረት የሆኑ ከባድና ቀላል መሳርያዎችን ጭና ጅቡቲ መድረሷን ኢትዮኖሚክስ እጅ የገባ መረጃ ያመለክታል።

ጅጅጋ የተሰኘችው መርከብ መሳርያ ጭና ጅቡቲ ደርሳለች

“የትግራይን ሕዝብ እናጠፋዋለን ሲሉ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ቃል በቃል ነግረውኛል” የአውሮፓ ሕብረት ልዩ መልዕክተኛ

29

ባለፉት 6 ወራት ውስጥ ሁለት ጊዜ ወደ አዲስ አበባ ተጉዘው የነበሩት የፊንላንዱ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ፔካ ሃቪስቶ በትላንትናው እለት አስደንጋጭ የሆነ ንግግር በአውሮፓ ሕብረት ምክር ቤት አድርገዋል። ሚንስትሩ የአውሮፓ ሕብረት ልዩ መልዕክተኛ በመሆን መጀመርያ በየካቲት ወር ከዛም በሚያዝያ ወደ አዲስ አበባ በተጓዙበት ወቅት ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድን ጨምሮ ከተለያዩ የኢትዮጵያ መንግስት አመራሮች ጋር ተገናኝተው የነበረ ሲሆን በትግራይ ላይ እየተካሄደ ያለው ጦርነት እንዲቆምና የኤርትራ ወታደሮችም ከትግራይ እንዲወጡ እንዲሁም የረሃብ አደጋ ያጋረጠባቸው በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ንፁሃን እርዳታ እንዲያልፍላቸው ያደረጉት ጫና ሳይሳካ ቀርቶ ወደ አውሮፓ ተመልሰው ነበር።

ታድያ በትላንትናው እለት በአውሮፓ ሕብረት ጠቅላይ ምክር ቤት “በትግራይ ላይ እየተፈፀመ ላለው የጦር ወንጀል ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድና ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ወደ ፍርድ የሚቀርቡ የመስልዎታል ወይ?” የሚል ጥያቄ ከአየርላንዱ ተወካይ ቀርቦላቸው ነበር። ሚንስትሩ ሲመልሱም “በአሁን ሰዓት በርካታ ገለልተኛ ተቋማት እየተፈፀመ ስላለው ግፍና ወንጀል ዝርዝር እያወጡ ቢሆንም የተባበሩት መንግስታት እያካሄደ ያለውን ምርመራ እስኪያጠናቅቅ ብንጠብቅ ይሻላል” ካሉ በኋላ “ባለፈው የካቲት የኢትዮጵያ ባለስልጣናትን ባገኘኋቸው ጊዜ የትግራይን ሕዝብ እንደሚያጠፉት፣ እንደሚያወድሙትና 100 ዓመታት ወደ ኋላ እንደሚመልሱት ቃል በቃል ነግረውኛል፣ እንደኔ ሃሳብ ከሆነ ይህ በጦር ወንጀል የሚያስጠይቅ ነው” ሲሉ አክለዋል።

ፔካ ሃቪስቶ በመጀመርያው የየካቲት ጉዟቸው የኢትዮጵያ ባለስልጣናትን ቢያንስ እንኳን በትግራይ ለተራቡ ንፁሃን እርዳታ እንዲያሳልፉ ለማሳመን ሳይችሉ መቅረታቸውን ተከትሎ የአውሮፓ ሕብረት የኢትዮጵያ መንግስት ላይ ምን አይነት እርምጃ ሊወስድ እንደሚችል በግልፅ ለጠቅላይ ሚንስትሩ ያስጠነቅቁ ዘንድ ለሁለተኛ ጊዜ በሚያዝያ ወር ወደ አዲስ አበባ ተልከው የነበረ ቢሆንም ዳግም ሳይሳካላቸው መመለሳቸው በአውሮፓውያኑ ዘንድ ቁጣን ጭሯል።

የኢትዮጵያ መንግስት ሃሰተኛ መረጃ ሲያሰራጭባቸው የነበሩ ከመቶ በላይ ገፆችን ዘግቻለው ሲል ፌስቡክ አስታወቀ

2

የማህበራዊ ድህረገፁ ፌስቡክ በትላንትናው እለት ባወጣው ዝርዝር ሪፖርት ከመቶ በላይ የሆኑ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ንክኪ ያላቸው ገፆችን እንደዘጋ አስታወቀ። ፌስቡክ ባደረገው ውስጣዊ ምርመራ እነዚህ ገፆች በብሔራዊ ደህንነት ተቋም ስር የሚተዳደረው የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) ሰራተኞች የከፈቷቸው እንደሆኑ ደርሼበታለው ያለ ሲሆን ገፆቹ እርስ በርስ በመቀናጀት ሃሰተኛ መረጃን ለህዝብ ሲያቀርቡ የቆዩ ናቸው ሲሉ የፌስቡክ የደህንነት ሃላፊ ናታንዬል ግሊቸር ገልፀዋል።

ከተዘጉት ውስጥ 65 በግለሰብ ስም የተከፈቱ አካውንቶች፣ 52 በዜናና የተለያዩ ስያሜዎች የተከፈቱ ገፆች፣ 27 የቡድን/ማህበር ገፆችና 32 የኢንስታግራም አካውንቶች ይገኙበታል። እነዚህ ገፆች ባጠቃላይ ከአንድ ሚልዮን በላይ ተከታዮች የነበሯቸው ሲሆን ላለፈው አንድ አመት አካባቢ በተደራጀ መልኩና በተከታታይ ህዝብን የሚያደናግሩ የፖለቲካ ፅሁፎችን ሲለቁ እንደቆዩ ፌስቡክ አክሎ ገልጿል።

የፌስቡክ ሃላፊው ናታንዬል ለአብነት ከጠቀሷቸው ገፆች ውስጥ ኢትዮ ፋክትስ፣ ኢትዮ ኒውስ፣ አዲስ ሚድያ ኔትወርክና ዘ አክሱማዊት ኢንፎ ትዩብ የተባሉት የሚገኙበት ሲሆን የተለያዩ ጠቅላይ ሚንስትር አብይንና ብልፅግና ፓርቲን ከሚያሞግሱ ፅሁፎች ጀምሮ ስለ ትግራይ ጦርነት የተሳሳቱ መረጃዎችን የሚያጋሩና ብሎም ስለ አሜሪካ ማዕቀብ የተዛቡ መረጃዎችን የሚያሰራጩ ፅሁፎችን ሲለጥፉ ቆይተዋል።

ናታንዬል ግሊቸር አክለውም የኢንሳ ሰራተኞች ከገፆቹ ጀርባ ያለው ማንነታቸውን ለመደበቅ ሙከራ ያደርጉ እንደነበርና ነገር ግን በፌስቡክ ምርመራ ማንነታቸው እንደተደረሰበት ገልፀዋል።

“ዳቦ ከጠፋ ለምን ኬክ አይበሉም?” አዲስ አበቤነትና የኢትዮጵያውያን ሰቆቃ

10

እንደ ኢትዮጵያውያን አቆጣጠር በ1965 ዓ.ም በወሎ ስለተከሰተው አስከፊ ረሃብ መረጃ የደረሰው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምናልባት አዲስ አበባ ላይ በቂ ግንዛቤ ላይኖር ይችላል በሚል ከኒውዮርክ አንድ ሃላፊ ይልካል። መልዕክተኛውም ወደ አዲስ አበባ የተጓዘው በወቅቱ የኢትዮጵያ ንጉስ ለነበሩት ቀዳማዊ ንጉስ ሃይለስላሴ ስለ ረሃቡ አስከፊነትና እያስከተለ ስላለው እልቂት በዝርዝር ለማስረዳት ነበር። ይሁን እንጂ መልዕክተኛው በቤተ መንግስት ባደረገው ቆይታ ንጉሱ ወሎ ውስጥ ስለተፈጠረው ረሃብ ከነዝርዝሩ ጠንቅቀው እንደሚያውቁ ለመረዳት እንደቻለ ተናግሮ ነበር። እንደ የተባበሩት መንግስታት መልክተኛው ግንዛቤ ረሃብ ለገበሬዎች አዲስ አይደለም የሚል አመለካከት ንጉሱ እንደነበራቸውና እየተራበ ያለውም የሸዋ አማራ እስካልሆነ ድረስ ብዙ ሊያስጨንቅ አይገባም አይነት አቋም እንዳየባቸው ፅፎ አስቀምጧል። ይባስ ብሎም ሚልዮኖች በተራቡበት በዚህ ወቅት የንጉሱ የ80ኛ ዓመት የልደት በዓል በ35 ሚልዮን ዶላር (በዛሬ ዋጋ 215 ሚልዮን ዶላር) ወጪ አዲስ አበባ ላይ እየተከበረ እንደነበር የታሪክ መፃህፍት ያወሳሉ።

መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ የአገር መሪዎችና ደጋፊዎቻቸው በተራበ ሕዝብ ላይ ፊታቸውን በማዞር ለራሳቸው ቅንጦት ቅድምያ መስጠታቸው በአፄ ሃይለስላሴ የቀረም አይደለም። ከ12 ዓመታት በኋላ በ1977 ዓ.ም በኢትዮጵያ ታሪክ አስከፊ የተባለውና እስከ አንድ ሚልዮን ሕዝብ እንዳለቀበት በሚነገርለት የሰሜን ወሎ (የዛሬዎቹ አፋርና ትግራይ) ረሃብ ወቅት የመንግስቱ ሃይለማርያም መንግስት የኢሰፓን 10ኛ ዓመት በዓል ለማክበር 100 ሚልዮን ዶላር (በዛሬ ዋጋ 615 ሚልዮን ዶላር) እንዳወጣ የአሜሪካው ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ በ1977 የህዳር 12 እትሙ ዘግቦት ነበር።

ታድያ ዛሬም በ21ኛው ክፍለ ዘመን አገሪቱ በሁሉም አቅጣጫ ቀውስ ውስጥ በገባችበትና ጊዜ የማይሰጠው የረሃብ አደጋ በሚልዮኖች ላይ በተደቀነበት ወቅት እንደተለመደው አዲስ አበባ ላይ ያለው ድባብ “ዳቦ ከጠፋ ለምን ኬክ አይበሉም” ይመስላል። ባለፉት 12 ወራት ብቻ ሴቶችና ህፃናትን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ የአማራ ገበሬዎች በቤንሻንጉልና በወለጋ ተጨፍጭፈው ሌሎች ሺዎች ደግሞ ቤት ንብረታቸውን ጥለው ተሰደዋል። በተመሳሳይ መልኩ ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ የጉሙዝ ተወላጆች በአማራ ታጣቂዎች የተገደሉ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩትም ወደ ሱዳን ተሰደው በመጠለያ ካምፖች ውስጥ ይገኛሉ። በሌላ በኩል በምስራቅ ኢትዮጵያ በአፋርና በሱማሌ ክልሎች መካከል ከመሬት ይገባኛል ጋር ተያይዞ በተደጋጋሚ በሚከሰቱ ግጭቶች በመቶዎች እንደተገደሉ መረጃዎች ያመለክታሉ። በተጨማሪም በቅርቡ በደቡብ ክልል በተለያዩ ወረዳዎችና  እንዲሁም በአማራ ክልል አጣዬና አካባቢዋ ላይ ብሎም በመላው ኦሮምያ በኦነግና በመንግስት ታጥቂዎች መካከል እየተከሰቱ ባሉ ግጭቶች የበርካቶች ህይወት ከማለፉም ባለፈ የተሰደዱና ንብረት የወደመባቸው ንፁሃን ቁጥር ጥቂት የሚባል አይደለም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢትዮጵያ እያስተናገደቻቸው ካሉ የእርስ በርስ ግጭቶች የባሰውና በከፋ መልኩ የዓለምን ትኩረት የሳበው የውጭ ሃይሎችም ጭምር በተዋናይነት እየተሳተፉ የሚገኙበት በትግራይ ክልል ላይ ላለፉት ሰባት ወራት እየተካሄደ ያለው ጦርነት ነው።  ይህ ጦርነት ከተለኮሰበት ጥቅምት ወር ጀምሮ ነፁሃንንና ከሁሉም ወገን ያሉ ተዋጊ ሃይሎችን ጨምሮ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር የሰው ልጅ ህይወት እንደ ቅጠል ረግፎበታል።

በአጠቃላይም እነዚህ ሁሉ ቀውሶች ተደምረው ኢትዮጵያ ከአገር ሳይወጡ ውስጥ ለውስጥ የተፈናቀሉና የተሰደዱ ቁጥራቸው እስከ 5 ሚልዮን የሚደርስ ዜጎችን በመያዝ ከዓለም በአንደኛ ቦታ ላይ ትገኛለች።፡

ታድያ ይህ ሁሉ እሳት ከጫፍ እስከ ጫፍ በተቀጣጠለበት ሰዓት የአገሪቱ ዋና ከተማ የሆነችው አዲስ አበባ ማለቅያ በሌላቸው ክብረ በአላት፣ የቅንጦት ፕሮጀክቶች ምርቃትና ስለ ኢትዮጵያ ገናናነት አውርተው በማይጠግቡ ልሂቃን ተጨናንቃ ትታያለች። ለአብነት ያህል ሰሞኑን የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነሯ ወ/ሮ ሌሊሴ ነሜ በትዊተር ገፃቸው ስለ ዮጋ ስፖርት ጥቅምና ከአገር ሰላም ጋር ስለመያያዙ የሚገልፅ ፅሁፍ በመናፈሻ ላይ ከተነሱት ፎቶ ጋር አያይዘው መለጠፋቸውን ተከትሎ በርካታ የውጭ ጋዜጠኞች  “አዲስ አበባ ምን አይነት ህልም ላይ ነች” የሚል ትዝብት አዘል አስተያየት ሲሰጡ ታይተው ነበር።

መንገዶች ሁሉ ወደ አዲስ አበባ ?

በጥንት ዘመን አብዛኛውን የአውሮፓና የመካከለኛው ምስራቅን ግዛቶች ያጠቃልል በነበረው የሮማውያን ስልጣኔ ይገነቡ የነበሩ መንገዶች ሁሉ አቅጣጫቸው የነገስታቱ መቀመጫ ወደነበረችው ሮም እንዲያመራ ተደርጎ ነበር። ከዚህም ነው “መንገዶች ሁሉ ወደ ሮም ያመራሉ” የሚለው ታዋቂ የምዕራባውያን ፈሊጥ የመነጨው። ሮማውያን ተቆጣጥረውት በነበረው ከስፔን እስከ ኢራቅ ከሚደርስ ግዛት የተለያዩ የእርሻ ውጤቶችን፣ ማዕድናትን፣ ጥሬ ገንዘብንና የጉልበት ሰራተኛ ባርያዎችን እንደፈለጉ ወደ ሮም እንዲያስመጡና እንዲያስገብሩ እንዲሁም ወታደሮቻቸው እንዳሻቸው በግዛቱ ተዘዋውረው ተልዕኮዎችን እንዲያስፈፅሙ በማለት ነበር መንገዶቹን ወደ ሮም አቅጣጫ አድርገው ይቀይሷቸው የነበረው።

በተመሳሳይ መልኩ ለዘመናት አዲስ አበባ ከተመሠረተች ጊዜ ጀምሮ የማዕከላዊ መንግስትን ስልጣን የያዙ አካላትና የከተማዋ ልሂቃን በሁሉም አቅጣጫ ካለው የኢትዮጵያ ክፍል ግብር ለመሰብሰብ ያመቻቸው ዘንድ የተለያዩ መንገዶችን ዘርግተዋል። እነዚህ መንገዶች በአስፋልትና በኮሮኮንች ብቻ የሚወሰኑ ሳይሆኑ መንግስታዊ መዋቅርን፣ የሃይማኖትና የፋይናንስ ተቋማትን እንዲሁም የትምህርት የስነጥበብና የታሪክ ቀረፃዎችን መሠረት ያደረጉ ናቸው። ታድያ በአንድነትና በኢትዮጵያዊነት ሽፋን “መንገዶች ሁሉ ወደ አዲስ አበባ” ያመራሉ የሚለው ሃብት ማካበትን ዋነኛ አላማው ያደረገ አስተሳሰብ ኢትዮጵያ ላለፉት መቶ ዓመታት በአስከፊ ድህነትና የእርስ በርስ ጦርነት ላይ ተጠምዳ ለመኖሯ ዋነኛ ምክንያት ነው ብሎ ኢትዮኖሚክስ ያምናል።

የአዲስ አበባ ተፈጥሮአዊ አመሠራረቷ በዓለማችን ኪራይ ሰብሳቢ ከተሞች ከሚባሉት ተርታ እንድትመደብ የሚያደርጋት ነው። ልክ የአንጎላዋ ዋና ከተማ ሉዋንዳ የአገሪቱን የነዳጅ ሃብትና ማዕድናት በመቸብቸብ የሚኖሩ ነጋዴዎችና ባለስልጣኖች መናኸርያ እንደሆነችው እንዲሁም የሩስያን የተፈጥሮ ሃብት የበዘበዙ ቱጃሮች ሃብታቸውን እንዳከማቹባት ሞስኮ ከተማ አዲስ አበባም ህልውናዋ በኪራይ ሰብሳቢዎች መናኸርያነቷ ላይ የተመሰረተ ነው። አገሪቱ ያሏት ወሳኝ ተቋማት በሙሉ ከብሔራዊ ባንክ እስከ ፋይናንስ ሚንስቴር እንዲሁም ሁሉም የመንግስትና የግል ባንኮች ዋና መስርያ ቤቶቻቸው በከተማዋ ላይ መሆኑ ከባሕር ዳር እስከ ጋምቤላና ሐረር ያለው ኢትዮጵያዊ የውጭ ተመልካች ሆኖ እንዲኖር አድርጎታል።፡ የአገሪቱ ፖሊሲም ሆነ ወሳኝ የእድገት መሳርያዎች የሰፊውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቅም ከግምት ከማስገባት ይልቅ አዲስ አበቤነትን ያማከሉና መንግስታዊ መዋቅርን እንደ ሽፋን በመጠቀም ሃብትን ወደ ከተማዋ ለማጋዝ የሚያገለግሉ ሆነው ከመቶ አመት በላይ አገልግለዋል።

ለምሳሌ ከተለያዩ ምንጮች የሚገኘው የአገሪቱ የውጭ ምንዛሬ በአብዛኛው የሚከማቸው በአዲስ አበባ ሲሆን ባንኮችም ቅድምያ ሰጥተው የሚያከፋፍሉት ለከተማዋ ነዋሪዎች ነው። ይህም የሆነው ከተለያዩ ክልሎች ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች በአብዛኛው ትርፍ የሚያስገኙት አዲስ አበባ ላሉ የመሃል ነጋዴዎችና ደላላዎች እንጂ በክልሎች ላሉ የምርቶቹ ባለቤቶች ስላልሆነ ነው።  ታድያ ትግራይ እንደ አንድ ክልል ያመረተችውን ሰሊጥ በቀጥታ ወደ ውጭ ልካ የሚጠበቅባትን ግብር በአግባቡ ለፌደራል መንግስት ብትከፍል ወይም የሲዳማ ቡና አምራቾች አዲስ አበባ ያሉ ነጋዴዎችን በመዝለል በቀጥታ ምርታቸውን ወደ አውሮፓ መላክ ቢጀምሩ አዲስ አበባ ላይ አለአግባብ ይከማች የነበረው የውጭ ምንዛሬ ወደ ክልሎች እንዲከፋፈል ሊያስገድድ ይችላል። ይህ ታድያ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሚገኘው ገቢ በስተቀር ምንም አይነት ምርት ወደ ውጭ የማትልከው አዲስ አበባ የውጭ ምንዛሬ ፍሰት እንዲቀንስባትና ወደ ከተማዋ የሚገቡት እንደ የቤት መኪና፣ አይፎንና ሌሎች የቅንጦት ቁሳቁሶች አቅርቦት እንዲቀንስ ሊያስገድዳት ይችላል።

በእርግጥ በማንኛውም ጤነኛ ተፈጥሮ ባላት አገር እንደዚህ አይነት የሃብት ክፍፍል ፍትሃዊና ተገቢ ተብሎ ሊወሰድ የሚገባው ነበር። ነገር ግን የአዲስ አበባ ህልውና የኢትዮጵያን ሃብት ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር ላይ የተመሠረተ በመሆኑ የዚህ አይነት ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል በከተማዋ ማህበረሰብ ዘንድ ተቀባይነት እንዳይኖረው አድርጎታል። ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ የሰው ሃይል ያላት አዲስ አበባም ጥቅሟን ለማስከበር መላውን የአገሪቱን ግዛት በጉልበት መቆጣጠር የማይቻላት በመሆኑ የተለያዩ ሃይማኖታዊ፣ ታሪካዊ፣ ፖለቲካዊና ሌሎች ትርክቶችን በመጠቀም እንዲሁም የኢትዮጵያን ዋነኛ ተቋማት አግታ በመያዝ መንገዶች ሁሉ ወደ ከተማዋ እንዲያመሩና በሁሉም አቅጣጫ ያለው ሃብት በአዲስ አበባ ቁጥጥር ስር እንዲሆን ላለፉት ከመቶ በላይ አመታት የተሰራበት ነው።

አዲስ አበባ የችግሮች ሁሉ ምንጭ?

በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ በዛሬዋ ኢትዮጽያ ውስጥ የተካተቱትን አብዛኛዎቹን ግዛቶች በጦር መሳርያ ሃይል የወረሩት ዳግማዊ አፄ ምኒሊክ ቢሆኑም እነዚህ ግዛቶች ተጠቃለው የኢትዮጵያ ካርታ አለም አቀፋዊ እውቅና እንዲያገኝና በግዛቶቹ የሚኖሩ ሕዝቦች የአዲስ አበባን አገዛዝ እንዲቀበሉ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከቱት ቀዳማዊ አፄ ሃይለስላሴ ነበሩ።

በጀነራል ዊንጌት በሚመራው ግዙፉ የእንግሊዝ ጦርና መነሻቸውን በአብዛኛው ከጎጃም ክፍለ ሀገር ባደረጉ አርበኞች ከፍተኛ ትግል ጣልያን ኢትዮጵያን ለቆ ለመውጣት ሲገደድ ወደ አዲስ አበባ የተመለሱት አፄ ሃይለስላሴ የራሳቸውን ጳጳስ በመሾም የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያንን ዋና የግብር መሰብሰብያና ሰፊውን ሕዝብ የመቆጣጠርያ ዘዴ አድርገው ያዋቀሯት ሲሆን ከቤተክርስትያኗ በተጨማሪም የአገሪቱ የትምህርት ስርአት፣ የታሪክ ምዝገባ፣ የስነ ጥበብ አቀራረብና የመንግስት መዋቅር አዲስ አበባን ብቸኛዋ አስገባሪና የሃብት ማዕከል ትሆን ዘንድ እንዲያስችሉ በጥንቃቄ የተደራጁ ሆነው ኖረዋል።

ታድያ ዛሬ ለአዲስ አበባ ማዕከላዊነት ዋነኛ ስጋትና ጠንቅ ነች ተብላ በተፈረጀችው ትግራይ ክልል ላይ ጦርነት ሲታወጅ ከሃይማኖት ተቋማት ጀምሮ እስከ አርቲስቶች ስፖርተኞችና ባለሃብቶች ብሎም ምሁራን ድረስ የተቀናጀ ጦርነቱን የመደገፍ እንቅስቃሴና በትግራይ ሕዝብ ላይ የተጋረጠውን ሰው ሰራሽ የረሃብ አደጋ የማስተባበል ሁኔታ አዲስ አበባ ላይ መታየቱ የከተማዋን ተፈጥሮአዊ ፀባይ የሚያንፀባርቅና እነዚህ አካላት የቆሙበትን በጋራ በጥቅም ላይ የተመሠረተ ምሰሶ የሚያጋልጥ እንጂ ብዙም የሚያስገርም ሊሆን አይገባም።

ያለፉትን መቶ አመታት ስንመለከትም ከዛሬው ብዙ የተለየ ታሪክ አናገኝም። በኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰቱ ጦርነቶች ሙሉ በሙሉ ማለት ይቻላል መነሻቸው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የአዲስ አበባን ጥቅም ከማስከበርና ተቀሪውን የኢትዮጵያ ሕዝብ እያስገበሩ ከመቀጠል ጋር የተያያዘ ነበር ። ይባስ ብሎም በነዚህ መቶ አመታት ውስጥ በተለያየ ጊዜ  በአማራ፣ አፋር፣ ትግራይ፣ ሱማሌና ሌሎችም ክልሎች የሚልዮኖችን ህይወት የቀጠፈው ረሃብ በበቂ የውጭና የአገር ውስጥ እርዳታ ሊቃለል እየቻለ አንዴ የአገር ገፅታ እንዳይበላሽ በሚል ሌላ ጊዜ ደግሞ ሕዝብን እንደ ማንበርከክያ ዘዴ መታየቱ አዲስ አበባ ላይ በተደጋጋሚ የሚቀነቀነው አንድነትና የዜግነት ፖለቲካ የኢትዮጵያ ሃብትን መቆጣጠር አላማው ያደረገና ይህንን ለማሳካት ሲባል የሚጠፋውም የሚልየኖች ህይወት በአዲስ አበቤነት ዘንድ ተቀባይነት ያለው እንደሆነ የሚያሳይ ነው።

ኢትዮጵያ በቂ የሆነ የእርሻ መሬት፣ የተፈጥሮ ሃብትና የሰው ሃይል እያላትም ቢሆን በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ንፁሃን ህይወታቸውን በረሃብና በጦርነት እንዲያጡ ተገደዋል። በጤፍ ምርቱ ከሚታወቀው የጎጃም ገበሬ ጀምሮ በዓለም አለ የተባለውን ቡና እስከሚያመርተው የወለጋ ህዝብና የጥንታዊ ታሪክ እንዲሁም ቅርስ ባለቤት እስከሆኑት የጎንደርና የትግራይ ሕዝቦች ዛሬም በድህነት፣ በመልካም አስተዳደር እጦትና በጦርነት የሚሰቃዩ ናቸው። በአንፃሩ ምንም አይነት የግብርና ምርትም ሆነ የኢንዱስትሪ ዘርፍ አልያም የቴክኖሎጂ ፈጠራ የሌላት አዲስ አበባ ዛሬም ነዋሪዎቿ ጫማቸውን በሊስትሮ የሚያስጠርጉባት፣ በቤት ሰራተኛ የሚገለገሉባት፣ እጅግ የቅንጦት የሚባሉ መኪኖችና መኖርያ ቤቶች የሚታዩባት ከተማ እንደሆነች ቀጥላለች።

ዓ.ም (ኢትዮጵያ) በረሃብ የጠፋ የሰው ህይወት ብዛት ረሃብ ያጠቃው ማህበረሰብ
1950 100,000 ትግራይ
1958 50,000 አማራ
1965 200,000 አማራ፣ ትግራይ፣ አፋር፣ ሱማሌ
1977 1,000,000 ትግራይ፣ አፋር፣ አማራ
1992 20,000 ትግራይ፣ አማራ፣ ሱማሌ
1995 ጥቂት ሺዎች
2008 0 – 1,000

ምንጭ ፣ የአለም የሰላም ተቋም

አዲስ አበቤነት ታሪካዊ መሠረቱ የሸዋ አማራ ቢሆንም ዛሬ ግን ከበርካታ ፈላሻዎች ጋር በመዋሃድ አንድ ዘርም ሆነ አንድ ሃይማኖት የማይገልፀው የኪራይ ሰብሳቢዎችና የወፋፍራም ባለሃብቶች ስርአት ሆኗል። አንድነትን በተደጋጋሚ የሚሰብከው ይህ ስርዐት ብሔርተኛ ፖለቲከኞች እንደሚሉት ለአማራ ሕዝብ ለይቶ የሚቆረቆርና የአማራን ሕዝብ ብቸኛ የኢትዮጵያ ባለቤት ለማድረግ የሚጥር ሳይሆን በአማራ ሕዝብ ባሕል፣ ሃይማኖት፣ ደም፣ ላብና እንባ ተንጠላጥሎ ጥቅሙን ሲያስጠብቅ ከመኖር ባሻገር ለድሃው የአማራ ገበሬ ብዙም ሲጨነቅ የሚታይ አይደለም።  ለዚህም አንዱና ዋነኛው ማስረጃ በአማራ ክልል በሚገኘው ሰፊ ሕዝብ ላይ ያለው ሲቸግረኝ ድረስልኝ ስጠግብ አይንህን አልየው የሚለው የአዲስ አበቤነት አስተሳሰብ ነው። ከ7 ወራት በፊት በትግራይ ላይ በታወጀው ጦርነት የአማራ ገበሬዎችንና ሚልሻዎችን መስዋእትነት የፈለገው የማዕከላዊ መንግስትም ሆነ የአዲስ አበባ ልሂቅ ከሚድያ ቅስቀሳ ጀምሮ የእርድ በሬ እስከመላክና ደም እስከመለገስ የሚደርሱ ማበረታቻዎችን ሲያጎርፍ ታይቶ የነበረ ቢሆንም ዛሬ ስለ ሞቱት የአማራ ገበሬዎችም ሆነ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተውጣጥተው ትግራይ ላይ ስለቀሩት የመከላከያ ሰራዊት አባላት መስማትም ሆነ ማውራት እንደማይፈልግ በተደጋጋሚ ግልፅ እያደርገ ይገኛል። የመንግስትም ሆነ የግል ሚድያዎች ትግራይ ላይ ዘምተው ህይወታቸውን ስላጡት ወጣቶች እንዳታነሱ የተባሉ ይመስል በከንቱ ህይወቱን ስላጣው ገበሬ ከመነጋገር ይልቅ ስለ ኢትዮጵያ ገናናነት፣ መሬት ላይ ስለማይታየው አንድነትና ፣ ምናባዊ ሃያልነቷ በመስበክ ላይ ተጠምደው ይታያሉ።

ከዛም አልፎ ትግራይ ላይ እየተባባሰ የመጣውን ረሃብ ተከትሎ የአሜሪካና የአውሮፓ መንግስት ጦርነት አቁሙ በሚል በባለስልጣናት ላይ የቪዛ ማዕቀብ በመጣላቸው እነዚሁ የአዲስ አበባ ልሂቃን “እርዳታቸው ይቅርብን”፣ “ሉአላዊነታችንን አናስደፍርም”፣ “ለራሳችን አናንስም” የሚሉ ንግግሮችን በየእለቱ በመስበክ ላይ ይገኛሉ። እነዚህ ንግግሮችም በየገጠሩ ካለ ውጭ እርዳታ መኖር የማይችሉትን በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ተረጂዎች አስቆጥተዋል።

ድጋፍ ለጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ

በኢትዮጵያ ስልጣን ተቆጣጥሮ ያለው የብልፅግና መንግስት አዲስ አበባ ላይ ሊገነባ ለሚጥረው “ለኛ ሲዘንብ ለናንተ ያካፋል” የሚል በአሜሪካን አገር “ትሪክል ዳውን ኢኮኖሚክስ” በመባል የሚታወቅ የኢኮኖሚ መርህ በአዲስ አበባ ማሕበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ማግኘቱ ከከተማዋ ታሪካዊ ማንነት ጋር የሚሄድ ነው። የትሪክል ዳውን ኢኮኖሚክስ መርህ መሠረቱን አሜሪካ ባደረገውና ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ በሚከተሉት አክራሪ የብልፅግና ወንጌል ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ የሚቀነቀን ሲሆን መንግስታዊ መዋቅሮችንና ፖሊሲዎችን ከመጠቀምም ወደ ኋላ ሳይሉ ሃብታሞች ያሻቸውን ያክል ሃብት እንዲያካብቱ የሚያበረታታ ነው። ለዚህም ነው ጠቅላይ ሚንስትሩ ስልጣን ከያዙ ጀምሮ አዲስ አበባን በማሳመር፣ እጅግ ከፍተኛ ገንዘብ የሚወጣባቸው የእራት ግብዣዎችን በማዘጋጀትና ሙሉ በሙሉ ባይሳካላቸውም እንደ ቴሌ፣ አየር መንገድ፣ ባንኮችና የመሳሰሉትን ለውጭ ባለሃብቶች ለመሸጥ ላይ ታች ሲሉ የቆዩት። በኦርቶዶክስነት ሲመሰል የኖረው አዲስ አበባዊነትም በድንገት “መሬት ላይ የሌለ ነገርን እንዳለ አድርገህ አስመስልና የተመኘኸው እውን ይሆናል” በሚል ስብከት በሚታወቀው የፕሮስፔሪቲ ወይም የብልፅግና ወንጌል እንደ አዲስ መቀባት ጀምሯል ። ይህ ታድያ የሚያሳየው አዲስ አበባዊነት ሃይማኖትን፣ ታሪክንና አጠቃላይ ማንነትን እንደ ወቅታዊው ጊዜና ሁኔታ አመችነት እያገለባበጠ ጥቅምን ለማስከበር እንደሚጠቀምበት ነው።

ዛሬ አዲስ አበባ በጦርነትና በቀውስ የተከበበች ደሴት ሆና እየኖረች ነው። አዲስ አበባዊነትና የብልፅግና ወንጌልም  አንድ የሚያደርጋቸው ሃብትን ያማግበስበስ የጋራ አመለካከት በማግኘታቸው በእከከኝ ልከክህ እየተደጋገፉ ህልውናቸውን ለማስከበር በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ጦርነት አውጀዋል። ይባስ ብሎም ጠቅላይ ሚንስትሩ “ሚልዮኖች ያልቃሉ ኢትዮጵያ ግን ትቀጥላለች” የሚል ንግግር በአደባባይ ሲናገሩ ይሰማሉ አዲስ አበቤነትም በጭብጨባ ድጋፉን ይገልፃል። ለአማራ ሕዝብ ተቆርቋሪ ይሆናሉ ተብለው የተፈሩት ግለሰቦች በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል፣ ለኦሮሞ ህዝብ ድምፅ ይሆናሉ ተብለው የተጠረጠሩትም እስር ቤት ገብተዋል አልያም ተገድለዋል። እንዲሁም የራሱ ፖለቲካዊ፣ ታሪካዊና ባህላዊ እሴቶች ባለቤት በመሆኑ ለአዲስ አበባ አልገዛም በሚል ለዘመናት በሚታወቀው የትግራይ ሕዝብ ላይ ግልፅ የሆነ የዘር ማጥፋት ዘመቻ አውጀዋል።

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

ቢሮ እንኳን ሳይኖረው የ3.6 ቢልዮን ዶላር ፕሮጀክት የወሰደው የአሜሪካ ኩባንያና የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ትብብር

7

ባሳለፍነው ታህሳስ ተቀማጭነቱን በኒውዮርክ ከተማ ባደረገ አንድ ክዋርትዝ የተሰኘ የኢንተርኔት ጋዜጣ ላይ የታተመው ፅሁፍ የኢትዮጵያን መንግስት አንገት ያስደፋና በአንዳንድ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ቁጣን ያጫረ ነበር። ይሁን እንጂ የዚህ ፅሁፍ ወደ አማርኛ አለመተርጎም ከጉዳዩ ክብደት አንፃር በአገር ውስጥ የሚገባውን ያህል ትኩረት ሳያገኝ እንዲቀርና ተድበስብሶ እንዲያልፍ አድርጎታል።

ጉዳዩ እንዲህ ነው። በሱማሌ ክልል ከምድር በታች የነጭ ጋዝ ሃብት ስለመኖሩ ባለሙያዎች ማረጋገጣቸውን ተከትሎ በአካባቢው የማጣርያ ጣብያን ለመገንባት አንድ ግሪንኮም የተባለና በአሜሪካን አገር ቨርጂንያ ክልል ውስጥ የንግድ ፈቃድ ያወጣ ኩባንያ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ይዋዋላል። ይህ አቶ ነብዩ ጌታቸው በተባለ አሜሪካዊ ዜጋ የሚመራው ኩባንያ እንደ ኢትዮጵያውያን አቆጣጠር በ2012 ዓ.ም ሚያዝያ 20 ቀን ነበር ማጣርያውን ለመገንባት የ3.6 ቢልዮን ዶላር ውል ከነዳጅና ማዕድን ሚንስቴር ጋር የተፈራረመው።

ታድያ ለዚህ ማጣርያ ጣብያ ግንባታ የተመደበው 3.6 ቢልዮን ዶላር ከአስር አመት በፊት የህዳሴ ግድብ መሠረት ሲጣል ተመድቦ ከነበረው 4 ቢልዮን ዶላር ጋር መቀራረቡ የፕሮጀግቱን ግዝፈት የሚያሳይ ነበር። ይህ በእንዲህ እንዳለ  በኳርትዝ ጋዜጣ የታተመው ፅሁፍ ይህንን ያህል ግዙፍ ፕሮጀክት እንዴት ለአለም አቅፍ አጭበርባሪዎች እንደተሰጠና የኢትዮጵያ ባለስልጣናት የተጫወቱትን አጠራጣሪ የሆነ ሚና ለአለም ለማጋለጥ በቅቶ ነበር።

ጉዳዩን ማን አጋለጠው?

