በዓለም ገበያ የሚዘዋወረው ባለ 1 ቢልዮን ዶላር የኢትዮጵያ ቦንድ ዋጋ አገግሟል

0

የኮሮና ቫይረስ መሰራጨትን ተከትሎ ዋጋው አሽቆልቁሎ የነበረው የኢትዮጵያ ዩሮ ቦንድ በዚህ በያዝነው ሳምንት በዓለም ገበያ ላይ በሙሉ ዋጋው ወይም 1 ቦንድ በመቶ ዶላር በመሸጥ ላይ ይገኛል፡፡ የዛሬ 5 ዓመት ኢትዮጵያ 1 ቢልዮን ዶላር ያክል ከዓለም ኢንቨስተሮች ለመበደር ስትል የሸጠችው ይህ ቦንድ ከመጋቢት ወር ጀምሮ ከኮሮና ወረርሽኝ መስፋፋት ጋር ተያይዞ በመጣ ስጋት አንዳንድ ኢንቨስተሮች በእጃቸው ያለውን ቦንድ ለሽያጭ በማቅረባቸው ከበሽታው መከሰት በፊት ከነበረው ዋጋ እስከ 21 ፐርሰንት ወርዶ በመሸጥ ላይ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት በዓመት 62.5 ሚልዮን ዶላር ወለድ ለባለ ቦንድ ኢንቨስተሮች የሚከፍል ሲሆን ምናልባት በበሽታው ምክንያት በሚመጣ የኢኮኖሚ ቀውስ ኢትዮጵያ ወለዱን መክፈል ልታቆም ትችላለች በሚል ስጋት አየርላንድ ላይ የሚገበያየው ቦንድ ተፈላጊነቱ ሊቀንስና ዋጋውም ሊወርድ ችሎ ነበር፡፡

የዩሮ ቦንድ ማለት አገራት ወይም ትላልቅ ኩባንያዎች በውጭ ምንዛሬ ገንዘብ ለመበደር ሲፈልጉ ለዓለም ኢንቨስተሮች የሚሸጡት ሲሆን ተበዳሪዎቹ ገንዘቡን የሚመልሱበት የጊዜ ቀመርም መጀመርያ ላይ የሚወሰን ነው፡፡ በቦንድ መልክ የሚገኝን ብድር ከሌሎች አይነት ብድሮች የሚለየው የብድሩ ሙሉ መጠን በአንድ ጊዜ የሚከፈለው ቦንዱ ቀድሞ የተተመነለት የህይወት ዘመን ሲያበቃ ሲሆን ተበዳሪው አካል እንደ ስምምነቱ በአመት ሁለቴ ወይም አንዴ ወለዱን ብቻ እየከፈለ ይቆያል፡፡ ቦንዱ የህይወት ዘመኑ እስካላለቀ ድረስም ኢንቨስተሮች ለሶስተኛ አካል የመሸጥ መብታቸው የተጠበቀ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ቦንዱን ለገበያ ባቀረበችበት ሰዓት የ1 ቦንድ ዋጋ 100 ዶላር ሆኖ እያለ ኢንቨስተሮች እርስ በርስ ቦንዱን በሚሻሻጡበት ጊዜ ግን ዋጋው ከ100 ዶላር በላይም ሆነ በታች ሊሸጥ ይችላል፡፡ ይህ የሶስተኛ ወገን መገበያያ ዋጋ የሚወሰነው በአቅርቦትና ፍላጎት ላይ ተመስርቶ ሲሆን ቦንዱን የሸጠችው አገር ወቅታዊ የፖለቲካና የኢኮኖሚ አቋም በዋጋው ላይ ተፅዕኖን ያሳድራል፡፡ በተጨማሪም ቦንዱ ለኢንቨስተሮች የሚያስገኘው ዓመታዊ ወለድ ሌሎች አካላት አዳዲስ በሚሸጧቸው ቦንዶች ላይ ከሚገኘው ወለድ ጋር ተነፃፅሮ ተፈላጊነቱ ሊቀንስ ወይም ሊጨምር ይችላል ፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያ የዛሬ 5 ዓመት ልትከፍል የተስማማችው ዓመታዊ ወለድ 6.625 ፐርሰንት ሆኖ ሳለ በዚህ ዓመት ኮሮና ካመጣው አደጋ ጋር ተያይዞ አበዳሪዎች አዳዲስ ከሚሸጡ የታዳጊ አገራት ቦንድ የሚጠይቁት ወለድ ከ7 ፐርሰንት በላይ ከደረሰ የኢትዮጵያውን ቦንድ ተፈላጊነት ብሎም ዋጋውን ይቀንሰዋል ማለት ነው፡፡

በ2007 ዓ.ም ለገበያ የቀረበውና የ10 ዓመት ዕድሜ ያለው የኢትዮጵያ ቦንድ ባለ 1 ቢልዮን ዶላር ቢሆንም ገዢ ኢንቨስተሮች ለሽያጭ ከወጣው መጠን በላይ ለመግዛት እስከ 3.2 ቢልዮን ዶላር አቅርበው ነበር፡፡ ይህ ከፍተኛ ፍላጎት ሊመጣ የቻለው ኢትዮጵያ ልትከፍል የተስማማችበት 6.625 ፐርሰንት የወለድ መጠን በወቅቱ ባደጉት አገራት ይገኝ ከነበረው ወለድ እጅጉን የላቀ በመሆኑና ከወለዱ የሚገኘው ትርፍ ኢንቨስተሮችን በማጓጓቱ ነበር፡፡ በቦንድ ግብይቱ ላይ የተሳተፉት አብዛኛዎቹ ትላልቅ የአሜሪካና የአውሮፓ የኢንቨስትመንት ተቋማት መሆናቸው ደግሞ በወቅቱ ኢትዮጵያ በነበረችበት የኢኮኖሚ አቋምና ብድሩን የመክፈል ብቃት ላይ የነበራቸውን እምነት አሳይቷል፡፡ ሆኖም ቦንዱ በተሸጠ ከ1 ዓመት በኋላ በኦሮምያ ክልል በተለያዪ አካባቢዎች የተቀሰቀሰው ፀረ መንግስት ተቃውሞና ይህንንም ተከትሎ የመጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በቦንዱ ዋጋ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖን እንዲያስከትል አድርጎት ነበር፡፡

ነግር ግን ከለት ወደለት እየተቀጣጠለ የመጣው የኦሮምያ ክልል አለመረጋጋት የቦንዱን መገበያያ ዋጋ የባሰውኑ እንዲያሽቆለቁል ይገፋዋል የሚል ግምት ፈጥሮ እያለ ብዙም ሳይቆይ ዋጋው እያገገመ መምጣቱ የቦንዱ ዋጋ በተበዳሪው አገር ባለው የአገር ውስጥ ሁኔታ ብቻ እንደማይወሰን አሳይቶ ነበር፡፡ በተመሳሳይ መልኩ በ2010 የጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድን ወደ ስልጣን መምጣትና ቃል የገቧቸውን በርካታ ለውጦች እንዲሁም ወደ ነፃ ገበያ የሚያጋድል አመለካከታቸው እያደረ ጎልቶ መውጣት የቦንዱን ዋጋ ሽቅብ ይገፋዋል ተብሎ ቢጠበቅም እምብዛም ሳይለወጥ ቆይቷል፡፡ ይህ የሚያሳየውም በአገር ውስጥ ካለው ሁኔታ ባልተናነሰ መልኩ ባደጉትም ሆነ በታዳጊ አገራት በጥቅል የሚታዩ ሁኔትዎች የቦንድ ኢንቨስተሮችን ፍላጎት ከፍና ዝቅ እንደሚያደርገው ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ በስዊዘርላንድ ያለ የኢንቨስትመንት ተቋም ለታዳጊ አገራት የመደበው ገንዘብ 20 ቢልዮን ዶላር ሆኖ ሳለ በአውሮፓና በአሜሪካ ያለው አማካይ የወለድ መጠን ድንገት ቢቀንስ ትርፉ ላይ ጉዳት የሚያደርስ በመሆኑ ከአሜሪካ ሊገዛ የነበረውን ቦንድ በመተው ተጨማሪ ገንዘብ ወደ ታዳጊ አገራት ይመድባል ማለት ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የአለም የነዳጅ ዋጋ ወይም የመዳብ ማዕድን ዋጋ ድንገት ቢያሽቆለቁል በበርካታ የነዳጅና ኮፐር አምራች በሆኑ አገራት ላይ፣ እንዲሁም በጎረቤቶቻቸው ላይ በቀጥተኛና በተዘዋዋሪ መልኩ ጉዳት ስለሚያደርስ ኢንቨስተሮቹ ለታዳጊ አገራት የመደቡትን ገንዘብ ሊቀንሱና ወደ በለፀጉት አገራት ሊያዘዋውሩት ይችላሉ፡፡ ይህ ወደ ታዳጊ አገራት የሚቀርበውን የገንዘብ አቅርቦት በመጨመር የቦንዶችን ዋጋ ያስወድዳል፡፡

በዚህ ዓመት ታድያ ከወራት በፊት የተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝ አለምን ሙሉ የጎዳ ሆኖ ሳለ የበለፀጉትን አገራት ቦንድ ዋጋ ብዙም ሳይጎዳ ነገር ግን እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ታዳጊ አገራት በሸጡት ቦንድ ላይ ጠንካራ ተፅዕኖን አሳድሯል፡፡ ኮሮና ከመከሰቱ በፊት ከዋጋው በላይ በ109 ዶላር ሲሸጥ የነበረው የኢትዮጵያ ዩሮ ቦንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ዋጋው እስከ 85 ዶላር ወርዶ ነበር፡፡ ይህ ሊሆን የቻለው ያደጉት አገራት መንግስታት ከበቂ በላይ ተቀማጭ ገንዘብ ያላቸው በመሆኑ የቦንዱ ሙሉ ክፍያ መፈፀምያ ጊዜ ሲደርስም ሆነ ለአመታዊ የወለድ ክፍያው የሚሆን ገንዘብ ስለማያጡ በአንፃሩ ግን እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ታዳጊ አገራት ከኤክስፖርትና ከዳያስፖራ የሚያገኙት የውጭ ምንዛሬ ሲቀንስ ወለድም ሆነ ሙሉ እዳቸውን መክፈል ሊቸግራቸው ይችላል በሚል እሳቤ ነው፡፡ እንደተፈራውም አንዳንድ እንደ ዛምብያና አርጀንቲና ያሉ አገራት የወለድ መክፈያ ጊዜያቸውን ያሳለፉ ሲሆን የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድም በበኩላቸው ጂ20 ለሚባለው የሃብታም አገራት ቡድን ለአፍሪካ የብድር ማቃለያ እንዲደረግላት ደብዳቤ ፅፈዋል፡፡

በእርግጥ የኢትዮጵያን እዳ ወክሎ በዓለም ገበያ የሚዘዋወረው የ1 ቢልዮን ዶላር ቦንድ ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ ከሚባሉት ውስጥ ይመደባል፡፡ ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ ያቀረበችው 1 ቦንድ ብቻ ሲሆን እንደ ኬንያና ናይጄርያ ያሉ አገራት ከሶስትና አራት በላይ ቦንዶችን ሸጠዋል፡፡ በተጨማሪም እንደ ደቡብ አፍሪካ አይነት ከመንግስትም አልፎ ትላልቅ ኩባንያዎች የራሳቸውን ቦንድ በውጭ ገበያ ሸጠው የተበደሩባቸው አገራትም አሉ፡፡ በቦንድ መልኩ የሚገኝ ብድር በአብዛኛው ጊዜ በታዳጊ አገራት ዘንድ የማይወደድ ሲሆን ለዚህም ምክንያቱ የቦንድ ኢንቨስተሮች የሚጠይቁት የወለድ መጠን ከአለም ባንክ፣ አይ ኤም ኤፍም ሆነ እንደ ቻይና ካሉ መንግስታት በቀጥታ ከሚገኝ ብድር ጋር ሲነፃፀር እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ከዚህ ቦንድ ሽያጭ ያገኘችው 1 ቢልዮን ዶላር ለተለያዩ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች እንደዋለ የተነገረ ሲሆን ገንዘቡ ከዋለባቸው ፕሮጀችቶች ውስጥም ኢትዮጵያና ጅቡቲን የሚያገናኘው የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታና ሁለት የኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታዎች ይገኙበታል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here