Wednesday, May 25, 2022

ቢሮ እንኳን ሳይኖረው የ3.6 ቢልዮን ዶላር ፕሮጀክት የወሰደው የአሜሪካ ኩባንያና የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ትብብር

“ነገሮች ሲጓተቱ የኩባንያው ሃላፊዎች ወደ ጠቅላይ ሚንስትሩ ቢሮ መጉላላት ደረሰብን የሚል ደብዳቤ ይፅፋሉ፤ ሰዎቹ ግንኙነት አላቸው”

Must Read

ሰበር ዜና – ዛሬ ረፋድ ላይ አዲግራት ከተማ በትግራይ ሰራዊት እጅ ወድቃለች

ባለፉት አራት ቀናት ዘመቻ አሉላ አባነጋ በሚል ፀረ ማጥቃት የጀመረው በህወሃት የሚመራው የትግራይ ሰራዊት በርካታ ከተሞችን መቆጣጠሩን ከስፍራው የደረሰን...

“የትግራይን ሕዝብ እናጠፋዋለን ሲሉ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ቃል በቃል ነግረውኛል” የአውሮፓ ሕብረት ልዩ መልዕክተኛ

ባለፉት 6 ወራት ውስጥ ሁለት ጊዜ ወደ አዲስ አበባ ተጉዘው የነበሩት የፊንላንዱ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ፔካ ሃቪስቶ በትላንትናው እለት...

የኢትዮጵያ መንግስት ሃሰተኛ መረጃ ሲያሰራጭባቸው የነበሩ ከመቶ በላይ ገፆችን ዘግቻለው ሲል ፌስቡክ አስታወቀ

የማህበራዊ ድህረገፁ ፌስቡክ በትላንትናው እለት ባወጣው ዝርዝር ሪፖርት ከመቶ በላይ የሆኑ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ንክኪ ያላቸው ገፆችን እንደዘጋ አስታወቀ።...

ባሳለፍነው ታህሳስ ተቀማጭነቱን በኒውዮርክ ከተማ ባደረገ አንድ ክዋርትዝ የተሰኘ የኢንተርኔት ጋዜጣ ላይ የታተመው ፅሁፍ የኢትዮጵያን መንግስት አንገት ያስደፋና በአንዳንድ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ቁጣን ያጫረ ነበር። ይሁን እንጂ የዚህ ፅሁፍ ወደ አማርኛ አለመተርጎም ከጉዳዩ ክብደት አንፃር በአገር ውስጥ የሚገባውን ያህል ትኩረት ሳያገኝ እንዲቀርና ተድበስብሶ እንዲያልፍ አድርጎታል።

ጉዳዩ እንዲህ ነው። በሱማሌ ክልል ከምድር በታች የነጭ ጋዝ ሃብት ስለመኖሩ ባለሙያዎች ማረጋገጣቸውን ተከትሎ በአካባቢው የማጣርያ ጣብያን ለመገንባት አንድ ግሪንኮም የተባለና በአሜሪካን አገር ቨርጂንያ ክልል ውስጥ የንግድ ፈቃድ ያወጣ ኩባንያ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ይዋዋላል። ይህ አቶ ነብዩ ጌታቸው በተባለ አሜሪካዊ ዜጋ የሚመራው ኩባንያ እንደ ኢትዮጵያውያን አቆጣጠር በ2012 ዓ.ም ሚያዝያ 20 ቀን ነበር ማጣርያውን ለመገንባት የ3.6 ቢልዮን ዶላር ውል ከነዳጅና ማዕድን ሚንስቴር ጋር የተፈራረመው።

ታድያ ለዚህ ማጣርያ ጣብያ ግንባታ የተመደበው 3.6 ቢልዮን ዶላር ከአስር አመት በፊት የህዳሴ ግድብ መሠረት ሲጣል ተመድቦ ከነበረው 4 ቢልዮን ዶላር ጋር መቀራረቡ የፕሮጀግቱን ግዝፈት የሚያሳይ ነበር። ይህ በእንዲህ እንዳለ  በኳርትዝ ጋዜጣ የታተመው ፅሁፍ ይህንን ያህል ግዙፍ ፕሮጀክት እንዴት ለአለም አቅፍ አጭበርባሪዎች እንደተሰጠና የኢትዮጵያ ባለስልጣናት የተጫወቱትን አጠራጣሪ የሆነ ሚና ለአለም ለማጋለጥ በቅቶ ነበር።

ጉዳዩን ማን አጋለጠው?

አንድ ስለ ኢትዮጵያ የነዳጅና ጋዝ ዘርፍ በቂ እውቀት ያለው የመንግስት ሰራተኛ በግሪንኮምና በኢትዮጵያ መንግስት የተገባው ይህ ውል አላማረውምና ቀስ ብሎ ለኳርትዝ ጋዜጠኞች ስለተደረገው የተምታታ ስምምነት የሚያውቀውን ሹክ ይላቸዋል፡፡ ከኳርትዝ ጋዜጠኞች አንዱ የሆነው ትውልደ ኢትዮጵያዊ ዘካርያስ ዘላለምም ጉዳዩን መከታተልና ማጣራትን ስራዬ ብሎ ይያያዘዋል። ጋዜጠኛው ዘካርያስ ምርመራውን አጠናቆ ሲያበቃም ያገኘው መረጃ ከተጠበቀው በላይ ከብዶና አሳፋሪ ሆኖ አግኝቶታል። አጠያያቂ በሆነ መልኩ እንደዚህ አይነት ግዙፍ ፕሮጀክት የተሰጠው ይህ ግሪንኮም የተባለ ኩባንያም ሆነ ሃላፊዎቹ ፕሮጀክቱን ሰርተው ለማስረከብ የሚያስችላቸው ምንም አይነት ብቃትና ልምድ የሌላቸው ሆነው የተገኙ ሲሆን ይባስ ብሎም የቨርጅንያ ክልል መዝገብ ቤት እንደሚያመላክተው ግሪንኮም ከአንድም ሁለት ጊዜ ከስራ ፈቃድ ጋር በተያያዘ አመታዊ ክፍያውን በአግባቡ ሳይከፍል የንግድ ፍቃዱ እስከ መሰረዝ ደርሶ ነበር።  በ2012 ሚያዝያ ላይ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ውሉን በተፈራረመበት ወቅትም በአሜሪካ ምንም አይነት የስራ ፈቃድ የሌለውና ከነጭራሹም መዝገብ ውስጥ ያልነበረ ፍቃዱም ከ5 ወራት በፊት ተሰርዞ እንደነበር ለማረጋገጥ ተችሏል።

ይሁን እንጂ እነዚህ ሁሉ አጠራጣሪ ምልክቶች በኩባንያው ላይ እየታዩም ቢሆን የኢትዮጵያ መንግስት በቂ የሆነ ጥናት ባለማድረጉ ሊታለል ችሏል። አልያም የመንግስት ባለስልጣናት ስለኩባንያው አጠራጣሪ ማንነት እያወቁ ጆሮ ዳባ ልበስ ብለው ለሕዳሴ ግድብ ከወጣው ብዙም የማይተናነስ ወጪ ያለውን የ3.6 ቢልዮን ዶላር የነጭ ጋዝ ማጣርያ ግንባታ ምንም አይነት ፕሮጀክት ሰርቶ ለማያውቀውና በአግባቡ ቢሮ እንኳን ለሌለው ግሪንኮም አሳልፈው ሰጥተዋል።

በዓለም በሃይል ማመንጨት ዘርፍ አሉ ከተባሉት እመደባለው” የሚለው ግሪንኮም የሱማሌ ክልሉን ፕሮጀክት ለማግኘት ሲል የተለያዩ ከእውነት የራቁ መረጃዎችን ሲያቀርብ ቆይቷል። ስለ ጉዳዩ የተጠየቁት የኢትዮጵያ ማዕድን ነዳጅና ባዮጋዝ ኮርፖሬሽን ዋና ሃላፊ አቶ ሙሉጌታ ዳምጠው “ግሪንኮም በዘርፉ ላይ ምንም አይነት ብቃት እንደሌለው አውቃለው፤ ኩባንያውም ከጅምሩ ግንባታውን እራሱ እንደማያከናውነውና ለሶስተኛ ወገን አሳልፎ እንደሚሰጠው ግልፅ አድርጎ ነው የገባው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። በእርግጥ ይህ የአቶ ሙሉጌታ ምላሽ ግሪንኮም ግንባታውን ለማከናወን ከኮርያው ሆንዳይ ኢንጅነሪንግና ኮንስትራክሽን ጋር በጥምረት እሰራለው በሚል በአንድ ወቅት በይፋ ከማወጁ ጋር የሚሄድ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞም ከአመት በፊት ሚያዝያ ወር ላይ በፋና ብሮድካስቲንግ የተዘገበው ዜና እንደሚያሳየው ግሪንኮም ከኮርያው ሆንዳይ ጋር ለመስራት ተስማምቻለው በሚል አውጆ እንደነበር ያሳያል።

ሆኖም ስለተሳትፎው በተደጋጋሚ የተነገረለት የኮርያው ሆንዳይ ኩባንያን የሚያስተዳድሩት ሃላፊዎች ለኳርትዝ በላኩት ኢሜል ኢትዮጵያ ውስጥ አለ ከተባለው ፕሮጀክት ጋር ፈፅሞ ግንኙነት እንደሌላቸውና ግሪንኮም የነዳጅ ማጣርያውን ለመገንባት አብረውት እንዲሰሩ ጥያቄ አቅርቦላቸው የነበረ ቢሆንም የራሳቸውን ጥናት ካደረጉ በኋላ ላለመሳተፍ እንደወሰኑ ገልፀዋል። የሆንዳይ ኢንጅነሪንግና ኮንስትራክሽን ቃል አቀባይ ጂንሆንግ ቾይ ለጋዜጠኞች  በፃፉት ኢሜልም “ከግሪንኮም ጋር ምንም አይነት ስምምነት እንዳልተፈራረምን እንዲታወቅልን እንፈልጋለን፤ በወቅቱ ለግሪንኮም ስለ ኩባንያው የሚያስረዱ የፋይናንስና የሕግ ሰነዶችን እንዲልክልን ጥያቄ ብናቀርብለትም ምንም አይነት መልስ ሳናገኝ ቀርተናል” የሚል እራሳቸውን ከግሪንኮም ስላገለሉበት ምክንያት ፍንጭ የሚሰጥ ምላሽ ሰጥተዋል።

እንደ ጂንሆንግ ቾይ ምላሽ ድርጅታቸው በዚህም ሳያበቃ ስለ ግሪንኮም ውስጣዊ ምንነት የሚያጠና የሶስተኛ ወገን አካል ቀጥሮ የነበረ ሲሆን “ባገኘነው መረጃ መሰረት ግሪንኮም በወቅቱ ምንም አይነት ሌላ ፕሮጀክት እንደሌለው በመገንዘባችን ኩባንያው በማንኛውም አይነት መግለጫ ላይ ስማችንን ያለፈቃዳችን እንዳያነሳ አሳስበነው ነበር” ይላሉ።

የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ስለ ግሪንኮም ትንሽ እንኳን ጥናት ቢያደርጉ ኖሮ ኩባንያው እንደሚለው ሳይሆን ከሆንዳይ ኢንጅነሪንግና ኮንስትራክሽን ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌለው በቀላሉ ለመረዳት በቻሉ ነበር። ልክ የኳርትዝ ጋዜጠኞች እንዳደረጉትም የሆንዳይ ሃላፊዎችን ከግሪንኮም ስላላቸው ግንኙነትና በእርግጥ በግንባታው ላይ እንደሚሳተፉ ለመጠየቅ ሞክረው ቢሆን ኖሮ ኢትዮጵያ ውሉን ከመፈራረሟ ገና ከአራት ወራት በፊት ሆንዳይ ፕሮጀክቱ ላይ የመሳተፍ ፍላጎት እንደሌለው ማሳወቁን በተረዱም ነበር። ታድያ ለምን ሳያጣሩ ቀሩ? ወይስ ይህን ያህል የዋሆች ናቸው?

የግሪንኮም ማጭበርበር በዚህ የሚያበቃም አይደለም። ዋና ስራ አስክያጅ በመሆን ላለፉት 10 ዓመታት ሲያገለግል ቆይቷል የተባለው ትውልደ ኢትዮጵያዊ አቶ ነብዩ ጌታቸው በአሜሪካ አሉ የተባሉ ኩባንያዎችን ሲያማክር እንዲሁም በከፍተኛ አመራር ደረጃ ሲያገለግል እንደኖረና በርካታ ልምድን ያካበተ ስለመሆኑ በግሪንኮም ድህረ ገፅ ላይ የተፃፈ ቢሆንም አቶ ነብዩ በየትኛውም የአሜሪካ ትልቅ ድርጅት በከፍተኛ አመራር ደረጃ እንዳገለገለም ሆነ እንዳማከረ የሚያሳይ መረጃ ሊገኝ አልቻለም። አቶ ነብዩ ከትላልቅ ድርጅቶች ጋር ያለው ብቸኛው ግንኙነት በቨርጂንያ ክልል በአንድ የቶዮታ መኪና መሸጫ ውስጥ ተቀጥሮ መስራቱ ብቻ ነው።

በተጨማሪም የግሪንኮም ከፍተኛ አመራር ተብለው በድህረገፁ ፎቷቸውና የስራ ልምዳቸው የተዘረዘረው ግለሰቦች አምስት ነጭ አሜሪካውያን ሶስት እስያውያንና አቶ ነብዩን ጨምሮ ሁለት ኢትዮጵያውያን ወይም ትውልድ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ በሃይል ማመንጨትና በተለያዩ ዘርፎች በከፍተኛ አመራርነት አሉ በተባሉ ኩባንያዎች እንዲሁም በግል ድርጅቶቻቸው እንዳገለገሉ ቢፃፍም ኳርትዝ ባደረገው ምርመራ እንዲሁም ኢትዮኖሚክስ ባደረገው ተጨማሪ ምርመራ የነዚህ ሰዎች የስራ ልምድም ሆነ ማንነት በጣም አጠራጣሪ ሆኖ ተገኝቷል።

የግሪንኮም ሃላፊዎች ተብለው ፎቷቸው ከተለጠፉት ሰዎች ውስጥ በኮርያ የእርዳታ ድርጅት ተቀጥሮ የሚሰራና ፎቶው ከኢንተርኔት ተሰርቆ የተለጠፈበት ግለሰብ ይገኝበታል

ይባስ ብሎም ከግሪንኮም ሃላፉዎች አንዱ ነው የተባለውና ከየመን እስከ ኮርያና ኢንዶኔዥያ ድረስ ነዳጅ በማውጣትና እንደ ሃንት ኦይል በመሳሰሉት ግዙፍ የአሜሪካ የነዳጅ አውጪ ኩባንያዎች በመስራት የ50 አመታትን ልምድ እንዳካበተ የተነገረለት ሃላፊ እንኳን የነዚህ ሁሉ ልምዶች ባለቤት ሊሆን ይቅርና ግሪንኮም ፎቶውን ከኢንተርኔት ላይ ሰርቆ በድህረ ገፁ ላይ የለጠፈበት በኮርያ በአንድ ተራ የእርዳታ ድርጅት ውስጥ ተቀጥሮ የሚሰራ ግለሰብ ሆኖ ተገኝቷል። ስለ ግለሰቡ ይበልጥ ለማጣራት ወደ አሜሪካው የነዳጅ ኩባንያ ሃንት ኦይል መልዕክት የላኩት የኳርትዝ ጋዜጠኞችም በድርጅታቸው አገልግሏል ስለተባለው ግለሰብ ምንም እንደማያውቁና በየትኛውም ጊዜ ከነሱ ጋር ሰርቶ እንደማያውቅ አረጋግጠዋል።

የግሪንኮም ዋና ስራ አስክያጅ አቶ ነብዩ ጌታቸው በ2012 የነጭ ጋዝ ማጣርያውን ለመገንባት ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር የ3.6 ቢልዮን ዶላር ውል በተፈራረሙበት ሰሞን ፕሮጀክቱ ሲያልቅ ኢትዮጵያ ከውጭ ከሚመጣ ጋዝ ትላቀቃለች ብለው ነበር። ግሪንኮምን ወክለው ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር የተፈራረሙት ሌላኛው ግለሰብ አቶ አማኑኤል መኩርያ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ ከአስር ሺ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የስራ እድል እንደሚፈጥርም ገልፀው ነበር። ታድያ ዛሬ የሃይል ማመንጨት ባለሙያ ሁነው ብቅ ይበሉ እንጂ አቶ አማኑኤል ከዚህ በፊት የሚታወቁት አዲስ አበባ ላይ ባላቸው ታዋቂ የጃዝ መሸታ ቤት ነበር።

አሁንም ጥያቄው እንደዚህ አይነት አጠያያቂ የሆነ ማንነትን ይዞ የመጣው ግሪንኮም እንዴት ይህንን የሚያክል ግዙፍ የ3.6 ቢልዮን ዶላር ፕሮጀክት ከመንግስት ሊረከብ ቻለ ነው። በ2011 ሪፖርተር ጋዜጣ በእንግሊዘኛ እትሙ ባወጣው ፅሁፍ ላይ በወቅቱ የኢትዮጵያ ማዕድን ነዳጅና ባዮጋዝ ዳይሬክተር የነበሩት አቶ አንዳርጌ በቀለ ስለ ግሪንኮም በቂ ጥናት እንዳከናወኑ የገለፁ ሲሆን “የኩባንያውን የፋይናንስ የቴክኒካልና የሕግ አቋም በአግባቡ ገምግመን የሚያረካ ውጤት አግኝተናል” ብለው ነበር።

ከሁለት አመታት በኋላ ኳርትዝ አቶ አንዳርጌን አግኝቶ እንዴት እነዚህ ሁሉ አጠራጣሪ ምልክቶችን እያዩ የግሪንኮምን ፕሮፖዛል ተቀብለው አፀደቁ ብሎ ላቀረበላቸው ጥያቄ “አንድን ኩባንያ ገና ለገና የሚያምታታ ነገር አገኘንበት ብለን እንዲሸሽ ማድረግ የለብንም” ካሉ በኋላ “ኢትዮጵያ ከዚህ የምትጠቀመው ነገር ሊኖር ይችላል፤ በዛላይ ደግሞ ከኛ በተጨማሪ ሌሎች የመንግስት ተቋማትም ፕሮፖዛሉን አፅድቀውታል” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ሌላኛው የማዕድን ነዳጅና ባዮጋዝ መስርያቤት ሃላፊ አቶ ሙሉጌታ ዳምጠው በበኩላቸው መስርያቤታቸው ከግሪንኮም ጋር ስለ ቴክኒካል ጉዳዮች በመወያየት ላይ እያለ የማዕድን ሚንስቴር ጣልቃ በመግባት ሃላፊነቱን ተረክቦ ጉዳዩን መከታተል እንደጀመረና የሳቸው መስርያቤትም ከሂደቱ እንደተገለለ ገልፀዋል።

አምባሳደር ፍፁም አረጋ በዋሽንግተን ዲሲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ

ግሪንኮም በድህረገፁ ላይ ያሰፈራቸው የተለያዩ ሃሰተኛ መረጃዎች እንዴት በመንግስት ዘንድ ጥያቄን አላስነሱም ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄም ሃላፊው ሲመልሱ ኩባንያው ከጠቅላይ ሚንስትሩ ፅህፈት ቤት ጀምሮ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር በመሆን ከሚያገለግሉት አቶ ፍፁም አረጋና ሌሎች የበላይ አካላት ድጋፍ እንደነበረውና ይህንን ግንኙነት ተጠቅሞ ሂደቱን ለማፋጠን እንደቻለ አስታውቀዋል። አቶ ሙሉጌታ ሲያብራሩም  “ነገሮች ሲጓተቱ የኩባንያው ሃላፊዎች ወደ ጠቅላይ ሚንስትሩ ቢሮ መጉላላት ደረሰብን የሚል ደብዳቤ ይፅፋሉ፤ ሰዎቹ ግንኙነት አላቸው” ይላሉ።

አቶ ሙሉጌታ ለግሪንኮም ድጋፍ የሚሰጡ ሁለት ደብዳቤዎች ከአምባሳደር ፍፁም አረጋ ወደ መስርያ ቤታቸው እንደተላከም ያወሳሉ። አምባሳደር ፍፁም መጀመርያ በጠቅላይ ሚንስትሩ ቢሮ ሲሰሩ ኋላም በአሜሪካ አምባሳደር ሆነው ከተሾሙ በኋላ በፃፏቸው ሁለት ደብዳቤዎች ግሪንኮም አስተማማኝ ኩባንያ እንደሆነና ኢትዮጵያ ውስጥ ገብቶ ለመስራት ብቃት እንዳለው መስክረውለት ነበር ሲሉ አቶ ሙሉጌታ ያስታውሳሉ።

በሌላ በኩል በ2012 ሚያዝያ ላይ የኢትዮጵያ መንግስትን ወክለው የተፈራረሙትና በወቅቱ የማዕድንና ነዳጅ ሚንስትር የነበሩት አቶ ሳሙኤል ኡርካቶ ባሳለፍነው ነሓሴ ያለ ምንም ማብራርያ ከሃላፊነታቸው በድንገት የተነሱ ሲሆን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስትር ሆነው ተሾመዋል። የአቶ ሳሙኤል ቦታን በመተካትም ስለ ግሪንኮም ፕሮጀግት ምንም የሚያውቁት ነገር እንደሌለ የተናገሩት የቀድሞው የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ የማዕድንና ነዳጅ ሚንስትር ሆነው ከወራት በፊት ተሹመዋል።

ኳርትዝ አቶ ሳሙኤልን በስልክ አግኝቶ ስለ ፕሮጀክቱ ጥያቄ ቢያቀርብላቸውም ስለ ጉዳዩ ለመነጋገር ፍቃደኛ እንዳልሆኑ ገልፀው ስልኩን ዘግተውታል። በግሪንኮምና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል በተደረገው የፊርማ ስነስርአት ላይ ከቀሞው የማዕድንና ነዳጅ ሚንስትር አቶ ሳሙኤል አጠገብ በስፍራው የነበሩት ዶ/ር ቀፀላ ታደሰ በወቅቱ በሚንስቴር መስርያቤቱ የነዳጅ ፈቃድ ሰጪ ዳይሬክተር ሆነው ያገለግሉ የነበሩ ሲሆን በፊርማ ስነስርአቱ ላይ የመንግስት ሚድያዎች በተገኙበት ግሪንኮምን ሲያሞግሱ ታይተው ነበር። ኳርትዝ ዶ/ር ቀፀላንም በተመሳሳይ መልኩ ሊያናግራቸው ቢሞክርም ፈቃደኛ አልሆኑም ነበር። ዶ/ር ቀፀላ ግሪንኮም ከኢትዮጵያ መንግስት በተፈራረመ በአጭር ጊዜ ውስጥ ጡረታ እንደወጡ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

ከግሪንኮም ጋር የተገባው ውል መፍረስ

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኳርትዝ ጋዜጣ ያተመውን ዝርዝር ተከትሎ ሁለት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የማዕድንና ነዳጅ ሚንስትር ባለስልጣናት የማጣርያ ጣብያውን ለመገንባት ከግሪንኮም ጋር የገቡትን የ3.6 ቢልዮን ዶላር ውል ሊያፈርሱት እንደሆነ ገልፀዋል።፡የማዕድንና ነዳጅ ሚንስቴር ሚንስትር ዲኤታ ዶ/ር ኮዋንግ ቱትላም መስርያ ቤታቸው ውሉን ለማፍረስ ወስኗል የሚል መልዕክት እንደላኩለት ጋዜጣው በሌላኛው እትሙ ዘግቧል። የመጀመርያው ዘገባ እየተሰራ በነበረበት ወቅት ጋዜጠኞቹን ለማነጋገር ፈቃደኛ ያልነበሩት ባለስልጣናትም ዘገባው ያስከተለውን ቁጣ ተገንዝበው ይመስላል ዳግም ለማነጋገር በተደረገው ሙከራ የተሻለ ፈቃደኛነት እንደነበራቸው ኳርትዝ ይገልፃል። ሚንስትር ዲኤታ ዶ/ር ኮዋንግ ፕሮጀክቱ ለግሪንኮም ሲሰጥ በወቅቱ በሃላፊነት ላይ እንዳልነበሩ አስምረው “አንዳንዶቻችን ስለ ኩባንያው ታማኝነት ጥርጣሬ ነበረን፤ ስለዚህም መንግስት ብዙ ኪሳራ ሊያስከትል ወደሚችል ውል እንዳይገባ ሙከራ አድርገን ነበር” ይላሉ።

ዶ/ር ኮዋንግ ይቀጥላሉ “እንዳውም ከግሪንኮም ጋር የተገባው ውል ግንባታ ሳይጀመር ለአንድ አመት ያህል ጥናት በማድረግ ብቻ እንዲወሰን ቢልም ገና ስራ ሳይጀመር ቀብድ እንዲከፈላቸው በጣም ፈልገው ነበር። ስራ ከመጀመራቸው በፊት የ100 ሚልዮን ዶላር ቀብድ ሲጠይቁም እቅዳቸው ቀብዱን እንደ መነሻ ተጠቅመው በቢልዮን ዶላሮች የሚቆጠር ገንዘብ ከውጭ መበደር እንደነበር በኋላ ነው የተረዳነው። 100 ሚልዮን ዶላሩ እንዲፈቀድላቸው ከበላይ አካላት ከፍተኛ ጫና ቢደረግብንም እኛ ግን አሻፈረን ነበር ያልነው” በማለት ኩባንያው ገንዘብ ቶሎ ለመቀበል የነበረውን ፍላጎትና ምን ያህል የመንግስት ባለስልጣናት ድጋፍ እንደነበረው ያብራራሉ። ታድያ ሚንስትር ዲኤታው “የበላይ አካላት” ያሏቸውን ሰዎች ማንነት ለመግለፅ አልፈለጉም።

ስለዚህ አወዛጋቢ ጉዳይ አምባሳደር ፍፁም አረጋም ሆነ የጠቅላይ ሚንስትሩ ቢሮ ይፋዊ መግለጫ ያልሰጡ ቢሆንም አምባሳደር ፍፁም አረጋ ግን ትዊተር በተባለው የማህበራዊ ድህረ ገፅ ላይ ከኳርትዝ ጋዜጠኛ ዘካርያስ ዘላለም ጋር አንድ ሁለት ሲባባሉ ተስተውለው ነበር። ለመሆኑ የኢትዮጵያ መንግስት ስንት ፕሮጀክቶችን ለሌሎች ግሩንኮሞች አሳልፎ ሰጥቶ ይሆን?

 

 

 

- Advertisement -

8 COMMENTS

  1. Another form of corruption. The PM in his address to the parliament in second half of 2020 said that no one can ask him about the financial procedure of Sheger Beautifying or the Parking construction at Meskel Square.

  2. መልካም እስኪ እኛም ደግሞ የናንተን ዜና ለማመን የመረጃ ምንጫችሁን አድራሻዎች አጋሩን። በዘገባው ላይ የመረጃችሁ አብዛኛው ምንጭ ጋዜጠኛ ዘካርያስ ዘላለም ለ ኩአርትዝ መፅሄት ያቀረበው ዘገባ ነው።
    ማነው ዘካርያስ ዘላለም? ፕሮፋይሉን ማወቅ እንድንችል የሶሻል ሚድያ(ትዊተር)አድራሻውን አጋሩን።
    ለማንኛውም እናመሰግናለን።

  3. I am no longer positive the place you are getting your information, but good topic. I needs to spend some time studying more or figuring out more. Thanks for fantastic info I used to be searching for this information for my mission.

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisement -

Latest News

ሰበር ዜና – ዛሬ ረፋድ ላይ አዲግራት ከተማ በትግራይ ሰራዊት እጅ ወድቃለች

ባለፉት አራት ቀናት ዘመቻ አሉላ አባነጋ በሚል ፀረ ማጥቃት የጀመረው በህወሃት የሚመራው የትግራይ ሰራዊት በርካታ ከተሞችን መቆጣጠሩን ከስፍራው የደረሰን...

“የትግራይን ሕዝብ እናጠፋዋለን ሲሉ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ቃል በቃል ነግረውኛል” የአውሮፓ ሕብረት ልዩ መልዕክተኛ

ባለፉት 6 ወራት ውስጥ ሁለት ጊዜ ወደ አዲስ አበባ ተጉዘው የነበሩት የፊንላንዱ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ፔካ ሃቪስቶ በትላንትናው እለት አስደንጋጭ የሆነ ንግግር በአውሮፓ ሕብረት...

የኢትዮጵያ መንግስት ሃሰተኛ መረጃ ሲያሰራጭባቸው የነበሩ ከመቶ በላይ ገፆችን ዘግቻለው ሲል ