Sunday, April 11, 2021

በአስመራ ከተማ የሚሳኤል ጥቃት ተፈፀመ

Must Read

በአክሱም ከተማ ስለተፈፀመው ጭፍጨፋ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ሙሉ ሪፖርቱን ይፋ አደረገ

  ተቀማጭነቱን በለንደን ከተማ ያደረገውና በሰብአዊ መብት ጉዳዮች ላይ በመላው አለም ክትትል የሚያደርገው አምነስቲ ኢንተርናሽናል ከሰአታት በፊት ባወጣው ባለ 25...

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከፊል ድርሻ ለቱርክ መንግስት ሊሸጥ ነው

ዛሬ ከዋሽንግተን ዲሲ አካባቢ የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው በጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የሚመራው የኢትዮጵያ መንግስት የኢትዮጵያ አየር መንገድን እስከ...

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ የሸጠችው ቦንድ ዋጋው እያሽቆለቆለ ነው

ከውጭ ባለሃብቶች 1 ቢልዮን ዶላር ለመበደር በ2007 እ.ኢ.አ ኢትዮጵያ የሸጠችው ቦንድ በአየርላንድ የቦንድ ገበያ ላይ ባለሃብቶቹ እርስ በርስ የሚገበያዩበት...

ይህ ዘገባ በየጊዜው መረጃ የሚጨመርበት ስለሆነ ይከታተሉ

ከጠዋቱ 1:55 ህዳር 6

በትላንትናው ምሽት መነሻቸው ከትግራይ ክልል እንደሆኑ የሚገመቱ ሚሳኤሎች በአስመራ ከተማ ላይ ጥቃት ፈፅመዋል። አለም አቀፉ የዜና አውታር ሮይተርስ በአስመራ ከተማ የሚገኙ አምስት የዲፕሎማቲክ ምንጮችን ገልፆ እንደዘገበው “በትንሹ” ሶስት ሚሳኤሎች በኤርትራዋ ዋና ከተማ ላይ ያረፉ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ሁለቱ የአስመራ አየር ማረፍያን እንዳጠቁ ተሰምቷል።  የኤርትራ መንግስት እስካሁን በጉዳዩ ላይ ይፋ መግለጫ ያልሰጠ ሲሆን ጥቃቱ በሰውም ሆነ በንብረት ላይ ምን ያህል ጉዳት እንዳደረሰ የታወቀ ነገር የለም።

ከጠዋቱ 4፡00 ህዳር 4

የትግራይ ክልል ለነዋሪዎች ቦንድ መሸጥ ጀመረ። ይህ “መከታ ልማት ትግራይ” የሚል ስያሜ የተሰጠው ቦንድ የ5 አመት እድሜ ያለው ሲሆን አላማውም ሕብረተሰቡ በእጁ ላለው ገንዘብ ዋስትና እንዲኖረው ነው ተብሏል። በተጨማሪም የክልሉ ምክትል ርእሰ መስተዳደር የሆኑት ዶ/ር አብርሃም ተከስተን ጠቅሶ የቦንዱ ሽያጭ ሌላው ጥቅም ትግራይ ክልል ያጋጠማትን አደጋ ለመከላከል የሚረዳ ነው ሲል የክልሉ ሕዝብ ግንኙነት ቢሮ በፌስቡክ ገፁ ገልጿል። ዶ/ር አብርሃም የክልሉ ሕብረተሰብ ዕድሜ ሳይገድበው ሁሉም ነዋሪ ቦንዱን እንዲገዛ ጥሪ አቅርበዋል። የክልሉ የፋይናንስ ሀላፊ አቶ ዳንኤል አሰፋ በበኩላቸው ቦንዱ ችግሮችን ለመፍታት የሚያግዝና በሁሉም ባንኮች እንዲሁም የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ተፈፃሚነት ይኖረዋል ብለዋል።

በተያያዘ መልኩ መቀመጫነቱን በትግራይ ክልል ያደረገው ደደቢት የማይክሮ ፋይናንስ ተቋም፣ እስካሁን ስራ እንዳላቆመ አስታውቋል። ይሁን እንጂ ሕብረተሰቡ ቆጥቦ መጠቀም ያለበት በመሆኑ ከ10ሺ ብር በላይ ማውጣት እንደማይቻል የተቋሙ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሙሉጌታ ብርሃነ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል። አቶ ሙሉጌታ አክለውም ማይክሮ ፋይናንሱ ለ70ሺ የሚሆኑ ጡረተኞች ከእለተ ማክሰኞ ጀምሮ ክፍያ መፈፀም መጀመሩንና እንዲሁም 100ሺ ለሚሆኑ የክልሉ መንግስት ሰራተኞች የጥቅምት ወር ደሞዝ መክፈል ተጀምሯል ብለዋል።

በትግራይ ክልልና በኢትዮጵያ የፌደራል መንግስት መካከል የተቀሰቀሰውን ይፋ ጦርነት ተከትሎ በክልሉ ያሉ ባንኮች በብሔራዊ ባንክ ትእዛዝ ላለፉት 10 ቀናት ዝግ ሆነው መቆየታቸውንና እስካሁንም ስራ እንዳልጀመሩ ከክልሉ የሚወጡ ዘገባዎች ያሳያሉ።

ከጠዋቱ 4፡30 ጥቅምት 27

የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሃፊ አንቶንዮ ጉቴሬዝ በትግራይ ክልል ያለው ሁኔታ እጅጉን እንዳሳሰባቸው በትዊተር ገፃቸው ገለፁ። መቀመጫቸውን በኒውዮርክ ከተማ ያደረጉት ፖርቱጋላዊው ዋና ፀሃፊ የኢትዮጵያ መረጋጋት ለአፍሪካ ቀንድ እጅጉን ወሳኝ እንደሆነ አሳስበው በአካባቢው ያለው ውጥረት በአፋጣኝ እንዲቃለልና በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ጥሪ አቅርበዋል።

ከጠዋቱ 4፡03 ጥቅምት 27

ኑቨል ደጅቡቲ የተባለው የፈረንሳይኛ ድህረ ገፅ እንደዘገበው 16 የሚሆኑ የትግራይ ተወላጅ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ከሁለት ቀናት በፊት ወደ ጅቡቲ ገብተዋል። 1 ኮረኔል፣ 1 ኮማንደርና 12 ሉተናንቶችን የያዘው ይህ ቡድን ጅቡቲ ገብቶ ጥገኝነት ቢጠይቅም የጅቡቲ መንግስት ግን አሳልፎ ለኢትዮጵያ መንግስት ለመስጠት መወሰኑን ዘግቧል። እነዚህ የመከላከያ አባላት በጄኔቫው የ1951 ኮንቬንሽን መሠረት ጅቡቲ አሳልፋ ልትሰጣቸው እንደማይገባ እየተከራከሩ ነበር የሚለው ድህረገፁ የጅቡቲ መንግስት በወታደራዊ አውሮፕላን ትላንት ማምሻውን ወደ አዲስ አበባ ሊልካቸው አቅዶ እንደነበር ያወሳል። ይሁን እንጂ አባላቱ ወደ አዲስ አበባ ይመለሱ አይመለሱ እስካሁን ሊያረጋግጥ አልቻለም።

ከጠዋቱ 3:45 ጥቅምት 27

በአዲስ አበባ ቦሌ አየር ማረፍያ የትግራይ ብሔር አባላት የሆኑ መንገደኞች ተመርጠው ከአገር እንዳይወጡ እንደተከለከሉ ኢትዮኖሚክስ አረጋግጧል። መንገደኞቹ የውጭ አገር ቪዛ ያላቸው ቢሆንም መታወቅያዎቻቸውን በመጠቀም ብሔራቸው እየተለየ ከበረራ እንዲቀሩ ተደርጓል። በተመሳሳይ መልኩ በአየር ማረፍያው የሚሰሩ የትግራይ ብሔር አባላት የሆኑ የጥበቃና የደህንነት ሰራተኞች በአሁኑ ወቅት ከስራቸው እረፍት ወስደው በየቤታቸው እንዲቆዩ መደረጋቸውን ኢትዮኖሚክስ አረጋግጧል።

ከጠዋቱ 2፡00 ጥቅምት 27

ሱዳን ውስጥ ካሉት 18 ክልሎች አንዷ የሆነችውና ከኤርትራ እስከ ትግራይ ሁመራ ከተማ የሚዘረጋ አዋሳኝ ድንበር ያላት የቃሳላ ክልል በሁመራ በኩል ያለውን አዋሳኝ ድንበር መዝጋቷን አስታወቀች። የድንበሩን መዘጋት ያስታወቁት የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳዳሪ ፋትሃል ራህማን አልአሚን ሲሆኑ ሱዳን ኒውስ ኤጀንሲ የተባለው የመንግስት ሚድያ እንደዘገበው ድንበሩን የመዝጋት ውሳኔ የተደረገው በኢትዮጵያ በትግራይ ክልል አቅራብያ ባለው ውጥረት ምክንያት መሆኑን ታውቋል። የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳዳሪ አክለውም በቅርቡ ሁኔታውን ለመቃኘት ወደ ድንበሩ እንደሚጓዙ አስታውቀው አሁን ባለው ሁኔታ ማንኛውም አይነት የታጠቀ ግለሰብም ሆነ ቡድን ወደ ድንበራቸው እንደማያስገቡ አስታውቀዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም የሌላኛዋ ጋዳረፍ የተባለች የሱዳን ክልል አስተዳዳሪ ወታደሮቻቸውን ወደ ኢትዮጵያ የአማራ ክልል ድንበር አቅራብያ ማስጠጋታቸውን አስታውቀዋል። አስተዳዳሪው እንዳሉት ወታደሮቹን ማንቀሳቀስ ያስፈለገው ድንበር ተሻግረው በመግባት በሱዳን ገበሬዎች ላይ ጥቃት የሚያደርሱ ቡድኖች ሊኖሩ ይችላሉ በሚል ስጋት መሆኑን ገልፀዋል።

ከጠዋቱ 12፡00 ጥቅምት 27

የተባበሩት መንግስታት በትግራይ ክልል ለሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ኤርትራውያን ስደተኞች መደበኛ የምግብና የቁሳቁስ እርዳታን ማቅረብ እንዳልቻለ የአሜሪካው ኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ዘገበ። ተቋሙ በትግራይ ክልል የሚያደርገው እንቅስቃሴ የተስተጓጎለበት ከመሆኑም በተጨማሪ ሰራተኞቹ ወደ መቀሌ ለመግባት የይለፍ ቃል እስኪሰጣቸው ድረስ በከተማዋ መግብያ እየተጠባበቁ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።

ከምሽቱ 1፡42 ጥቅምት 26

የኢትዮጵያ አየር ሃይል በመቀሌ ከተማ የአየር ድብደባ አካሄደ። ድብደባው ምን አይነት ጉዳት እንዳደረሰም ሆነ በየትኛው የመቀሌ አካባቢ እንደተፈፀመ ኢትዮኖሚክስ ለማረጋገጥ አልቻለም።

ከምሽቱ 12፡00 ጥቅምት 26

በሱማልያ ጌዶ ከተማ ያሉ የኢትዮጵያ ወታደሮች ካምፓቸውን ለቀው ወደ ኢትዮጵያ ድንበር እየተመለሱ እንደሆነ የአይን እማኞችን ጠቅሰው የተለያዩ የሱማልያ መገናኛ ብዙሃን እየገለፁ ይገኛሉ። እነዚህ ወታደሮች አልሻባብን በመዋጋት ላይ ላለው የአፍሪካ ሕብረት አሚሶም ጦር ኢትዮጵያ ካበረከተቻቸው ወታደሮች ውጪ ያሉና በቀጥታ በኢትዮጵያ መከላከያ ሃይል እዝ ስር የነበሩ መሆናቸው ታውቋል።

ከጠዋቱ 5፡12 ጥቅምት 25

የኢፌድሪ ሚኒስትሮች ምክር ቤት በትግራይ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አወጀ። ከደቂቃዎች በፊት ከጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት የወጣ መግለጫ እንደሚከተለው ነው፡

“የኢፌድሪ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ጥቅምት 25/2013 ባደረገው 21ኛ አስቸኳይ ልዩ ስብሰባ መንግሥት የሀገርን ሰላምና ሕልውና፣ የሕዝብንና የዜጎችን ደህንነት የማረጋገጥ እና ሀገሪቷን ወደ ሁከትና ብጥብጥ የሚወስዱ ማናቸውንም ድርጊቶችን የመከላከል ሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነት ያለበት መሆኑን በመገንዘብ፤ እንዲሁም በትግራይ ብሔራዊ ክልል ውስጥ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን እንዲሁም የሕዝብን ሰላምና ፀጥታ አደጋ ላይ የሚጥሉ በተለይም የሀገርን ሉዐላዊነት የሚገዳደሩ፣ የፌደራል መንግሥት በሕገ መንግሥቱ የተሰጠውን ሥልጣንና ኃላፊነት በክልሉ እንዳይወጣ እና ሀገሪቷን የጦር አውድማ የሚያደርጉ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔዎችን ጭምር በመጣስ በርካታ ሕገ ወጥ ተግባራት እየተፈፀሙ በመሆኑ፤ ይህን ሁኔታ በመደበኛው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የማይቻልበት ደረጃ ላይ መደረሱን በመረዳት፤ በሕገ መንግሥቱ በተደነገገው መሠረት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመጠበቅ ልዩ እርምጃዎችን መውሰድ የሚያስችል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመደንገግ እና ተግባራዊ በማድረግ ሁኔታውን በመቆጣጠር በሀገሪቱ ሰላምና ሕልውና ላይ የተጋረጠውን አደጋ መከላከል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 93/1/ሀ መሰረት የሚከተለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለስድስት ወራት ተፈጻሚ የሚሆን ሲሆን፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚያስፈፅም በኢፌድሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ሰብሳቢነት የሚመራና አግባብነት ካላቸው አካላት የተወጣጡ አባላት ያሉት ግብረኃይል በዚህ አዋጅ ተቋቁሟል። ግብረኃይሉ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲሆን ‘‘የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ግብረሀይል’’ ተብሎ ይጠራል።አዋጁ በመላው የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መስተዳድር ተፈፃሚ የሚደረግ ሲሆን፣ እንደያስፈላጊነቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተፈፃሚ ወይም ቀሪ የሚሆንባቸውን ተጨማሪ አካባቢዎችነ ግብረኃይሉ በሚያወጣው በመመሪያ ይወስናል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አስመልክቶ ዝርዝር መርጃዎች በየጊዜው ለህብረተሰቡ የሚሰጡ ይሆናል።”

 

ከጠዋቱ 4፡56 ጥቅምት 25

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ጎንደር፣ መቀሌ፣ ሽሬና አክሱም የሚያደርጋቸውን በረራዎች ላልተወሰነ ጊዜ ማቋረጡን ኢትዮኖሚክስ አረጋግጧል።

ከጠዋቱ 4፡14 ጥቅምት 25

አሁን በደረሰን መረጃ መነሻቸውን ከመቀሌ አሉላ አባነጋ አየር ማረፍያ ያደረጉ ሁለት ኤርባስ አውሮፕላኖች በርካታ ወታደሮችን ይዘው አዲስ አበባ ቦሌ አየር ማረፍያ ደርሰዋል። እነዚህ በተለምዶ በመንገደኛ ተርሚናል ያርፉ የነበሩ አውሮፕላኖች ዛሬ በካርጎ ማስተናገጃ ያረፉ ሲሆን ወድያውኑ በወተዳሮች እንደተከበቡ ኢትዮኖሚክስ በስፍራው ካሉ ታማኝ ምንጮች ለመረዳት ችሏል።

ከጠዋቱ 4፡00 ጥቅምት 25

ትላንትና ማምሻውን በመቀሌ ከተማ ከባድ የቶክስ ልውውጥ እየተሰማ እንደነበር የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢትዮኖሚክስ ያስታወቁ ሲሆን ይህንን ተከትሎም በትግራይ ክልል የስልክና የኢንተርኔት ግንኙነቶች ሙሉ ለሙሉ ተቋርጠዋል። ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ከሰአታት በፊት በፌስቡክ ገፃቸው በሰጡት መግለጫ “ሕወሐት በትግራይ በሚገኘው የመከላከያ ካምፕ ላይ ጥቃት አድርሷል። ሰሜን ዕዝንም ለመዝረፍ ሙከራ አድርጓል። ” ሲሉ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ አክለውም “የመከላከያ ሠራዊታችን በኮማንድ ፖስት እየተመራ ሀገሩን የማዳን ተልዕኮውን እንዲወጣ ትእዛዝ ተሰጥቶታል።” ያሉ ሲሆን ኢትዮኖሚክስ ለጊዜው ሊያረጋግጣቸው ያልቻሉ በርካታ መረጃዎች በአካባቢው ተኩስ እንደቀጠለ እየዘገቡ ይገኛሉ።

የትግራይ ክልል መንግስት በበኩሉ ከጥቂት ሰአታት በፊት ባወጣው መግለጫ በክልሉ ምንም አይነት የአየር ላይ በረራ እንዲሁም የሰራዊት እንቅስቃሴ እንዳይኖር ማገዱን አስታውቋል። በተጨማሪም “የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ ከትግራይ ሕዝብ ጎን ለመቆም ወስኗል” የሚል መግለጫ በድምፂ ወያነ የተዘገበ ቢሆንም በአካባቢው ባሉ የስልክና የኢንተርኔት ግንኙነቶች መቋረጥ ምክንያት ከሁለቱ ወገኖች በኩል ከሚሰጡ መግለጫዎች ውጪ ኢትዮኖሚክስ በመሬት ላይ ያለውን እውነታ እስካሁን በአግባቡ ለማረጋገጥ አልቻለም።

- Advertisement -

2 COMMENTS

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisement -

Latest News

በአክሱም ከተማ ስለተፈፀመው ጭፍጨፋ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ሙሉ ሪፖርቱን ይፋ አደረገ

  ተቀማጭነቱን በለንደን ከተማ ያደረገውና በሰብአዊ መብት ጉዳዮች ላይ በመላው አለም ክትትል የሚያደርገው አምነስቲ ኢንተርናሽናል ከሰአታት በፊት ባወጣው ባለ 25...

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከፊል ድርሻ ለቱርክ መንግስት ሊሸጥ ነው

ዛሬ ከዋሽንግተን ዲሲ አካባቢ የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው በጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የሚመራው የኢትዮጵያ መንግስት የኢትዮጵያ አየር መንገድን እስከ ግማሽ የሚጠጋ የባለቤትነት ድርሻ ለቱርክ...

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ የሸጠችው ቦንድ ዋጋው እያሽቆለቆለ ነው

ከውጭ ባለሃብቶች 1 ቢልዮን ዶላር ለመበደር በ2007 እ.ኢ.አ ኢትዮጵያ የሸጠችው ቦንድ በአየርላንድ የቦንድ ገበያ ላይ ባለሃብቶቹ እርስ በርስ የሚገበያዩበት ዋጋ ማሽቆልቆሉን ቀጥሏል። ከሶስት ሳምንታት...

ኤርትራ፤ ከተራራው ጀርባ ጠልቃ የቀረችው ሰሜናዊት ኮኮብ

  ኤርትራ ከባህር በሯ በዘለለ፤ ምድሯ ጥቅም የለውም የሚለው አስተሳሰብ ከኢትዮጲያ ጋር ፍቺ ሳትፈጽም በፊት ገዢ ሃሳብ ሆኖ ነው የኖረው፡፡ በደርግ ጊዜ የኢትዮጲያ ፕሬዝዳንት የነበሩት...

ኢኮኖሚያዊ ህልሙ በፖለቲካ ይጨናገፍ ይሆን?

  በ2013 እ.ኤ.አ. የአዲስ አበባ መስፋፋት የኦሮሚያ ገበሪዎችን አፈናቅሏል በሚል የተጀመረው የጸጥታ አለመረጋጋት ሰባት አመታትን አስቆጥሯል፡፡ ይህ አመጽ አሁን ያሉትን ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ ስልጣን አምጥቶ...
- Advertisement -

More Articles Like This

- Advertisement -