አንድ ስለ ኢትዮጵያ የነዳጅና ጋዝ ዘርፍ በቂ እውቀት ያለው የመንግስት ሰራተኛ በግሪንኮምና በኢትዮጵያ መንግስት የተገባው ይህ ውል አላማረውምና ቀስ ብሎ ለኳርትዝ ጋዜጠኞች ስለተደረገው የተምታታ ስምምነት የሚያውቀውን ሹክ ይላቸዋል፡፡ ከኳርትዝ ጋዜጠኞች አንዱ የሆነው ትውልደ ኢትዮጵያዊ ዘካርያስ ዘላለምም ጉዳዩን መከታተልና ማጣራትን ስራዬ ብሎ ይያያዘዋል። ጋዜጠኛው ዘካርያስ ምርመራውን አጠናቆ ሲያበቃም ያገኘው መረጃ ከተጠበቀው በላይ ከብዶና አሳፋሪ ሆኖ አግኝቶታል። አጠያያቂ በሆነ መልኩ እንደዚህ አይነት ግዙፍ ፕሮጀክት የተሰጠው ይህ ግሪንኮም የተባለ ኩባንያም ሆነ ሃላፊዎቹ ፕሮጀክቱን ሰርተው ለማስረከብ የሚያስችላቸው ምንም አይነት ብቃትና ልምድ የሌላቸው ሆነው የተገኙ ሲሆን ይባስ ብሎም የቨርጅንያ ክልል መዝገብ ቤት እንደሚያመላክተው ግሪንኮም ከአንድም ሁለት ጊዜ ከስራ ፈቃድ ጋር በተያያዘ አመታዊ ክፍያውን በአግባቡ ሳይከፍል የንግድ ፍቃዱ እስከ መሰረዝ ደርሶ ነበር።  በ2012 ሚያዝያ ላይ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ውሉን በተፈራረመበት ወቅትም በአሜሪካ ምንም አይነት የስራ ፈቃድ የሌለውና ከነጭራሹም መዝገብ ውስጥ ያልነበረ ፍቃዱም ከ5 ወራት በፊት ተሰርዞ እንደነበር ለማረጋገጥ ተችሏል።

ይሁን እንጂ እነዚህ ሁሉ አጠራጣሪ ምልክቶች በኩባንያው ላይ እየታዩም ቢሆን የኢትዮጵያ መንግስት በቂ የሆነ ጥናት ባለማድረጉ ሊታለል ችሏል። አልያም የመንግስት ባለስልጣናት ስለኩባንያው አጠራጣሪ ማንነት እያወቁ ጆሮ ዳባ ልበስ ብለው ለሕዳሴ ግድብ ከወጣው ብዙም የማይተናነስ ወጪ ያለውን የ3.6 ቢልዮን ዶላር የነጭ ጋዝ ማጣርያ ግንባታ ምንም አይነት ፕሮጀክት ሰርቶ ለማያውቀውና በአግባቡ ቢሮ እንኳን ለሌለው ግሪንኮም አሳልፈው ሰጥተዋል።

በዓለም በሃይል ማመንጨት ዘርፍ አሉ ከተባሉት እመደባለው” የሚለው ግሪንኮም የሱማሌ ክልሉን ፕሮጀክት ለማግኘት ሲል የተለያዩ ከእውነት የራቁ መረጃዎችን ሲያቀርብ ቆይቷል። ስለ ጉዳዩ የተጠየቁት የኢትዮጵያ ማዕድን ነዳጅና ባዮጋዝ ኮርፖሬሽን ዋና ሃላፊ አቶ ሙሉጌታ ዳምጠው “ግሪንኮም በዘርፉ ላይ ምንም አይነት ብቃት እንደሌለው አውቃለው፤ ኩባንያውም ከጅምሩ ግንባታውን እራሱ እንደማያከናውነውና ለሶስተኛ ወገን አሳልፎ እንደሚሰጠው ግልፅ አድርጎ ነው የገባው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። በእርግጥ ይህ የአቶ ሙሉጌታ ምላሽ ግሪንኮም ግንባታውን ለማከናወን ከኮርያው ሆንዳይ ኢንጅነሪንግና ኮንስትራክሽን ጋር በጥምረት እሰራለው በሚል በአንድ ወቅት በይፋ ከማወጁ ጋር የሚሄድ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞም ከአመት በፊት ሚያዝያ ወር ላይ በፋና ብሮድካስቲንግ የተዘገበው ዜና እንደሚያሳየው ግሪንኮም ከኮርያው ሆንዳይ ጋር ለመስራት ተስማምቻለው በሚል አውጆ እንደነበር ያሳያል።

ሆኖም ስለተሳትፎው በተደጋጋሚ የተነገረለት የኮርያው ሆንዳይ ኩባንያን የሚያስተዳድሩት ሃላፊዎች ለኳርትዝ በላኩት ኢሜል ኢትዮጵያ ውስጥ አለ ከተባለው ፕሮጀክት ጋር ፈፅሞ ግንኙነት እንደሌላቸውና ግሪንኮም የነዳጅ ማጣርያውን ለመገንባት አብረውት እንዲሰሩ ጥያቄ አቅርቦላቸው የነበረ ቢሆንም የራሳቸውን ጥናት ካደረጉ በኋላ ላለመሳተፍ እንደወሰኑ ገልፀዋል። የሆንዳይ ኢንጅነሪንግና ኮንስትራክሽን ቃል አቀባይ ጂንሆንግ ቾይ ለጋዜጠኞች  በፃፉት ኢሜልም “ከግሪንኮም ጋር ምንም አይነት ስምምነት እንዳልተፈራረምን እንዲታወቅልን እንፈልጋለን፤ በወቅቱ ለግሪንኮም ስለ ኩባንያው የሚያስረዱ የፋይናንስና የሕግ ሰነዶችን እንዲልክልን ጥያቄ ብናቀርብለትም ምንም አይነት መልስ ሳናገኝ ቀርተናል” የሚል እራሳቸውን ከግሪንኮም ስላገለሉበት ምክንያት ፍንጭ የሚሰጥ ምላሽ ሰጥተዋል።

እንደ ጂንሆንግ ቾይ ምላሽ ድርጅታቸው በዚህም ሳያበቃ ስለ ግሪንኮም ውስጣዊ ምንነት የሚያጠና የሶስተኛ ወገን አካል ቀጥሮ የነበረ ሲሆን “ባገኘነው መረጃ መሰረት ግሪንኮም በወቅቱ ምንም አይነት ሌላ ፕሮጀክት እንደሌለው በመገንዘባችን ኩባንያው በማንኛውም አይነት መግለጫ ላይ ስማችንን ያለፈቃዳችን እንዳያነሳ አሳስበነው ነበር” ይላሉ።

የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ስለ ግሪንኮም ትንሽ እንኳን ጥናት ቢያደርጉ ኖሮ ኩባንያው እንደሚለው ሳይሆን ከሆንዳይ ኢንጅነሪንግና ኮንስትራክሽን ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌለው በቀላሉ ለመረዳት በቻሉ ነበር። ልክ የኳርትዝ ጋዜጠኞች እንዳደረጉትም የሆንዳይ ሃላፊዎችን ከግሪንኮም ስላላቸው ግንኙነትና በእርግጥ በግንባታው ላይ እንደሚሳተፉ ለመጠየቅ ሞክረው ቢሆን ኖሮ ኢትዮጵያ ውሉን ከመፈራረሟ ገና ከአራት ወራት በፊት ሆንዳይ ፕሮጀክቱ ላይ የመሳተፍ ፍላጎት እንደሌለው ማሳወቁን በተረዱም ነበር። ታድያ ለምን ሳያጣሩ ቀሩ? ወይስ ይህን ያህል የዋሆች ናቸው?

የግሪንኮም ማጭበርበር በዚህ የሚያበቃም አይደለም። ዋና ስራ አስክያጅ በመሆን ላለፉት 10 ዓመታት ሲያገለግል ቆይቷል የተባለው ትውልደ ኢትዮጵያዊ አቶ ነብዩ ጌታቸው በአሜሪካ አሉ የተባሉ ኩባንያዎችን ሲያማክር እንዲሁም በከፍተኛ አመራር ደረጃ ሲያገለግል እንደኖረና በርካታ ልምድን ያካበተ ስለመሆኑ በግሪንኮም ድህረ ገፅ ላይ የተፃፈ ቢሆንም አቶ ነብዩ በየትኛውም የአሜሪካ ትልቅ ድርጅት በከፍተኛ አመራር ደረጃ እንዳገለገለም ሆነ እንዳማከረ የሚያሳይ መረጃ ሊገኝ አልቻለም። አቶ ነብዩ ከትላልቅ ድርጅቶች ጋር ያለው ብቸኛው ግንኙነት በቨርጂንያ ክልል በአንድ የቶዮታ መኪና መሸጫ ውስጥ ተቀጥሮ መስራቱ ብቻ ነው።

በተጨማሪም የግሪንኮም ከፍተኛ አመራር ተብለው በድህረገፁ ፎቷቸውና የስራ ልምዳቸው የተዘረዘረው ግለሰቦች አምስት ነጭ አሜሪካውያን ሶስት እስያውያንና አቶ ነብዩን ጨምሮ ሁለት ኢትዮጵያውያን ወይም ትውልድ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ በሃይል ማመንጨትና በተለያዩ ዘርፎች በከፍተኛ አመራርነት አሉ በተባሉ ኩባንያዎች እንዲሁም በግል ድርጅቶቻቸው እንዳገለገሉ ቢፃፍም ኳርትዝ ባደረገው ምርመራ እንዲሁም ኢትዮኖሚክስ ባደረገው ተጨማሪ ምርመራ የነዚህ ሰዎች የስራ ልምድም ሆነ ማንነት በጣም አጠራጣሪ ሆኖ ተገኝቷል።

የግሪንኮም ሃላፊዎች ተብለው ፎቷቸው ከተለጠፉት ሰዎች ውስጥ በኮርያ የእርዳታ ድርጅት ተቀጥሮ የሚሰራና ፎቶው ከኢንተርኔት ተሰርቆ የተለጠፈበት ግለሰብ ይገኝበታል

ይባስ ብሎም ከግሪንኮም ሃላፉዎች አንዱ ነው የተባለውና ከየመን እስከ ኮርያና ኢንዶኔዥያ ድረስ ነዳጅ በማውጣትና እንደ ሃንት ኦይል በመሳሰሉት ግዙፍ የአሜሪካ የነዳጅ አውጪ ኩባንያዎች በመስራት የ50 አመታትን ልምድ እንዳካበተ የተነገረለት ሃላፊ እንኳን የነዚህ ሁሉ ልምዶች ባለቤት ሊሆን ይቅርና ግሪንኮም ፎቶውን ከኢንተርኔት ላይ ሰርቆ በድህረ ገፁ ላይ የለጠፈበት በኮርያ በአንድ ተራ የእርዳታ ድርጅት ውስጥ ተቀጥሮ የሚሰራ ግለሰብ ሆኖ ተገኝቷል። ስለ ግለሰቡ ይበልጥ ለማጣራት ወደ አሜሪካው የነዳጅ ኩባንያ ሃንት ኦይል መልዕክት የላኩት የኳርትዝ ጋዜጠኞችም በድርጅታቸው አገልግሏል ስለተባለው ግለሰብ ምንም እንደማያውቁና በየትኛውም ጊዜ ከነሱ ጋር ሰርቶ እንደማያውቅ አረጋግጠዋል።

የግሪንኮም ዋና ስራ አስክያጅ አቶ ነብዩ ጌታቸው በ2012 የነጭ ጋዝ ማጣርያውን ለመገንባት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር የ3.6 ቢልዮን ዶላር ውል በተፈራረሙበት ሰሞን ፕሮጀክቱ ሲያልቅ ኢትዮጵያ ከውጭ ከሚመጣ ጋዝ ትላቀቃለች ብለው ነበር። ግሪንኮምን ወክለው ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር የተፈራረሙት ሌላኛው ግለሰብ አቶ አማኑኤል መኩርያ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ ከአስር ሺ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የስራ እድል እንደሚፈጥርም ገልፀው ነበር። ታድያ ዛሬ የሃይል ማመንጨት ባለሙያ ሁነው ብቅ ይበሉ እንጂ አቶ አማኑኤል ከዚህ በፊት የሚታወቁት አዲስ አበባ ላይ ባላቸው ታዋቂ የጃዝ መሸታ ቤት ነበር።

አሁንም ጥያቄው እንደዚህ አይነት አጠያያቂ የሆነ ማንነትን ይዞ የመጣው ግሪንኮም እንዴት ይህንን የሚያክል ግዙፍ የ3.6 ቢልዮን ዶላር ፕሮጀክት ከመንግስት ሊረከብ ቻለ ነው። በ2011 ሪፖርተር ጋዜጣ በእንግሊዘኛ እትሙ ባወጣው ፅሁፍ ላይ በወቅቱ የኢትዮጵያ ማዕድን ነዳጅና ባዮጋዝ ዳይሬክተር የነበሩት አቶ አንዳርጌ በቀለ ስለ ግሪንኮም በቂ ጥናት እንዳከናወኑ የገለፁ ሲሆን “የኩባንያውን የፋይናንስ የቴክኒካልና የሕግ አቋም በአግባቡ ገምግመን የሚያረካ ውጤት አግኝተናል” ብለው ነበር።

ከሁለት አመታት በኋላ ኳርትዝ አቶ አንዳርጌን አግኝቶ እንዴት እነዚህ ሁሉ አጠራጣሪ ምልክቶችን እያዩ የግሪንኮምን ፕሮፖዛል ተቀብለው አፀደቁ ብሎ ላቀረበላቸው ጥያቄ “አንድን ኩባንያ ገና ለገና የሚያምታታ ነገር አገኘንበት ብለን እንዲሸሽ ማድረግ የለብንም” ካሉ በኋላ “ኢትዮጵያ ከዚህ የምትጠቀመው ነገር ሊኖር ይችላል፤ በዛላይ ደግሞ ከኛ በተጨማሪ ሌሎች የመንግስት ተቋማትም ፕሮፖዛሉን አፅድቀውታል” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ሌላኛው የማዕድን ነዳጅና ባዮጋዝ መስርያቤት ሃላፊ አቶ ሙሉጌታ ዳምጠው በበኩላቸው መስርያቤታቸው ከግሪንኮም ጋር ስለ ቴክኒካል ጉዳዮች በመወያየት ላይ እያለ የማዕድን ሚንስቴር ጣልቃ በመግባት ሃላፊነቱን ተረክቦ ጉዳዩን መከታተል እንደጀመረና የሳቸው መስርያቤትም ከሂደቱ እንደተገለለ ገልፀዋል።

አምባሳደር ፍፁም አረጋ በዋሽንግተን ዲሲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ

ግሪንኮም በድህረገፁ ላይ ያሰፈራቸው የተለያዩ ሃሰተኛ መረጃዎች እንዴት በመንግስት ዘንድ ጥያቄን አላስነሱም ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄም ሃላፊው ሲመልሱ ኩባንያው ከጠቅላይ ሚንስትሩ ፅህፈት ቤት ጀምሮ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር በመሆን ከሚያገለግሉት አቶ ፍፁም አረጋና ሌሎች የበላይ አካላት ድጋፍ እንደነበረውና ይህንን ግንኙነት ተጠቅሞ ሂደቱን ለማፋጠን እንደቻለ አስታውቀዋል። አቶ ሙሉጌታ ሲያብራሩም  “ነገሮች ሲጓተቱ የኩባንያው ሃላፊዎች ወደ ጠቅላይ ሚንስትሩ ቢሮ መጉላላት ደረሰብን የሚል ደብዳቤ ይፅፋሉ፤ ሰዎቹ ግንኙነት አላቸው” ይላሉ።

አቶ ሙሉጌታ ለግሪንኮም ድጋፍ የሚሰጡ ሁለት ደብዳቤዎች ከአምባሳደር ፍፁም አረጋ ወደ መስርያ ቤታቸው እንደተላከም ያወሳሉ። አምባሳደር ፍፁም መጀመርያ በጠቅላይ ሚንስትሩ ቢሮ ሲሰሩ ኋላም በአሜሪካ አምባሳደር ሆነው ከተሾሙ በኋላ በፃፏቸው ሁለት ደብዳቤዎች ግሪንኮም አስተማማኝ ኩባንያ እንደሆነና ኢትዮጵያ ውስጥ ገብቶ ለመስራት ብቃት እንዳለው መስክረውለት ነበር ሲሉ አቶ ሙሉጌታ ያስታውሳሉ።

በሌላ በኩል በ2012 ሚያዝያ ላይ የኢትዮጵያ መንግስትን ወክለው የተፈራረሙትና በወቅቱ የማዕድንና ነዳጅ ሚንስትር የነበሩት አቶ ሳሙኤል ኡርካቶ ባሳለፍነው ነሓሴ ያለ ምንም ማብራርያ ከሃላፊነታቸው በድንገት የተነሱ ሲሆን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስትር ሆነው ተሾመዋል። የአቶ ሳሙኤል ቦታን በመተካትም ስለ ግሪንኮም ፕሮጀግት ምንም የሚያውቁት ነገር እንደሌለ የተናገሩት የቀድሞው የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ የማዕድንና ነዳጅ ሚንስትር ሆነው ከወራት በፊት ተሹመዋል።

ኳርትዝ አቶ ሳሙኤልን በስልክ አግኝቶ ስለ ፕሮጀክቱ ጥያቄ ቢያቀርብላቸውም ስለ ጉዳዩ ለመነጋገር ፍቃደኛ እንዳልሆኑ ገልፀው ስልኩን ዘግተውታል። በግሪንኮምና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል በተደረገው የፊርማ ስነስርአት ላይ ከቀሞው የማዕድንና ነዳጅ ሚንስትር አቶ ሳሙኤል አጠገብ በስፍራው የነበሩት ዶ/ር ቀፀላ ታደሰ በወቅቱ በሚንስቴር መስርያቤቱ የነዳጅ ፈቃድ ሰጪ ዳይሬክተር ሆነው ያገለግሉ የነበሩ ሲሆን በፊርማ ስነስርአቱ ላይ የመንግስት ሚድያዎች በተገኙበት ግሪንኮምን ሲያሞግሱ ታይተው ነበር። ኳርትዝ ዶ/ር ቀፀላንም በተመሳሳይ መልኩ ሊያናግራቸው ቢሞክርም ፈቃደኛ አልሆኑም ነበር። ዶ/ር ቀፀላ ግሪንኮም ከኢትዮጵያ መንግስት በተፈራረመ በአጭር ጊዜ ውስጥ ጡረታ እንደወጡ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

ከግሪንኮም ጋር የተገባው ውል መፍረስ

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኳርትዝ ጋዜጣ ያተመውን ዝርዝር ተከትሎ ሁለት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የማዕድንና ነዳጅ ሚንስትር ባለስልጣናት የማጣርያ ጣብያውን ለመገንባት ከግሪንኮም ጋር የገቡትን የ3.6 ቢልዮን ዶላር ውል ሊያፈርሱት እንደሆነ ገልፀዋል።፡የማዕድንና ነዳጅ ሚንስቴር ሚንስትር ዲኤታ ዶ/ር ኮዋንግ ቱትላም መስርያ ቤታቸው ውሉን ለማፍረስ ወስኗል የሚል መልዕክት እንደላኩለት ጋዜጣው በሌላኛው እትሙ ዘግቧል። የመጀመርያው ዘገባ እየተሰራ በነበረበት ወቅት ጋዜጠኞቹን ለማነጋገር ፈቃደኛ ያልነበሩት ባለስልጣናትም ዘገባው ያስከተለውን ቁጣ ተገንዝበው ይመስላል ዳግም ለማነጋገር በተደረገው ሙከራ የተሻለ ፈቃደኛነት እንደነበራቸው ኳርትዝ ይገልፃል። ሚንስትር ዲኤታ ዶ/ር ኮዋንግ ፕሮጀክቱ ለግሪንኮም ሲሰጥ በወቅቱ በሃላፊነት ላይ እንዳልነበሩ አስምረው “አንዳንዶቻችን ስለ ኩባንያው ታማኝነት ጥርጣሬ ነበረን፤ ስለዚህም መንግስት ብዙ ኪሳራ ሊያስከትል ወደሚችል ውል እንዳይገባ ሙከራ አድርገን ነበር” ይላሉ።

ዶ/ር ኮዋንግ ይቀጥላሉ “እንዳውም ከግሪንኮም ጋር የተገባው ውል ግንባታ ሳይጀመር ለአንድ አመት ያህል ጥናት በማድረግ ብቻ እንዲወሰን ቢልም ገና ስራ ሳይጀመር ቀብድ እንዲከፈላቸው በጣም ፈልገው ነበር። ስራ ከመጀመራቸው በፊት የ100 ሚልዮን ዶላር ቀብድ ሲጠይቁም እቅዳቸው ቀብዱን እንደ መነሻ ተጠቅመው በቢልዮን ዶላሮች የሚቆጠር ገንዘብ ከውጭ መበደር እንደነበር በኋላ ነው የተረዳነው። 100 ሚልዮን ዶላሩ እንዲፈቀድላቸው ከበላይ አካላት ከፍተኛ ጫና ቢደረግብንም እኛ ግን አሻፈረን ነበር ያልነው” በማለት ኩባንያው ገንዘብ ቶሎ ለመቀበል የነበረውን ፍላጎትና ምን ያህል የመንግስት ባለስልጣናት ድጋፍ እንደነበረው ያብራራሉ። ታድያ ሚንስትር ዲኤታው “የበላይ አካላት” ያሏቸውን ሰዎች ማንነት ለመግለፅ አልፈለጉም።

ስለዚህ አወዛጋቢ ጉዳይ አምባሳደር ፍፁም አረጋም ሆነ የጠቅላይ ሚንስትሩ ቢሮ ይፋዊ መግለጫ ያልሰጡ ቢሆንም አምባሳደር ፍፁም አረጋ ግን ትዊተር በተባለው የማህበራዊ ድህረ ገፅ ላይ ከኳርትዝ ጋዜጠኛ ዘካርያስ ዘላለም ጋር አንድ ሁለት ሲባባሉ ተስተውለው ነበር። ለመሆኑ የኢትዮጵያ መንግስት ስንት ፕሮጀክቶችን ለሌሎች ግሩንኮሞች አሳልፎ ሰጥቶ ይሆን?

 

 

 

በአክሱም ከተማ ስለተፈፀመው ጭፍጨፋ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ሙሉ ሪፖርቱን ይፋ አደረገ

0

 

ተቀማጭነቱን በለንደን ከተማ ያደረገውና በሰብአዊ መብት ጉዳዮች ላይ በመላው አለም ክትትል የሚያደርገው አምነስቲ ኢንተርናሽናል ከሰአታት በፊት ባወጣው ባለ 25 ገፅ ሪፖርት ከሕዳር 21 እስከ ሕዳር 22 ባሉት 24 ሰአታት ውስጥ ብቻ የኤርትራ ወታደሮች በአክሱም ከተማ ነዋሪ በሆኑ ንፁሃን ላይ ጭፍጨፋ ስለማካሄዳቸውና በመቶዎች የሚቆጠሩ መገደላቸውን ይፋ አድርጓል። ዝርዝር ሪፖርቱ በተጨማሪም ጭፍጨፋው ከመካሄዱ 9 ቀናት ቀደም ብሎ ሕዳር 12 ከሸረ አቅጣጫ የመጣው የኢትዮጵያና የኤርትራ መከላከያ ሃይሎች ጥምር ሃይል የአክሱም ከተማን ከሩቅ በመድፍ እንደደበደበና ሴቶችና የታዘሉ ህፃናትን ጨምሮ ከመድፍ በተተኮሱ ጥይቶች በርካታ ንፁሃን እንደተገደሉ ያሳያል።

“ሕግ ማስከበር” በሚል ዘመቻ ከ 4 ወራት በፊት የተጀመረው ዘመቻ እስካሁን የበርካቶችን ህይወት ቀጥፏል። በተለይም የተለያዩ የትግርኛ ቋንቋ የዜና አውታሮች በኤርትራና በኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት አባላት፤ እንዲሁም ከጎረቤት ክልል በመጡ የአማራ ሚልሻዎች ስለተፈፀሙ ጭፍጨፋዎች እየተዘገበ የቆየ ቢሆንም ክልሉ ሙሉ በሙሉ ማለት ይቻላል ከውጭው አለም ጋር እንዳይገናኝ ተደርጎ መቆየቱ ተፈፀሙ ስለተባሉት ጭፍጨፋዎች በቂ ማስረጃ ሳይገኝ ቆይቷል።

ሆኖም ባለፈው ጥር ደብረ አባይ በተባለች መንደር በኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት አባላት የተፈፀመ ጭፍጨፋን የሚያሳየውን ቪድዮ ጨምሮ የተለያዩ የፎቶና የቪድዮ ማስረጃዎች በግላጭ ወደ አደባባይ መውጣት የጀመሩ ሲሆን ዛሬ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያወጣው በአይን ምስክሮችና በሳተላይት ፎቶዎች የተደገፈ ዝርዝር ሪፖርት በአለም አቀፍ ሕግ በጦር ወንጀል ሊያስጠይቁ የሚችሉ ወንጀሎች በትግራይ እንደተፈፀሙ ያሳያል።

 

ሕዳር 19

ከሰአት በኋላ ከበስተ ምዕራብ ከሽረ ከተማ አቅጣጫ ወደ አክሱም የመጣው የኤርትራና የኢትዮጵያ መከላከያ ጥምር ሃይል ወደ ከተማዋ ከተጠጋ በኋላ መድፍ መተኮስ ጀመረ። በወቅቱ  የትግራይ ልዩ ሃይል አባላትም ሆነ የትግራይ ሚልሻ ቀደም ብሎ አክሱምን ሙሉ በሙሉ ለቆ ወጥቶ የነበረ በመሆኑ ከኤርትራና ኢትዮጵያ ጥምር ሃይል የሚተኮሰው መድፍ በንፁሃን ላይ ሲያርፍ እንደነበር አምነስቲ ያነጋገራቸው የአይን እማኞች ይናገራሉ። በተኩሱ የተደናገጡ በርካታ የአክሱም ነዋሪዎች ከተማዋን ለቀው ለመሸሽ ሲጣደፉ እንደተመለከቱና አንዳንዶችም በድልድዮችና ህንፃዎች ስር ለመደበቅ ሲሞክሩ እንደተመለከቱ የአይን እማኞች መስክረዋል። በርካታ ወጣቶች፣ አረጋውያንና አንዲት ህፃን ልጅ ያዘለች እናት ለመሸሽ ስትሮጥ ከነልጇ ተመታ እንደተገደለች ሪፖርቱ ይዘግባል።

በመቀጠልም ጥምር ሃይሉ ከተማዋን ከተቆጣጠረ በኋላ የኤርትራ ወታደሮች የትግራይ ልዩ ሃይል አባላትንና ሚልሻዎችን ለማግኘት የቤት ለቤት አሰሳ ቢጀምሩም ምንም አይነት ታጣቂ ሳያገኙ በርካታ ንፁሃንን በተለይም ታዳጊዎችን ጨምሮ ወንዶችን እየለዩ ረሽነዋል። አንዲት የከተማው ነዋሪ ለአምነስቲ በሰጠችው ቃል ወታደሮቹ በየቤቱ እየገቡ “ወንዶቹን አውጡ” እያሉ ብዙ ግድያ መፈፀማቸውን የመሰከረችበት በሪፖርቱ ላይ ተካቷል።

ሪፖርቱ አክሎም የከተማው ነዋሪዎች ስልካቹን አምጡ እየተባሉ ማንኛውም አይነት ከህወሃት ጋር ንክኪ ያለው ፎቶ ከተገኘ እንደተገደሉና የተቀሩትም እንደተዘረፉ ይገልፃል። እንደ ሌላ የአይን እማኝ ምስክርነት ደግሞ በሞተር ሳይክል ሲጓዙ የነበሩ ሁለት ሰዎች የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የደንብ ልብስ በለበሱ ወታደሮች ሲገደሉ የተመለከተ ቢሆንም በርካታ የኤርትራ ወታደሮች የኢትዮጵያ የደምብ ልብስ የሚለብሱ በመሆኑ ገዳዮቹ ከየትኛው ወገን እንደሆኑ እርግጠኛ መሆን ሳይችል እንደቀረ ተናግሯል።

 

ሕዳር 22

ለቀናት የቀጠለውን ጭፍጨፋ ተከትሎ ሕዳር 22 የትግራይ ሚልሻ ይሁኑ ወይም የትግራይ ልዩ ሃይል በውል ያልታወቁ ታጣቂዎች  ከአክሱም ፅዮን ማርያም ቤ/ክ በስተምስራቅ በሚገኝ ማይ ቆሆ ተብሎ በሚጠራ ተራራ አካባቢ በሰፈረው የኤርትራ ጦር ላይ ጠዋት አካባቢ ቶክስ ይከፍታሉ። ይህ በአይን እማኞች ግምት ከ50 እስከ 80 የሚሆን ቁጥር ያለው የትግራይ ሃይል ወድያውኑ ከአካባቢው ነዋሪዎች ድጋፍ ማግኘት የጀመረ ሲሆን የአክሱም ወጣቶች ቢለዋ፣ ዱላና ድንጋይ በመያዝ ውግያውን መቀላቀላቸውን አምነስቲ ገልጿል። ይሁን እንጂ በኤርትራውያኑ ላይ ተኩስ የከፈቱት እንደተጠበቀው የትግራይ ልዩ ሃይል አባላት ሳይሆኑ የአካባቢው ታጣቂዎች እንደሆኑና በርካታ የኤርትራ ወታደሮችን መግደላቸውን አንድ ሁኔታውን የተመለከተ እማኝ ቢገልፅም እንደ ሌሎች እማኞች ምስክርነት ግን ከኤርትራውያኑ ጋር ከባድ የሃይል ሚዛን ልዩነት እንደነበር የትግራይ ወጣቶች ምንም የመሳርያ ልምድ የሌላቸውና በደንብ ከታጠቁትና ከሰለጠኑት የኤርትራ ወታደሮች ጋር ሊመጣጠኑ እንዳልቻሉ ገልጿል።

ከቀኑ 9 ሰአት እስከ 10 ሰአት ባለው ሰአትም የኤርትራ ወታደሮችን የጫኑ ገልባጭ መኪኖች ለእገዛ በሰልፍ ወደ አክሱም የገቡ ሲሆን 10 ሰአት ላይ ጭፍጨፋው እንደተጀመረ ሌላ የአይን እማኝ ያብራራል። የአይን እማኙ አክሎም ወታደሮቹ በቀጥታ ወደ ጅምላ ጭፍጨፋ መግባታቸውን ይገልፃል። በአክሱም ዩንቨርስቲ መምህር የሆነ ሌላ ምስክር በበኩሉ በአንድ ህንፃ ላይ ከሁለተኛ ፎቅ ሆኖ ኤርትራውያኑ በአስፋልት ላይ የነበሩ ወጣቶችን ሲገድሉ በአይኑ እንደተመለከተና ወንዶች እየተመረጡ እየተገደሉ መሆኑን ሲያውቅ ከከተማ ሸሽቶ እንደወጣ ለአምነስቲ ቃሉን ሰጥቷል።

አምነስቲ ያናገራቸው 40 የሚሆኑ ምስክሮች ሁሉም ማለት ይቻላል ቃላቸውን የሚያስማማ ነገር ቢኖር ጭፍጨፋው በተከናወነባቸው ቀናት በአክሱም ምንም አይነት የትግራይ ልዩ ሃይልም ሆነ ሚልሻ እንዳልነበረና ጭፍጨፋው በንፁሃን ላይ በተለይም ወንዶች ላይ ለይቶ ያተኮረ እንደነበር ነው።

አምነስቲ በሪፖርቱ አክሎ እንዳስረዳውም ኤርትራውያኑ በተደጋጋሚ ለአክሱም ሕዝብ ጭፍጨፋው ማስጠንቀቅያ እንደሆነና ማንኛውም አይነት ጥቃት ከሕዝቡም ሆነ ከታጣቂዎች የሚሰነዘርባቸው ከሆነ ደግመው እንደሚፈፅሙት አስጠንቅቀዋል። አንድ ምስክር ሲያስረዳ ወደ አራት መቶ የሚሆኑ ወጣቶች በአንድ የተጀመረ ህንፃ መሰረት ባለ ጉድጓድ ውስጥ ታጉረው ከዚህ በኋላ ምንም አይነት ትግል ቢያደርጉ በጅምላ እንደሚጨፈጨፉ ስለዚህም የኤርትራውያኑን ወረራ በዝምታ እንዲቀበሉ ማስጠንቀቅያ በወታደሮቹ ተሰጥቷቸዋል።

የጅምላ መቃብሮች

በየአስፋልቱ ከተገደሉትና በቤት ለቤት አሰሳ ከተረሸኑት በመቶዎች የሚቆጠሩ የአክሱም ነዋሪዎች በተጨማሪ ከየቤቱና ከየመንገዱ ሬሳ ለቅመው በጋሪ እየጫኑ ወደ ጅምላ መቃብር ለመጓዝ ሲሞክሩ የነበሩትም ቶክስ እንደተከፈተባቸውና ብዙዎች እንደተገደሉ በኋላ ግን መንገድ ላይ የተጣለው የብዙዎች ሬሳ መፈረካከስ በመጀመሩና በአካባቢው ሽታ በመፍጠሩ ወስደው እንዲቀብሩ ስለተፈቀደላቸው በርካቶችን በጅምላ መቃብሮች ለመቅበር እንደቻሉ አምነስቲ ያነጋገራቸው 9 የቀብሩ ተሳታፊዎች ገልፀዋል። የጅምላ ጭፍጨፋው ሰለባ የሆኑት በአክሱም ቅዱስ ሚካኤል፣ አቡነ አረጋዊ፣ እንዳ ጋበር፣ አባ ፔንቴሌዎንና እንዳ እየሱስ አብያተ ክርስትያናት ተቀብረዋል። በአምነስቲ የተለቀቁ የሳተላይት ምስሎችም በአብያተ ክርስትያናቱ ዙርያ በቅርቡ ተቆፍረው የተደፈኑ ጉድጓዶች እንዳሉ ያረጋግጣሉ።

ከ50 በላይ ሬሳዎችን ወደ መቃብር ስፍራዎች እንዳጓጓዘ የሚናገር አንድ ግለሰብ በሕዳር 23 ብቻ 400 የሚሆኑ ሬሳዎችን እንደቆጠረ ሲናገር ሌላ የአይን እማኝ በበኩሉ 200 ሬሳዎችን በተለያዩ የቀብር ስነስርአቶች ላይ እንደተመለከተ ተናግሯል።

በአክሱም ሰመረት ሰፈር የሚገኘው አቡነ አረጋዊ ቤ/ክ በቅርቡ ትልልቅ የጅምላ መቃብሮች እንደተቆፈሩበት ያሳያል
ትልቁ የቀብር ስነስርአት የተፈፀመው በዚህ አርባዕቱ እንስሳት በተባለ ቤ/ክ ሲሆን ሁለት የጅምላ መቃብሮች ታህሳስ 6 በተነሳ የሳተላይት ምስል ይታያሉ

የጅምላ ዝርፍያ

በወታደሮች ከተጨፈጨፉት የአክሱም ነዋሪዎች በተጨማሪም የበርካታ ሰዎች መኖርያ ቤት፣ ሱቆች፣ ሆቴሎችና የተለያዩ የግልም ሆነ የመንግስት ተቋማት በመዘረፋቸው ሕዝቡ የሚበላው እስከ ማጣት እንደደረሰ አምነስቲ ይገልፃል። በተለይም ኤርትራውያኑ የውሃና የመብራት መሰረተ ልማትን ማውደማቸው የከተማው ነዋሪ ከወንዝና ኩሬ ንፅህናውን ያልጠበቀ ውሃ ለመጠጣት ተገዷል። የኤርትራ ወታደሮች ሲዘርፉ በአካባቢው የነበሩ የኢትዮጵያ ወታደሮችን እርዳታ እንደጠየቁ የተናገሩት ሌሎች ነዋሪዎች ኤርትራውያኑ እንዲያቆሙ ከኢትዮጵያ ወታደሮች ጥያቄ ቢቀርብላቸውም “ምን አገባህ አንተ አህያ” የሚል መልስ እንደተሰጣቸውና ዝም ብለው ሲመለከቱ እንደነበር መስክረዋል።

በተለይም የከተማዋ ሆስፒታሎችን መዘረፍና የህክምና ባለሙያዎችን መሸሽ ተከትሎ በርካታ ለሞት የማያበቃ ጉዳት የደረሰባቸው ነዋሪዎች በህክምና ማጣት ለሞት ተዳርገዋል። አንድ እማኝ ሲናገር “በቁርጭምጭሚቱ ላይ ተመቶ በህክምና ማጣት የሞተ ሰው አይቻለው…ሌላ ደሞ አንድ ሆዱን የተመታ ጓደኛዬ ሆስፒታል ውሰደኝ እያለ ቢለምነኝም እዛ ምንም እንደማያገኝ ስላወኩ ልረዳው አልቻልኩም። በመጨረሻም ደከመኝ እንቅልፌ በጣም መቷል እያለ ሞተ” ሲል ይገልፃል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከምግብ መድሃኒትና ቁሳቁሶች ዝርፍያ በኋላ ትልቅ ችግር ላይ የወደቀው የአክሱም ሕዝብ ለረሃብ በመጋለጡ አንዳንድ አማራጭ ያጡ ነዋሪዎች ኤርትራውያኑ ከፍተው የተዋቸውን ሱቆችና ምግብ ቤቶች ወደ መዝረፍ መግባታቸውንም ሪፖርቱ ያነሳል።

ሁሉም ምስክሮች ማለት ይቻላል በአክሱም ላይ የተደረገው ጭፍጨፋ በኤርትራ ወታደሮች እንደተፈፀመ ይገልፃሉ። ለዚህ እንደ ማስረጃ ያነሷቸውም ወታደሮቹ ሲጓጓዙባቸው የነበሩት የጭነት መኪኖች የኤርትራ ታርጋ ያላቸው መሆኑን፣ ወታደሮቹ በአብዛኛው የኤርትራ የመከላከያ ደንብ ልብስ የለበሱ መሆናቸውን፣ የኢትዮጵያ የመከላከያ ደንብ ልብስ የለበሱትም ቢሆን በሚያደርጉት ኮንጎ ጫማና በሚጠቀሙት የትግርኛ ቅላፄ ወይም አረብኛ ቋንቋን በቀላሉ እንደሚለዩ ብሎም ከአንዳንድ እንደ ቤን አሚር ያሉ የኤርትራ ብሔረሰቦች የመጡ ወታደሮች ደግሞ ፊታቸው ላይ ያለውን የመተልተል ምልክት ናቸው። በተጨማሪም አንዳንድ ወታደሮች በግልፅ ኤርትራውያን እንደሆኑ ነግረውናልም ይላሉ የአክሱም ነዋሪዎች።

ይህ በአክሱም የተፈፀመ የጅምላ ጭፍጨፋ በተለያዩ ከተሞች እንደተፈፀመም የሚያመላክቱ በርካታ መረጃዎች ከትግራይ እየወጡ ይገኛሉ። በድብረ አባይ የተቀረፀው ቩድዮ ጂኦ ሎኬቲንግ በሚባለው ቴክኖሎጂ በመጠቀም ቦታው በእርግጥ ደብረ አባይ መሆኑን ለማረጋገጥ የተቻለ ሲሆን በቪድዮው ላይ በትንሹ 25 የሚሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች በኢትዮጵያ ወታደሮች ተገድለው ሬሳቸው መሬት ላይ ወድቆ ይታያል። ቪድዮው ይበልጥ ትኩረት እንዲያገኝ ያደረገው ደግሞ ካሜራ ይዞ የሚቀርፀው የኢትዮጵያ ወታደር መሆኑና ጭፍጨፋው የተፈፀመውም በሱና በሌሎች የኢትዮጵያ መከላከያ አባላት መሆኑን የሚያመላክት በቂ መረጃ እራሱ በቀረፀው ቪድዮ ላይ መኖሩ ነው።

በሌላ በኩል በእዳጋ ሓሙስ፣ በሽረ፣ በኢሮብ፣ በዛላምበሳ፣ በገርሁ ሰናይ፣ በእዳጋ አርቢ፣ በሁመራ፣ በአድዋና በተለያዩ የምዕራብ ትግራይ ወረዳዎች በኢትዮጵያ መከላከያ አባላት፣ በኤርትራ ወታደሮችና በአማራ ሚሊሻዎች የጅምላ ጭፍጨፋዎች እንደተካሄዱና አሁንም እየተካሄዱ እንደሆነ የሚያመላክቱ መረጃዎች በየቀኑ እየወጡ ይገኛሉ።

የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት እንደሚያመለክተው በትግራይ ክልል ከፍተኛ የጦር ወንጀሎች የተካሄዱ ሲሆን የጅምላ ጭፍጨፋ፣ የቅርስ ማውደም፣ የመሠረተ ልማት ማውደም፣ ሴቶችን በጅምላ መድፈርና ወዘተ የመሳሰሉት ወንጀሎች በአለም አቀፍ ሕግ ሊያስጠይቁ የሚችሉ ናቸው።

 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከፊል ድርሻ ለቱርክ መንግስት ሊሸጥ ነው

0

ዛሬ ከዋሽንግተን ዲሲ አካባቢ የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው በጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የሚመራው የኢትዮጵያ መንግስት የኢትዮጵያ አየር መንገድን እስከ ግማሽ የሚጠጋ የባለቤትነት ድርሻ ለቱርክ አየር መንገድ ለመሸጥ ጥያቄ ማቅረቡን ያመላክታል። ከቀናት በፊት በምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን የሚመራ አንድ የልኡካን ቡድን ወደ ቱርክ ተጉዞ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን ጉዳዩ የተነሳውም ከቱርክ ባለስልጣናት ጋር በተደረገ ዝግ ስብሰባ ላይ እንደሆነ የተገኘው መረጃ አክሎ ገልጿል።

አንድ የሶስተኛ ወገን አለም አቀፍ ተቋምን እንደ ምንጭ የሚጠቅሰው ይህ መረጃ ለዚህ የአየር መንገድ ባለቤትነት ድርሻ ኢትዮጵያ ከጥሬ ገንዘብ በተጨማሪ 3 የቱርክ ስሪት ያላቸው TB2 ተዋጊ ድሮኖችን ብሎም  የተለያዩ የጦር መሳርያዎችን በክፍያ መልክ ለመቀበል ዝግጁነቷን ለቱርክ መንግስት በሚስጥር ገልፃለች። ይህ መረጃ የወጣው ኢትዮጵያ የሚጠበቅባትን የ66 ሚልዮን አመታዊ የብድር ወለድ ለመክፈል እንዳቃታት ከጥቂት ሳምንታት በፊት በይፋ በገለፀችበትና በኢትዮጵያ ፌደራላዊ መንግስትና ከስልጣን ተገፍቶ በወጣው የትግራይ ክልል መንግስት መካከል እየተደረገ ያለው ጦርነት በተጋጋለበት ወቅት ነው።

ከቅርብ ቀናት በፊት ኢትዮኖሚክስ ከአካባቢው የደረሰው መረጃ እንደሚያመለክተው ከአማራ ክልል ወደ መቀሌ በሚያገናኘው ዋና መንገድ ላይ የምትገኘው አዲ ጉደም ከተማና ሌሎችም ከመቀሌ በስተ ደቡብና ምስራቅ የሚገኙ ወሳኝ ቦታዎች እራሱን የትግራይ መከላከያ ሃይል ብሎ በሚጠራው ጦር ቁጥጥር ስር መግባታቸውን ተከትሎ በትግራይ ክልል ሙሉ በሙሉ የመብራትና የስልክ ግንኙነት ዳግም እንዲቋረጥ በተደረገበት ሰዐት ነው። TB2 በመባል የሚጠሩት እነዚህ በሪሞት የሚበሩ የቱርክ ድሮኖች ጥቅምት ወር ላይ በአዘርባጃንና አርሜንያ መካከል በተደረገው የድንበር ጦርነት ከፍተኛ አስተዋፅኦን ማበርከታቸው የሚታወስ ነው።

የቱርክ ሰው አልባ ተዋጊ ድሮን

ከላይ የተጠቀሰው መረጃ አክሎም ኢትዮጵያ በተመሳሳይ መልኩ የኢትዮ ቴሌኮምን የተወሰነ ድርሻ ቮዳፎን ተብሎ ለሚጠራው አለም አቀፍ የግል ኩባንያ እንዲሁም የተለያዩ ኢንዱስትሪ ፓርኮችን ለቻይና ለመሸጥ በተጣደፈ እንቅስቃሴ ላይ እንዳለች ያሳያል።

የጠቅላይ ሚንስትሩ እቅድ ተሳክቶ እነዚህ ተቋማት በቅርቡ ከተሸጡ በቢልዮኖች ዶላር የሚቆጠር ገቢ ሊያስገኙ የሚችሉ ቢሆንም ይህ ገንዘብ በትክክል ለምን ይውላል የሚለው ጉዳይ አጠያያቂ ሆኗል። ከሳምንት በፊት በአምባሳደር ግርማ ብሩና በፋይናንስ ሚንስትር አህመድ ሽዴ የሚመራ ሌላ የልኡካን ቡድን ወደ ዋሽንግተን ዲሲ አቅንቶ የነበረ ሲሆን ከአለም ባንክና የአሜሪካ መንግስት ባለስልጣናት ጋር ውይይት አድርጎ ነበር። በዚህ ውይይት ላይም የአለም ባንክ አፋጣኝ የ15 ቢልዮን ዶላር ብድር ለኢትዮጵያ እንዲያቀርብ ብድሩንም ቴሌንና አየር መንገድን በመሸጥ ከሚገኘው ገቢ ኢትዮጵያ መልሳ መክፈል እንደምትችል ቃል ገብቶ የኢትዮጵያ መንግስት ጥያቄ አቅርቧል።

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣው የኑሮ መወደድ የኮሮና ወረርሽኝ ካደድረሰው ጉዳት ጋር ተደምሮ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እያደረሰ ይገኛል። ይሁን እንጂ ከሁሉ የባሰው በትግራይ ክልል እየተካሄደ ያለው ጦርነት በርካታ የውጭ ባለሃብቶች ኢትዮጵያን እንዲሸሹና እንደ አውሮፓ ሕብረት ያሉ ሃያላን የእርዳታ ገንዘብ እንዲያቋርጡ ማድገደዱ እንዲሁም ከፍተኛ የሆነ የአገሪቱ አቅም በጦርነቱ ላይ ማተኮሩ ከፍተኛ የዶላር እጥረትን ከማስከተሉም ባለፈ ከነዳጅ እስከ ዳቦና መድሃኒት እጥረት በመላው ኢትዮጵያ እንዲከሰት አድርጓል።

 

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ የሸጠችው ቦንድ ዋጋው እያሽቆለቆለ ነው

21

ከውጭ ባለሃብቶች 1 ቢልዮን ዶላር ለመበደር በ2007 እ.ኢ.አ ኢትዮጵያ የሸጠችው ቦንድ በአየርላንድ የቦንድ ገበያ ላይ ባለሃብቶቹ እርስ በርስ የሚገበያዩበት ዋጋ ማሽቆልቆሉን ቀጥሏል። ከሶስት ሳምንታት በፊት በ101.53 ዶላር በመገበያያው ላይ ሲሸጥ የነበረው ይህ ቦንድ ላለፉት ሶስት ሳምንታት ዋጋው በተከታታይ እየወረደ ቆይቶ በዛሬው እለት በ94.41 ዶላር እየተሸጠ ይገኛል።

ይህ የዋጋ ማሽቆልቆል በትግራይ ክልል እየተደረገ ካለው ጦርነት ጋር የተያያዘ ነው ተብሎ የሚገመት ሲሆን ቦንዱ በእጃቸው ያለ የውጭ ባለሃብቶች ምን ያህል ጦርነቱ እንዳሳሰባቸውና ለሌሎች ገዢዎች አሳልፈው ለመሸጥ እየተሽቀዳደሙ እንደሆነ የሚያሳይ ነው። ጦርነቱ ከመከሰቱ በፊት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እጥረት የነበረባት ኢትዮጵያ በ2017 እ.ኢ.አ ሙሉ የ1 ቢልዮን ዶላሩን የዕዳ ክፍያ በአንድ ጊዜ ለምትፈፅምበት ቦንድ በየአመቱ 66.25 ሚልዮን ዶላር ወለድ ትከፍላለች። ታድያ የአገሪቱ ተቀማጭ የውጭ ምንዛሬ ባለፉት አመታት በእጅግ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ የቆየ በመሆኑ በጦርነቱ ምክንያት የሚከሰቱ የወጪ ንግድ መስተጓጎል፣ የውጭ ኢንቨስተሮች ወደኋላ ማለት፣ የመሳርያ ግዢ ወጪ መጨመርና እንዲሁም የፖለቲካ አለመረጋጋት ይህንን ተቀማጭ የውጭ ምንዛሬ መጠን ይባሱን ሊያመናምነው ይችላል የሚል ስጋት አለ።

የአንድ ቦንድ ዋጋ በድንገት እንዲያሽቆለቁል ከሚያደርጉት ምክንያቶች አንዱ ተበዳሪው ብድሩንም ሆነ ወለዱን የመክፈል አቅሙ ወደ ጥያቄ ምልክት በሚገባበት ወቅት ነው። በእርግጥ አሁን ላይ ወርዶ ያለው የቦንዱ ዋጋ ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ባይሆንም እያሽቆለቆለበት ያለው ፍጥነት በዚህ ከቀጠለ ጦርነቱ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እያሳደረ እንደሆነ የሚያመላክት ይሆናል።

ኤርትራ፤ ከተራራው ጀርባ ጠልቃ የቀረችው ሰሜናዊት ኮኮብ

0

 

ኤርትራ ከባህር በሯ በዘለለ፤ ምድሯ ጥቅም የለውም የሚለው አስተሳሰብ ከኢትዮጲያ ጋር ፍቺ ሳትፈጽም በፊት ገዢ ሃሳብ ሆኖ ነው የኖረው፡፡ በደርግ ጊዜ የኢትዮጲያ ፕሬዝዳንት የነበሩት ኮ/ል መንግሰቱ ሃይለማሪያም ከሻዕቢያ እና ህወሃት ወታደሮች ጋር ሲያደርጉት የነበረው የረዘመ ጦርነት አማሯቸው የተናገሩትም ይህ ገዢ አስተሳሰብ የነበረ ስለመሆኑ አንደኛው አመላካች ነው፡፡

ወርቅ አይወጣበት፤ ዳይመንድ አይታረስበት፤ ይሄ ፋንድያ የሆነ መሬት…

ብለው ነበር ፕሬዝዳንቱ በአስቂነታቸው ከሚታወቁት ንግግሮቻቸው መካከል በአንደኛው ላይ፡፡ ይህ ለዘለዐለም የተደረገ የሚመስለው የሻዕቢያ የትጥቅ ትግል፤ ኤርትራ ከአዲስ አበባ በሚሾሙ ሹማምነት መተዳደሯን በማስቀረት ለባላባቶች እና ለልጆቻቸው ብቻ የተወሰነውን ድሎት ለተራውም ዜጋ ማካፈል በሚል የተጀመረ ነበር፡፡ የሻቢያ ትግል ያስቀመጠውን እራስን በራስ የማስተዳደር እስከመገንጠል አላማ አሳክቶ፤ ኤርትራ ከኢትዮጲያ ተለይታ የራሷን ጎጆ ከመሰረተች ድፍን ሶስት አስርተ አመታትን ሊያስቆጥር ጥቂት ወራት ብቻ ይቀሩታል፡፡ እራስ በራስ ማስተዳደሩ የተሳካላቸው የኤርትራ ሹማምንት ብዙም ሳይቆዩ በቀድሞ የትግል አጋሮቻቸው ህውሃቶች፤ ከምትዘወረው ኢትዮጲያ ጋር በ1991 ዓ/ም እ.ኢ.አ. ደም ሊቃቡ ተቃጠሩ፡፡

በአዲስ አበባ ተወልዳ ያደገችውና ቤተሰቦቿ ከኤርትራ የሆኑት ሊዲያ ተክለማሪያም (ኢትዮኖሚክስ በግለሰቧ ጥያቄ መሰረት ለደህንነቷ ሲባል ስሟን ቀይሮታል) የጦርነቱ ማስጀመሪያ ነጋሪት የተጎሰመበትን ጊዜ የትላንትን ያክል ታስታውሰዋለች፡፡

በወቅቱ አዲስ አበባ ውስጥ አብዮት ፋና በሚባል ትምህርት ቤት የ8ኛ ክፍል ተማሪ ነበርኩኝ፡፡ የኢትዮጲያ መንግስት በየትምህር ቤቱ የሚገኙ አስተማሪዎችን ጦርነት ሊጀመር መሆኑን እና ጥፋቱም የኤርትራ መንግስት እንደሆነ አስረዱ እያለ ይልካቸው ነበር ይመስለኛል፡፡ የሂሳብና የህብረተሰብ አስተማሪዎቼ፤ አኔ ወደነበርኩበት ክፍል እየመጡ ገለጻ ያደርጉልን ነበር፡፡ በወቅቱ አይደለምና እኔ ላይ ችግር ያመጣል ብዬ ላስብ ይቅርና፤ ጦርነት እራሱ ምን ማለት እንደሆነ በቅጡ የምንገነዘብ አይመስለኝም፡፡

ትላለች ሊዲያ ከአሜሪካን አገር ኢትዮኖሚክስ በፌስቡክ ባናገራት ወቅት፡፡

ነገሩ ከረረ፤ የኢትዮጲያ መንግስትም አመረረ፡፡ ኢትዮጲያ ተቀምጣችሁ የኤርትራን መንግስት በገንዘብ የምትደግፉ ግለሰቦች ጓዜን ሳትሉ፤ ቤተሰባችሁን ጠቅልላችሁ ውጡልን አለ፡፡ ለሊዲያ እና ቤተሰቧ ጦርነቱ በራቸውን አንኳኳ፡፡

እኔ ህይወቴን በሙሉ ኤርትራዊ ነኝ የሚለው ስሜት ተሰምቶኝ እንደሚያውቅ አላስታውስም፡፡ ቤተሰቦቼም ሰለእንደዚህ አይነቱ ጉዳይ ሲወያዩም ትዝ አይለኝም፤ አይደለምና የኤርትራን መንግስት በገንዘብ ሊደግፉ ይቅርና፡፡ … የሆነው ሆኖ አንድ ቀን በጥዋት የመንግስት ወታደሮች መጥተው እኔን፤ ታናሽ ወንድሜን እና ሁለቱንም ወላጆቼ ለነገ ተዘጋጅተን እንድንጠብቅ ተነገረን፡፡ ታላቅ እህቴን ጎረቤት ደብቆ፤ ትተን የሄድነውን ቤታችንን እንድታስተዳድር በሚል አስቀሯት፡፡ 

ሊዲያ ታሪኳን ለማካፈል የምትሳሳ አትመስልም፡፡ ትቀጥላለች፡-

በንጋታው ጸሃይ ሳትወጣ መኪና ላይ ተጫንን፡፡ የስምንተኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተናን ሳልፈተን ነበር አስመራ የሄድኩት፡፡ የትምህርቱ ነገር በዛው አከተመለት፡፡ ኤርትራ ሲዖል ሆነችብኝ፡፡ ከመጀመሪያ ደረጃ በላይ ትምህርት መቀጠል የቅንጦት ነው ተባለ፡፡ ከአገር መውጣት የመጀመሪያው ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ሆነ፡፡ 

ትላለች ሊዲያ፡፡

በወቅቱ የኤርትራውያን ከኢትዮጲያ መውጣት በአዲስ አበባ ኢኮኖሚዊ እንቅስቃሴ ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ ግልጽ ብሎ ይታይም ነበር፡፡ ኤርትራውያን በወቅቱ በዋናነት የመኪና ጥገናና መለዋወጫ ንግድ ውስጥ ዋና ተዋናይ እንደነበሩ ይታወሳል፡፡ መልቀቃቸውን ተከትሎ ጋራዦች፤ የመኪና መለዋወጫ ሱቆች እና መሰል እንቅስቃሴዎች ተቀዛቅዘው ቆይተው ነበር፡፡ ጦርነቱ የአዲስ አበባን ኢኮኖሚ ለተወሰነ ጊዜ ቢያቀዘቅዝም፤ የኤርትራን መላው ኢኮኖሚ ደግሞ አግቶት ነው የኖረው፡፡

የግጭቱ ምክኒያት በሁለቱ አገራት መንግስታት መሪዎች ፖለቲካዊ ነው የሚል ሙግት ቢቀርብበትም፤ አብዛኛው ምክኒያት ኢኮኖሚያዊ እንደሆነ የሚሞግቱ ጸሃፍት አሉ፡፡ ማር ማይክልሰን በተባለ አጥኚ በ1998 እ.ኤ.አ. የቀረበ አንድ ጥናት የግጭቱን ኢኮኖሚያዊ ምክኒያቶች ይዳስሳል፡፡ ከኤርትራ ጎጆ መውጣትም በኋላ፤ ሁለቱ አገራት በጋራ አኮኖሚያዊ ስምምነት የሚመራ የኢኮኖሚ ስርዐት መገንባት ችለው ነበር፡፡ ስምምነቱ  ኢትዮጲያ የአሰብ እና የምፅዋን የባህር በሮች እንድትጠቀም እና ኤርትራም የኢትዮጲያን የገንዘብ ኖት እንድትጠቀም የፈቀደም ነበር፡፡

ስምምነቱ ወደመሬት ወርዶ ከተተገበረ ጥቂት አመታት በኋላ፤ ከግጭቱ መቀስቀስ ቀደም ብሎ፤ የኢኮኖሚ ስምምነቱ የጋራ ጥቅምን መሰረት ያደረገ አልነበረም የሚሉ ወቀሳዎች ይቀርቡበት ጀመር፡፡ ብር ኢትዮጲያ ውስጥም ኤርትራ ውስጥም ዋጋው እኩል መሆን አለበት ተብሎ ቀድሞ የተወሰነው የምንዛሬ ህግ፤ ኢትዮጲያ የኤርትራ ኢኮኖሚ ላይ ምንም ቁጥጥር ስለሌለኝ ይጎዳኛል በሚል ማጉረምረም ጀመረች፡፡ ኢትዮጲያ ውስጥ የሚኖሩ ኤርትራውያን፤ ቡና እና ወርቅን የመሳሰሉ ምርቶችን እንደዜጋ በርካሽ እየገዙ እና ወደ ኤርትራ እየላኩ ኤርትራ እንደ አገር ለውጪ ንግድ እያዋለችው ነው፤ ይህም አኔ ለውጪ ንግድ ማዋል ያለብኝን ምርት እያሳጣኝ ነው፤ ከዚያም አልፎ የኢትዮጲያ መገለጫ የሆነው ቡና በአለም አቀፍ ገበያ ላይ የኤርትራ መገለጫ ሆኗል የሚሉ ክሶች ይቀርቡ ጀመር፡፡

መሰረታዊ ምክኒያቱን እነዚህ እና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ ምክኒያቶች ያደረገው አለመግባባት፤ በድንበር መወረር ቀስቃሽነት ወደጦርነት አመራ፡፡ ጦርነቱ ሁለት አመታትን እና ከ60 ሺህ በላይ ዜጎችን ቀጥፎ፤ በአልጄሪያ አደራዳሪነት ተጠናቀቀ፡፡ የአለም መገናኛ ብዙሃን ሁለት መላጦች በማበጠሪያ የተጣሉበት ብለው የተሳለቁበት ጦርነት ከተጠናቀቀም በኋላ፤ ለኤርትራ- ጎጆ መውጣት እራስን ወደ መቻል ሳይቀየር ቆየ፡፡

ከጦርነቱ መጠናቀቅም በኋላ ኢትዮጲያ ያልታመነች ማን ይታመናል ያሉ የሚመስሉት የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ፤ የአሜሪካን እና የአውሮፓ አገራትን ጨምሮ ሌሎችም ኤምባሲዎችን ዘግተው አስመራን እንዲለቁ አዘዙ፡፡ ኢትዮጲያን ማስቀየም ያልፈልጉት የአለም አገራት፤ ኤርትራ የመሳሪያ ግዢን እንዳትፈጽም ማዕቀብ ጣሉ፡፡ በግላጭም ባይሆን የኤምባሲዎቻቸው መዘጋት ያንገበገባቸው ሃያላን፤ ከኤርትራ ጋር መነገድ ነውር እንዲሆን፤ የባለስልጣናቶቿ የባንክ አካውንት እንዳይንቀሳቀስ፤ የአለም አቀፍ በረራንም እንዳያደርጉ በሚሉ እርምጃዎች ብስጭታቸውን ገለጹ፡፡

መገንጠል፤ ራስን ለመቻልና ለኢኮኖሚ ፍትሃዊነት በር ከፋች ነው የሚል ቃል የተገባላቸው ዜጎች፤ ቃል የተገባው ሳይሆን ቢቀር፤ የቻሉት በአየር፤ ያልቻሉት በባህር መሰደዱን ተያያዙት፡፡ ህይወታቸው ሳያልፍ አውሮፓ፤ አሜሪካን አሊያም እስራኤል የደረሱትም፤ ተሳክቶላቸዋል ለማለት በማያስደፍር ደረጃ የአለም አቀፍ መገናኛ ብዙኋን የሰቆቃ ታሪክ ምሳሌ ሲደረጉ ኖሩ፡፡ ሊዲያ ምንም እንኳን የውትድርና ስልጠናውን ፤ የባህር ስደቱን ብታመልጥም አሜሪካን ያን ያክል አስደሳች እንዳልሆነችላት ትመሰክራለች፡፡

በአባቷ በኩል በተገኘ በአሜሪካን አገር ኑሮውን ያደረገ እና በሁለት እጥፍ በእድሜ ለሚበልጣት ሰው አስመራ ላይ ተዳረች፡፡ ሊዲያም ወደ አሜሪካን አገር በረረች፡፡ አሜሪካም እንኳን መጣሽልኝ እንዳላለቻት ሊዲያ ለኢትዮኖሚክስ ታብራራለች፡፡

ወጣት ነህ ተብሎ ስለሚታሰብ ወንዶች እንድትማር፤ ስራ እንድትሰራ አይፈቅዱልህም፡፡ ዝም ብሎ ልጅ መውለድ፤ ልጅ ማሳደግ፡፡ አራት ልጆች ወልጄ እነሱን ሳሳድግ ነው የኖርኩት፡፡ መማር፤ ስራ መስራት፤ እራስን መቻል የነበረኝ ህልም ሁሉ ቅዠት ሆኖ ቀረ፡፡

የማር ማይክልሰን ጥናት እንደሚያሳየው፤ ኤርትራ ከመገንጠልም በኋላ የራሷን የኢኮኖሚ አቅም አስጠንታ ወደጥቅም ከመቀየር ይልቅ በቀጥታም በተዘዋዋሪም በኢትዮጲያ ኢኮኖሚ ላይ ጥገኝነት የተጠናወተው ነበር፡፡

ኤርትራ ከስደት የተረፉ ልጆቿን እንዴት ስታስተዳድር ከረመች?

ዊኪሊክስ የተባለው ሚስጥራዊ መረጃዎችን የሚያትመው ድህረ ገጽ በመጋቢት 2007 እ.ኤ.አ. በወቅቱ በኤርትራ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት ሮናልድ ማክሚዩለን ለዋሽንግተን የጻፉትን ደብዳቤ አውጥቶ ነበር፡፡ ማክሚዩለን በደብዳቤያቸው፤ በወቅቱ የኤርትራ የውጪ ንግድ የሚመጣላት የውጪ ምንዛሬ ከ20 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደማይዘል ይገልጻሉ፡፡ አምባሳደሩ ቀጥለውም፤ ከኤርትራ ውጪ የሚገኙ ኤርትራውያን ከሚያገኙት ገቢ ሁለት በመቶ ግብር ለመንግስት አንዲከፍሉ የማስገደድ እቅድም እንዳለ ያነሳሉ፡፡ በኤርትራ ኤምባሲዎች እና በሌሎች መንገዶች የሚሰበሰበው ይህ ግብር እና እርዳታ 80 ሺህ ከሚሆኑ ኤርትራውያን ወደ 35 ሚሊዮን ዶላር እያስገኘላቸው ሳይሆን እንዳልቀረ ግምታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡

አምባሳደሩ በተመሳሳይ አመት በጻፉት ደብዳቢያቸው ላይ ደግሞ ኤርትራ ከኳታር፤ ሳውዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤመሬቶች የገንዘብ ድጋፍ ሳያገኙ እንዳልቀሩ ይገምታሉ፡፡ ኢሳያስ ከኳታር በሚላክላቸው አውሮፕላን፤ ኳታር እንደሚመላለሱና ኢሳያስን መደገፍ ክርስቲያናዊት ኢትዮጲያን መጫን ከመሰላቸው አሚሮች ዶላር እንደሚሸጎጥላቸው ያነሳሉ፡፡ ያም ሆኖ በወቅቱ የአገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ክምችት ምናልባትም ከሁለት እና ሶስት ሳምንት ገቢን ከመሸፈን ሊያልፍ የሚችል እንዳልነበር ይገምታሉ፡፡

ማክሚዩለን በ2009 እ.ኤ.አ. ደብዳቢያቸው ደግሞ የኤርትራ ኢኮኖሚ አውራ የነበሩትን ሃጎስ ገ/ሂዎትን ኮሚዩኒስት እንደሆኑ እንደጠይቅዋቸው እና “አይደለሁም፤ ከጦርነቱ በፊት የአገሪቱን የግል ዘርፍ ለማሳደግ እቅድ የነበረ ቢሆንም፤ ከጦርነቱ በኋላ ግን፤ የአገር ደህንነትና ጸጥታ ዋንኛው አላማ” እንደተደረገ ነግረውኛል ብለው እንደጻፉ ዊኪሊክስ ያስነብባል፡፡ አምባሳደሩ በኢሜይላቸው በ2010 እ.ኤ.አ. የወርቅ ምርት በመጀመር የአገሪቱንም የስርዐቱንም ህልውና ከአደጋ ለመጠበቅ የታሰበ ቢሆንም፤ ከዚህ ምርት ግን ከ2013 እ.ኤ.አ. በፊት ገቢ ሊገኝ እንደማይችል፤ የኤርትራንም ኢኮኖሚ ከውድቀት ሊታደግ የሚችል አፋጣኝ መፍትሄ ይኖራል ብለው እንደማይገምቱ ይገልጻሉ፡፡

በ2014 እ.ኤ.አ. በኖርዌይ ኦስሎ ዩኒቨርስቲ ለህግ ፋካልቲ የቀረበ አንድ ጥናት ኤርትራ ዜጎቿን ለማስተዳደር ስታደርግ ስለቆየችው ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የተወሰኑትን ያነሳል፡፡ ከነዚህ እንቅስቃሴዎች መካከል የተቀናጀ የውጪ ንግድ ማሳለጫ ወደብ አገልግሎት፤ የቅጠላ ቅጠል እና ፍራፍሬ ምርት፤ እንዲሁም በበግ፤ ፍየል፤ ግመል፤ አህያ፤ ፈረስ አና የመሳሰሉት የቁም ከብቶች እርባታም ቀና ደፋ እያለች የዜጎቿን ህይወት ለማቆየት ስትውተረተር እንደከረመች ያሳያል፡፡ ኤርትራን ከ1300 ኪሎ ሜትር በላይ በሆነ ርዝመት እየታከከ በሚያልፈው የቀይባህር ውስጥ ከ1000 በላይ ዝርያ ያላቸውን የአሳ ምርት ለጥቅም ሲያውሉም እንደነበር ይገልጻል፡፡

በባለፉት ስድስት አመታት ኤርትራን ለማሰስ ድፍረቱን ያገኙ የከርሰ ምድር ጥናት ተመራማሪዎች እንደሚሉት ከሆነ ደግሞ ኤርትራ የማዕድን ሃብቷም ገና ጫፉ አልተነካም፡፡ የአገሪቱ የወርቅ፤ ብር፤ መዳብ፤ ዚንክ፤ ብረት፤ ፖታሽ፤ እና ሌሎች መዐድናት የአለም ኢንቨስተሮችን ቀልብ መማረክ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ ከነዚህ ኢንቨስተሮች አንዱ በካናዳው ነቭሰን እና በኤርትራ መንግስት የጋራ ድርሻ ባለቤትነት የተመሰረተው ቢሻ የመዐድን ምርት ድርጅት ነው፡፡

የኤርትራ መንግስት 40 በመቶ አንዲሁም ነቭሰን 60 በመቶ በሆነ የድርሻ ባለቤትነት በ2008 እ.ኤ.አ. የተከፈተው ማምረቻ በ2011 እ.ኤ.አ. ስራውን ጀምሯል፡፡ እንደጅማሮ ትንሽ ዋጋ ያላቸውን የወርቅ እና የብር መዐድናትን በማምረት  የጀመረ ሲሆን፤ በ2013 እ.ኤ.አ.  ደግሞ ዋጋቸው ትንሽ፤ ጥራታቸው ግን ከፍተኛ የሆኑ መዳቦችን ወደማምረት እንደተሸጋገረ የኦስሎ ዩኒቨርስቲው ጥናት ያሳያል፡፡ የኤርትራን የመዐድን ምርት ወደጥቅም ለመቀየር፤ መንግስቷ ኢንቨስተሮችን ሲያሳድድ፤ ኮንትራቶችን ሲፈርም ነው የከረመው፡፡

የዛራ እና ድብርባ የወርቅ ማምረት እንቅስቃሴዎች ውጤታማ ቢሆኑ ለኤርትራ በየአመቱ በመቶ ቢሊዮን ዶላሮች ያሳፍሳሉ ተብለውም ታቅደው ነበር፡፡ በዳናክል ረባዳማ ስፍራ ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው የፖታሽ ምርት ደግሞ፤ ለ200 አመታት የሊዝ ኪራይ ስምምነት የተፈረመበት ቢሆንም ለአገሪቱ ምንም ጠብ ሳያረግ ነው የኖረው፡፡ የዚህ ምክኒያቱ ደግሞ የምርት አንቅስቃሴዎችን በገንዘብ ለመደገፍ ፍቃደኛ የሆኑ አለም አቀፍ ኢንቨስተሮች ፍላጎት ማጣት ነው፡፡ ከመንግስት ጋር ውል የሚፈራረሙ ኮርፖሬሽኖች የፕሮጀክቶቹ አትራፊነት ምንም ያክል አሳማኝ ቢሆን የኤርትራ ፖለቲካዊ ሁኔታ መተማመንን ሳይፈጥር በመኖሩ ዜጎቿ ላም አለኝ በሰማይ ሲሉ ኖረዋል፡፡ ይህንን ሰንኮፋ ለመንቀል ተስፋ የተጣለበት ክስተት በ2018 እ.ኤ.አ. ተስምቷል፡፡

ከነዚህ እና ከሌሎች እንቅስቃሴዎች ኤርትራ በ2014 እ.ኤ.አ. ከ400 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንዳገኘች አምባሳደሩ የአለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅትን ጥቅሰው ያስቀምጣሉ፡፡ ሆኖም የአገሪቱ ከጠቅላላ ምርቷ ጋር ሲነጻጸር የነበረባት የበጀት እጥረት ከ20 በመቶ በላይ እንደሚሆን ግምታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡ አንደኛው ምክኒያት ደግሞ ከራሽያ እና ከዩክሬን የሚገዟቸው ውድ የጦር መሳሪያዎች ነበሩ፡፡ አምባሳደሩ ከራሺያው አቻቸው ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ የኤርትራ መንግስት 50 ሚሊዮን ዶላር ግምት ያለው መሳሪያ ከአገራቸው እንደገዛ ነግረውኝ ነበር ይላሉ፡፡ እንዲያ ከሆነ ደግሞ ኢሳያስ በውጭ ከሚገኙ ዜጎች በግብር መልክ የሚሰበስቡትን ገንዘብ መሳሪያ ላይ እንዳዋሉት ማሳያ ነው- እንደ ማክሚዪለን፡፡

ከተራሮቹ ጀርባ ብቅ ያለው የኢኮኖሚ ተስፋ ደምቆ ይወጣ ይሆን?

ወደነበረበት መመለስ የቻለውን የኢትዮጲያና ኤርትራ ግንኙነትን ተከትሎ፤ ኢትዮጲያ የተባበሩት መንግስታት ጊዜያዊ ሊቀመንበርነቷን ተጠቅማ አስፈጽማዋለች የተባለውና፤ ኤርትራን የማግለል ውሳኔ እንዲቀየር ሲደረግ የነበረው ጫና ተሳካ፡፡ የአገሪቱ ባልስልጣናት ከአገር ውጪ እንዲንሸራሸሩ፤ አገሪቱም የመሳሪያ ግዢን ባሻት ጊዜ እንደትፈጽም ተፈቅዷል ተባለ፡፡ የሁለቱ አገራት ዳግሞ ግንኙነት፤ ምንም እንኳን መርህ ላይ የተመሰረተ አይደለም፤ የህግ ማዕቀፍም ያጥረዋል ተብሎ ቢታማም፤ ለአብይ አህመድ የሰላም ኖቤል ሽልማትን ይዞ ከመምጣት ግን አላገደውም፡፡ በፊት በኤርትራ ለሚደረጉ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ገንዘባቸውን ለሰሰቱት የአለም አቀፍ ባንኮችና ኢንቨስተሮች አዲስ ተስፋን በጆሯቸው ሹክ ያለ መሰለ፡፡

መቀመጫውን ኒው ዮርክ ያደረገውና አለም አቀፍ የንግድና ኢንቨስትመንት መረጃዎችን የሚያዘዋውረው ብሉምበርግ፤ የመጀመሪያውን የውጪ ኢንቨስትመንት ተስፋ ይዞ ብቅ አለ፡፡ ብሉምበርግ በነሃሴ 2019 እ.ኤ.አ. ባወጣው ዘገባ፤ የአፍሪካ የፋይናንስ ትብብር እና የአፍሪካ የወጪ-ገቢ ንግድ ባንክ ተቋማት፤ መቀመጫውን አውስትራሊያ ላደረገው ደናካሊ የማዕድን ማምረቻ ድርጅት ኤርትራ ውስጥ ለሚያከናውነውና በ2014 እ.ኤ.አ. የ200 አመት የሊዝ ኪራይ ስምምነት ለተፈራረመበት የፖታሽ ማምረቻ ፕሮጀክት፤ የ200 ሚሊዮን ዶላር ብድር ማጽደቃቸውን አበሰረ፡፡

በኤርትራ ብሔራዊ የመዐድን ማምረቻ እና በደናካሊ እያንዳንዳቸው 50 በመቶ ድርሻ ኖሯቸው ያንቀሳቅሱታል የተባለውና በዳናክል ረባዳማ ስፍራ ለሚካሄደው የፖታሽ ምርት ፕሮጀክት ዋና ስራ አስፈጻሚ ደስታቸውን ገልጸው፤ ብድሩ ለማምረቻ ፋብሪካ ግንባታውና ለምርት እንቅስቃሴው ከሚያስፈልገው የገንዘብ ፍጆታ አብዛኛውን ይሸፍናል አሉ፡፡ ፕሮጀክቱ በህጋዊ ድህረገጹ፤ የዳናክል ፕረጀክት በአለም ግምባር ቀደሙ ጥራት ያለው የፖታሽ ማዕድንን በርካሽ ዋጋ የሚያቀርብ እንደሚሆን ገለጸ፡፡

ማምረቻው ስራ ሲጀምር በሁለት ዙር የፖታሽ ምርትን ለገበያ የሚያቀርብ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ በመጀመሪያዎቹ አምስት አመታት 472ሺህ ቶን፤ ከስድስተኛው አመት በኋላ ደግሞ 944 ሺህ ቶን የፖታሽ ምርትን ለገበያ እንደሚያቀርብ እቅድ ተይዟል፡፡ ከውትድርና ሌላ ቅጥር ለማያውቁት ኤርትራውያን፤ ከ450 በላይ ቀጥተኛ የሆነ የስራ እድልን ይፈጥራልም ተብሏል፡፡ ፕሮጀክቱን ለማቀላጠፍ ከሚገነቡ መሰረተ ልማቶች እና ከፕሮጀክቱ ጋር በተያያዘ ከሚጀመሩ የንግድ እንቅስቃሴዎች በ10ሺዎች ይጠቀማሉ የሚል ተስፋን ሰንቋል፡፡

ኤርትራ ፕሮጀክቱ ለስኬት ከበቃ እንደ አገር በአመት ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ በግብር መልክ እሰበስባለው ብላ ተስፋ ሰንቃለች፡፡ በአመት ከ10 ሚሊዮን ዶላር በላይ ደግሞ በወርሃዊ ደሞዝ መልክ ለዜጎቿ ይከፈላቸዋልም ተብሏል፡፡ ይህን ተከትሎም በአካባቢው የሚገኙ ኤርትራውያን ንጹህ ገቢ ከ20 እጥፍ በላይ ይጨምራልም እየተባለ ይገኛል፡፡ የማህበራዊ ግዴታን ለመወጣት የሚደረጉ ኢንቨስትመንቶችም- ኤርትራ ከተራሮቿ ጀርባ ከባህር በሮቿ በዘለለ ያላትን ኢኮኖሚያዊ አቅም፤ በተስፋ መልክ በጨረፍታ እንድታሳይ ሊረዳት የሚችል ይመስላል፡፡

በኤርትራ የፖታሽ ማዕድን ለማውጣት እየሰራ ያለው ደናካሊ ኩባንያ ከሁለት አመት በፊት በለንደን የአክስዮን ገበያን ሲቀላቀል

ከምድሯ በላይ የቀይ ባህርን፤ ከምድሯ በታች ዝቀው የማይጨርሱት መዐድኖቿን ተሸክማ፤ ዜጎቿን ለውትድርና፤ አለፍ ሲልም ለስደት መገበሩን ይብቃ ለማለት ጊዜው አሁን ይመስላል፡፡ ከማህጸኗ ተፈጥረው ከገጸ በረከቷ ሊቃመሱ ይቅርና የእናትነት ጣዕሟንም ሳያዩ ለተሰደዱ ልጆቿ፤ ምቹ አገር መፍጠርን ሹማምንቶቿ ተቀዳሚ አላማቸው ሊያርጉት ጊዜው አሁን ይመስላል፡፡

ልጆች ከፈለጉ ከአባታቸው ጋር እዚሁ ይቀመጡ፡፡ እኔ ቢሆንልኝ አስመራ ተመልሼ አንድ ንግድ ጀምሬ፤ ትንሽ ከፍ ካለ ደግሞ አዲስ አበባም ሌላ ከፍቼ እዚህና አዚያ እየተመላለስኩ መኖር ነው የምፈልገው፡፡

ትላለች ሊዲያ ቢሆንልሽ ብለሽ የምትመኚው ብሎ ኢትዮኖሚክስ ላቀረበላት ጥያቄ፡፡

ለእራሷ እና ለዜጎቿ ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካ የኢንቨስትመንት ፍሰት መግቢያ በር መሆን የምትችልን አገር መገንባት፤ ከኢሳያስ ፖለቲካዊ ፍላጎት በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል፡፡ የኤርትራን የኢኮኖሚ ተስፋ እንደተራሮቿ አግዝፎ መገንባት፤ እራሳቸውን እንዲፈትኑ የቀረበላቸው አዲሱ ግብግብ መሆኑን መረዳት፤ አገራቸውን እንደ አንድ ሰሞኑ ቅጽል ሰሟ ሰሜናዊት ኮከብ እንድትሆን ለማስቻል የመጀመሪያ እርምጃ ሊሆን ይችላል፡፡ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ራስን ለማስተዳደር የጀመሩት ትግል፤ እርሳቸውን ፕሬዝዳንት ከማረግ በዘለለ፤ እራስን ወደ መቻል እንዲሸጋገር ትግሉን የማስጀመሪያ ጊዜው አሁን ነው ቢባል ከእውነት የራቀ አይሆንም፡፡

ኢኮኖሚያዊ ህልሙ በፖለቲካ ይጨናገፍ ይሆን?

0

 

በ2013 እ.ኤ.አ. የአዲስ አበባ መስፋፋት የኦሮሚያ ገበሪዎችን አፈናቅሏል በሚል የተጀመረው የጸጥታ አለመረጋጋት ሰባት አመታትን አስቆጥሯል፡፡ ይህ አመጽ አሁን ያሉትን ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ ስልጣን አምጥቶ የተለያዩ ለውጦችን ቢያስመዘግብም፤ አሁንም ስሙን፤ አካባቢውን እና ምዕራፉን እየቀያየረ ቀጥሏል፡፡ የዳር አገርን ሲለበልብ የከረመው የጸጥታ ችግር የመሃሉን ህዝብ አንዴ ተስፋ እየሰጠ ሌላ ጊዜ ተስፋን እያሳጣ መረጋጋት እንደተሳነው ከርሟል፡፡

ራሄል ጌትነት ከጥቂት ሳምንታት በፊት ህይወቷ አሁን ባለው መልኩ ይቀየራል ብላ አልገመተችም ነበር፡፡ ራሄል የዩኒቨርስቲ ትምህርቷ ሳይሳካ በመቅረቱ ወደትውልድ ከተማዋ አዲስ አበባ በመመለስ አንዲት ኪዮስክ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ከፍታ የውበት መጠበቂያ ቁሳቁሶችን በመሸጥ መተዳደር ከጀመረች ውላ አድራለች፡፡ በዚህ ስራዋ ላይ ከተዋወቀችውና ከሁለት አመታት በላይ እጮኛዋ ከነበረው ፍቅረኛዋ ጋር አብረው ሲኖሩ የነበረ ቢሆንም እንዳቅማቸው ትንሽ የምሳ ፕሮግራም በማዘጋጀት ቤተሰቦቻቸውን ለማስተዋወቅ ለህዳር አጋማሽ ቀጠሮም ተይዞ ነበር፡፡

እድሜዬን ሙሉ እናቴን ከስልክ እና ከአሸንዳ በዐል ውጪ አይቻትም አናግሪያትም አላውቅም ትላለች፡፡ አሸንዳም ከቅርብ አመታት ወዲህ ነው መሄድ የጀመርኩት፡፡ ለረጅም ጊዜ ስለእናቴ የነበረኝ ትውስታ በጣም ውስን ሆኖ ነበር የኖርኩት፡፡

ትላለች ኢትዮኖሚክስ በፌስቡክ ባደረገላት ቃለመጠይቅ፡፡

ራሄል ትግራይ የምትገኝ እናቷን ወደ አዲስ አበባ መጥታ የቤተሰብ ትውውቅ ምሳ ለማረግ የነበራት እቅድ መልሳ እንድታስብበት ያደረጋትን መርዶ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጥቅምት 24/ 2013 ዓ/ም ይዘው ብቅ አሉ፡፡ ጠቅላዩ መቀሌ በሚገኘው የመከላከያ ሰሜን እዝ ላይ የትግራይ ክልልን የሚያስተዳድረው ህወሃት ጥቃት ማድረሱን እና እሳቸውም በአጸፋው መከላከያ ምላሽ እንዲሰጥ ማዘዛቸውን ለኢትዮጲያውያን አረዱ፡፡

አሁን አይደለምና የቤተሰብ ትውውቅ እናቴ እራሷ በህይወት መኖሯን እና አለመኖሯን አላውቅም፡፡ እኔ መሄድ አልችል፤ እሷ መምጣት አትችል፡፡ ድምጽዋን እንኳን መስማት አልቻልኩም፡፡

ትላለች ራሄል፤ በፌደራል መንግስትና በህወሃት መካከል በዝግ እየተካሄደ ባለው ወታደራዊ ግብግብ ሁሉም የመገናኛ ዘዴዎች የተቋረጡ በመሆኑ የፌደራል መንግስቱን እያማረረች፡፡ ለራሄል ምሬት የሆነው ዜና ለሌሎች ደግሞ ህግን የማስከበር እርምጃ ሆኗል፡፡ ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ በማህበራዊ ድህረ ገጹ የፌደራል መንግስት እርምጃውን በመውሰዱ ሳይሆን እስካሁን ሳይወስድ በመዘግየቱ ሊጠየቅ ይገባል የሚል እንድምታ ያለው ጽሁፍ አሰራጭቷል፡፡ ይህ ስሜት ለኮሌጅ የቋንቋ መምህር ለሆነው አክሊሉ በቀለም ተመሳሳይ ነው፡፡

ለ27 አመታት ሲደረግ የነበረውን እስር፤ ከአገር ማባረር፤ ግድያ እና ተቋማትን በጥቂት ግለሰቦች ስር መቆጣጠር እና ዝርፊያ ሁሉ ይቅር በሉ ተብለን ይቅር ብለናል፡፡ የመከላከያ ልጆቻችንን በተኙበት ማጥቃት ግን የለየለት አሸባሪነት ነው፡፡

ይላል አክሊሉ ከኢትዮኖሚክስ ጋር ባደረገው አጭር ውይይት፡፡

ክስተቱ በዜጎች እና በአገር ላይ ስለሚኖረው አሉታዊ ተጽዕኖ ግን ተናጋሪ አያሻም፡፡ ለጊዜው የአለም አቀፉን ማህበረሰብ ያሳሰበው ክስተቱ በአካባቢው ላይ የሚኖረው የጸጥታ ተጽዕኖ ነው የሚመስለው፡፡ ከእንግሊዝ፤ ጀርመንና አሜሪካ፤ ከአውሮፓ ህብረት እስከ አፍሪካ ህብረት ግብግቡ በፍጥነት ቆሞ ወደ ድርድር እንዲኬድ ሲማጸኑ ቆይተዋል፡፡ እንደነዚህ አካላት እይታ ዋናው አደጋ የምስራቅ አፍሪካ ጸጥታ ነው፡፡ ጠቅላዩ ክስተቱ ምስራቅ አፍሪካን አያሰጋም፤ ዘመቻው ውስን፤ የተመጠነና በአጭር ጊዜ የሚጠናቀቅ ነው ሲሉ የአለም አቀፉ ማህበረሰብን ሙግት ጆሮ ዳባ ልበስ ያሉት ይመስላሉ፡፡

ጦርነትም ይሁን ህግን የማስከበር እርምጃ፤ በክስተቱ ምክኒያት የታገተው የዜጎች ህልም ብቻ አይደለም፡፡ በትግራይ እና በፉደራል መንግስቱ መካከል በተጀመረው ወታደራዊ ግብግብ ከሌሎች የጸጥታ ሰንኮፋዎች ጋር ተደምረው የጠቅላይ ሚኒሰትሩን መንግስት ኢኮኖሚያዊ ህልም በአጭር እንዳያስቀረውም ያሰጋል፡፡

የኢትዮጲያ መጻይ ኢኮኖሚ ጠቅላዩ እንዳለሙት

ምንም አንኳን የአገሪቱ ፖለቲከኞች ፊት ለፊት በሚታየው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ተጠምደው እምብዛም ሲከራከሩበት ባይታዩም፤ ጠቅላዩ በቀጣይ አገሪቱን ሊወስዱበት ስላሰቡበት መንገድ ፍንጭ ሰጭ የሚሆኑ ውሳኔዎችን ሲያሳልፉ ቆይተዋል፡፡ መንበራቸውን በያዙ ገና በማለዳው የኢትዮጲያ አየር መንገድ ድርጅት ካለበት የእዳ ጫና አኳያ መሸጡ ያዋጣል ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ይሄኛው ሃሳብ የኢትዮጲያ አየር መንገድ ከአየር መንገድነቱ የዘለለ ዋጋ በኢትዮጲያውያን ዘንድ ስላለው በተነሳባቸው ተቃውሞ ወደኋላ ቢያፈገፍጉም የአለም ገበያው ውስጥ ዘው ብለው መግባት ስለመፈለጋቸው ግን ሌሎች ማስረጃዎችን ማግኘት ይቻላል፡፡

ከነዚህ ፍንጮች አንዱ የኢትዮ ቴሌኮምን 40 በመቶ ድርሻ ለአገር ውስጥ እና ለውጭ ባለሃብቶች ለመሸጥ የተወሰነው ውሳኔ ነው፡፡ ምንም እንኳን እንደ የኢትዮጲያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)፣ ህወሃትና ኦፌኮ ባሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከተሰነዘረው ወቀሳ የመሸጫ ጊዜውን ቢያራዝሙትም፤ የሽያጩ ጉዳይ ግን ያለቀለት እና በ2013 እ.ኢ.አ. እንዲጠናቀቅ አቅጣጫ የተቀመጠለት ነው፡፡ ጠቅላዩ በመጡ ሰሞን የልማት ባንክ የብድር ገንዘብን የግለሰቦች መጫወቻ በመሆናቸው ውጤታማ ሊሆኑ አልቻሉም የተባሉት የስኳር ፋብሪካዎችም ለሽያጭ ዝግጁ ሆነዋል፡፡

የአክሲዮን ድርሻ ሽያጭ ገበያ ለማስጀመር ያለመው የማዕከል ግንባታም እንደተጀመረ የብሔራዊ ባንክ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ከጥቂት ጊዜ ወዲህም የውጪ ምንዛሬ በገበያው እንዲወሰን፤ በእስልምና ህግ መሰረት ወለድ የለሽ ወይም ሀላል ባንኮች እንዲቋቋሙ፤ ጥቃቅን እና አነስተኛ የብድር ተቋማት ወደ ባንክነት እንዲያድጉ፤ የዳያስፖራው ማህበረሰብ በውጪ ምንዛሬ አካውንት መክፈት እንዲችል እና በፋይናንስ ዘርፉም በኢንቨስተርነት በቀጥታ መሳተፍ እንዲችል የሚፈቅዱ የህግ ማሻሻያዎች ተደርገዋል ወይም ለመተግበር በሂደት ላይ ይገኛሉ፡፡ አነዚህ ማሻሻያዎች ጠቅላዩ እና አማካሪዎቻቸው መንግስት በኢኮኖሚው ውስጥ ያለው አድራጊ ፈጣሪነት እየቀነሰ፤ ኢኮኖሚውም በአገር ውስጥ አና ከአገር ውጪ ባለው ገበያ እጣ ፋንታው እንዲወሰን መፈለጋቸውን አመላካቾች ናቸው፡፡

የኢትዮጲያ ኢኮኖሚ በገበያ መር ስርዐት- በጨረፍታ 

የኢትዮጲያ መንግስት በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በ2014 እ.ኤ.አ. ለአለም ገበያ ያቀረበው የቦንድ ሰነድ ለ10 አመት ቆይቶ በ2024 እ.ኤ.አ. ይጠናቀቃል ተብሎ የታቀደ ነው፡፡ የሰነዱ ሽያጭ መንግስት የአንድ ቢሊዮን ዶላር ብድር ያስገኝልኛል ብሎ ያቀደበትም ነበር፡፡ ኢትዮጲያ በቦንድ ሰነድ የሚገኝ ብድር በአገር ውስጥ በፌደራል እና በክልል ደረጃ ተጠቃሚ ብትሆንም በአለም አቀፍ ደረጃ ግን እንዲህ አይነቱ ይህ ነው የሚባል ብድር የለባቸውም ከሚባሉ የአፍሪካ አገራት መካከል አንዷ ናት ይላል ሴፍየስ የተባለ የጥናትና ትንተና ተቋም ስለቦንዱ በ2019 እ.ኤ.አ. ባቀረበው ትንተና ላይ፡፡

አገራት የተለያዩ የኢንቨስትመንት ፍላጎቶቻቸውን ለማሟላት የሚያስችል የብድር አቅርቦትን ለማግኘት በአለም አቀፍ ገበያ ላይ የሚሸጡ የቦንድ ሰነድ ያቀርባሉ፡፡ እነዚህ ሰነዶች መንግስታት ለትላልቅ ፕሮጀክቶቻቸው የገንዘብ አቅርቦት በብድር መልክ ለማግኘት ለገበያ የሚያቀርቧቸው ናቸው፡፡ በቀላል ቋንቋ መንግስታት ከግለሰቦች ብድርን ለማግኘት ለሽያጭ የሚያቀርቧቸው ሰነዶች ናቸው፡፡

ሰነድ ገዢዎች በመንግስታት ለሚሸጡ የቦንድ ሰነዶች ከሞላ ጎደል ጥሩ ፍላጎት አላቸው፡፡ ለግለሰብ ኢንቨስተሮች አሊያም ለድርጅቶች ከማበደር ለመንግስታት ማበደር የአበዳሪው ገንዘብ ስለመመለሱ ተጨማሪ ማስተማመኛ ይሰጣል፡፡ ሌላኛው ማስተማመኛ ተበዳሪ አሊያም ሰነድ ሻጭ መንግስታት በብድር ታሪካቸው መሰረት በግምገማ የሚሰጣቸው ነጥብ ነው፡፡ የብድር ገምጋሚ ገለልተኛ ድርጅቶች የተበዳሪውን በጊዜው ብድር የመመለስ ታሪክ ገምግመው ነጥብ ይሰጣሉ፡፡ ሰነድ ገዥዎች በዚህ ግምገማ ጥሩ ነጥብ ላላቸው አገራት ለማበደር ወይንም ሰነዶቻቸውን ለመግዛት የተሻለ ፍላጎት ሊኖራቸው እንደሚችል ይገመታል፡፡

የኢትዮጲያ የዩሮ ቦንድ በአለም አቀፍ ገበያው ላይ የነበረው አፈጻጸም ከሞላ ጎደል በተረጋጋ ሁኔታ ላይ እንደቆየ የሲፊዩስ ትንተና ያሳያል፡፡ ሰነዱን አሳልፈው በመሸጥ ለቦንዱ ባለቤቶች ሲያስገኝ የነበረው ገቢ በ2018 እ.ኤ.አ. ቀንሶ 5.47% የነበረ ሲሆን በ2016 እ.ኤ.አ. ደግሞ እጅግ ከፍ ብሎ 9.68% እነደነበረ የተደረገው ትንተና ያሳያል፡፡ ከ2019 እ.ኤ.አ. በፊት በነበሩት የኢትዮጲያ የቦንድ ሽያጭ ለአበዳሪዎቹ በየአመቱ በአማካኝ የ6.9 በመቶ ገቢን ሲያስገኝ ቆይቷል፡፡

ኢትዮጲያ በብድር ገምጋሚ ተቋማት ከዚህ በፊት በአለም አቀፍ የሰነድ ሽያጭ የመጣ ብድር ስለሌለባት “B” ወይም ጥሩ ሊባል የሚችል ውጤት ተሰጥቷታል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በውጪው ንግድ ላይ እየጠነከረ የመጣው የአገልግሎት ዘርፍ፤ ከዳይስፖራው ወደ አገር ቤት የሚላከው ገንዘብ እድገት እና ከቅርብ አመታት በፊት በመጣው ለውጥ ምክኒያት የአጋር አገራት ቀጥተኛ ድጋፍ እና የብድር አቅረቦትም ጨምሯል፡፡ በነዚህና በሌሎች ምክኒያቶች የኢትዮጲያ የሰነድ ዋጋ እየጨመረ እንደሚመጣ ተገምቶ የነበረ ቢሆንም በባበለፉት ጥቂት ቀናት ግን እየሆነ ያለው ይሄ አይመስልም፡፡

ባለፉት 10 ቀናት በዓለም ገበያ ላይ እየተገበያየ ያለው የኢትዮጵያ ቦንድ ዋጋው እየረከሰ መጥቷል

ከጥቅምት 25/ 2013 ዓ/ም እ.ኢ.አ. ጀምሮ ባሉት ቀናት የአገሪቱ ዬሮ ቦንድ ሰነድ ሽያጭ ዋጋው እየቀነሰ እንደመጣ የሚያሳዩ ምልክቶች አሉ፡፡ በግልጽ ቋንቋ የኢትዮጲያን የቦንድ ሰነድ ገዝቼ ብይዘው ላተርፍበት እችላለው ለሚለው መላምት ያለው የይሆናል እድል እየጠበበ ነው እንደማለት ነው፡፡ እውነት ነው፤ ጠባብ የሆነ የአትራፊነት እድል ያላቸውን ነገሮች በርካሽ መግዛት ልምዱ ላላቸው ደፋር ኢንቨስተሮች ዜናው ጥሩ ሊሆን ይችላል፡፡ ይሀ ግን ለደፋር ኢንቨስተሮች ጊዚያዊ ጥቅም ከማምጣቱ በዘለለ አገሪቱ ብድሯን የምትከፍል ታማኝ ተበዳሪ መሆኗን ለማመላከት ምንም ድርሻ አይኖረውም፡፡

በፌደራል መንግስቱና በህውሃት መካከል እየቀጠለ ያለው ወታደራዊ ግብግብ ለዚህ አመኔታ ማጣት ላለው ቀጥተኛ አስተዋጽኦ ማስረጃ ማግኘት አይቻልም፡፡ ሆኖም ወታደራዊም ሆነ ፖለቲካዊ ግብግብ፤ አሊያም ሌሎች ቀላል የሚመስሉ የመንግስት ውሳኔዎችን ጨምሮ በገበያ የሚወሰን ኢኮኖሚ ላይ ስላላቸው ቀጥተኛ ተጽዕኖ ጥናቶችን ማግኘት ይቻላል፡፡ የሴፍየስ ትንተና አገሪቱ ውስጥ ያለው የፖለቲካ አለመግባባት፤ የቦንድ ሰነዱ ዋጋ የሚገዛው ጠፍቶ እንዳይቀንስ እንዲሁም ከቅርብ አመታት በኋላ ካስመዘገበቻቸው ለውጦችም ተጠቃሚ እንዳትሆን እንቅፋት ሊሆንባት እንደሚችል በ2019 እ.ኤ.አ. ትንበያውን አስቀምጦ ነበር፡

ክርስቶፍ ሞዜር በ2007 እ.ኤ.አ. ጥናቱ የ1981 እ.ኤ.አ. የተደረገን ሌላ ጥናት ጠቅሶ የፖለቲካ አደጋዎች ከአገር ውጪ በሚሸጡ የቦንድ ሰነዶች ላይ ቀጥተኛ የሆነ ተጽዕኖ አላቸው ይላል፡፡ ክርስቶፍ በጥናቱ አገራት ብድርን የመክፈል ፍላጎት እና ብድርን የመክፈል አቅም ተለያይተው መታየት ያለባቸው ጉዳዮች እንደሆኑ ማስረጃዎች አሉ ይላል፡፡ ብድርን የመክፈል አቅም ቢኖርም ብድርን የመክፈል ፍላጎት ግን ፖለቲካዊ ውሳኔ መሆኑን ያነሳል፡፡ ይህን ፖለቲካዊ ውሳኔ በአገር ውስጥ የሚፈታተኑ ሁኔታዎች መኖራቸው በአለም አቀፍ ገበያ ውስጥ ለሚኖረው አፈጻጸም ቀጥተኛ ድርሻ ይኖራቸዋል ይላል፡፡

ሞሃመድ ቡዋዚዝ በታህሳስ ወር በ2010 እ.ኤ.አ እራሱን በጋዝ አርከፍክፎ በማቃጠል አመርቅዞ የሰነበተውን ፖለቲካዊ ቅያሜ ቀስቅሶ በቱኒዚያና በአረቡ አለም በፖለቲካ ንቅናቄ መልክ ለኮሰ፡፡ ይህ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በቱኒዚያ ኢኮኖሚ ላይ ጥሎ ያለፈውን ጥቁር ጠባሳ በ2018 እ.ኤ.አ. ያጠናው ሰላማ ዛይኒ የፖለቲካ ግብግብ ገበያ መር የሆነ ኢኮኖሚ ላይ ስላለው ተጽዕኖ የሚስማማ ይመስላል፡፡ የ2011 እ.ኤ.አ. የፖለቲካ አብዮት ተከትሎ የቱኒዚያ የአክሲዮን ድርሻ ገበያ በ21 በመቶ ቀንሶ እንደነበር፤ አብዮቱን ተከትሎ የታዩት የጸጥታ ችግሮችም አገሪቱን ለዘገምተኛ ኢኮኖሚያዊ እድገት ከመዳረጉም በላይ አገሪቱ የአለም አቀፍ ኢንቨስተሮችን ፍላጎት እንዳትማርክ አድርጓታል ይላል ሰላማ፡፡

በባለፉት ጥቂት አመታት በአለም ላይ የታዩ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ እውነታዎች በካፒታል ገበያው ላይ ከፍተና ተጽዕኖ እንዳላቸው ያሳዩ ሆነው አልፈዋል የሚሉት ደግሞ ዶ/ር ማውሪቺዮ ቫርጋስ እና ፍሎሪያን ሶመር ናቸው፡፡ በግንቦት 2015 እ.ኤ.አ.  ባቀረቡት ጥናት የአረብ አለሙ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በፖለቲካ እና በኢኮኖሚው ዘንድ ያለን ግንኙነት ምንያክል ጠንቃራ እንደሆነ የተማርንበት ነው ይላል፡፡ እንዳውም ከነዚህ አመታት በኋላ ኢንቨስተሮች ገንዘባቸውን ከማውጣታቸው በፊት ከፋይናንስ ዘርፍ አማካሪዎች በተጨማሪ የፖለቲካ ሁኔታ ተንታኞችም እየፈለጉ ይገኛሉ ይላሉ፡፡

ኢዜማ መንግስት የኢትዮትሌኮም 40 በመቶ ድርሻ ለመሸጥ ስለመወሰኑ በነሃሴ 2012 እ.ኢ.አ. ባዘጋጀው ውይይት የገበያ መር ኢኮኖሚ ውሳኔ ኢኮኖሚያዊ ብቻ አለመሆኑን ያሳየ ነበር፡፡ የፓርቲው መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በውይይቱ መጨረሻ ባደረጉት ንግግር ድርሻውን በዚህ ጊዜ መሸጡ ኪሳራ ነው ሲሉ ተደምጠው ነበር፡፡ የኢኮኖሚክስ ፕሮፌሰሩ ምክኒያታቸውን ሲያስረዱም፤ የኮሮና በሽታ አለም ላይ ባመጣው ሁኔታ የኢንቨስተሮች ፍላጎት በመቀነሱ በርካሽ ዋጋ እንዳንሸጠው ያሰጋኛል የሚል ነበር፡፡ ይህም በገበያ መር ኢኮኖሚ ውጤታማ መሆን ኢኮኖሚያዊ ውሳኔ ብቻ ሳይሆን ፖለቲካዊም፤ ማህበራዊም ከመሆኑ ባሻገር አስተማማኝ ጸጥታን እና ምቹ ሁኔታን አንደሚፈልግ ማሳያ ነው፡፡

እጣ ፋንታው በገበያው የሚወሰን ኢኮኖሚን መገንባት ጠንካራና ዘመን ተሻጋሪ መተማመንን የሚሰጡ ፖለቲካዊ፤ ማህበራዊና ህጋዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን ይጠይቃል፡፡ የፖለቲካ ግብግብን በጊዜ እና በቅጡ ማስተዳደር ያቃተው መንግስት ለወጠነው “ብልጽግና” ስልጣን ባለው የፖለቲካ ፓርቲ አሊያም በሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ቅዠት ሆኖ ይቀር ወይ የሚል ጥያቄ እንድናነሳ አስገዳጅ ይሆናል፡፡ ዜጎች በመንግስት የታለመላቸው “ብልጽግና” ቢዘገይ ወይ ቢቀር እንኳን በግል ጥረታቸው የገነቡት ህልማቸው የቅንጦት እንዳይሆንባቸው መጣር ሁሉም ተዋናይ ሊያሟሉት የሚገባ ትንሹ መስፈርት ነው፡፡ ለራሄል እና ለእጮኛዋ ለጊዜው የቤተሰብ ትውውቅ ማካሄድ የቅንጦት ሆኖባቸዋል፡፡ ለጊዜው በግምት እና በቁዘማ በትንሿ ሱቅ ውስጥ ማሳለፍ ግዴታ ሆኗል፡፡

አረ ሁሉም ነገር ቀርቶብኝ በመጣችና ከኔው ጋር እዚሁ በኖረች፡፡

ትላለች ራሄል የቤተሰብ ትውውቁ በአሁኑ ወቅት ቢቀርም ቅር እንደማይላት ስታብራራ፡፡ እጣ ፋንታው በገበያው በሚወሰንበት ኢኮኖሚ ይዞት በሚመጣው የፉክክር አለም ውስጥ ያልተራመደ ህይወት ወደኋላ እንደሄደ ይቆጠራል፡፡ የጸጥታ ችግርና የፖለቲካ ግብግብ ዜጎችን ከትዳር፤ አገርን ከአም አቀፍ ተወዳዳሪነት ማዘግየቱን ባህል አድርጎ ከተያያዘው፤ ምህረት የለሽ የገበያው ዳኝነት ሲታከልበት ውድድሩ ንበረትን በርካሽ ከመሸጥ የዘለለ ውጤት ሳያመጣ እንዳይቀር ያሰጋል፡፡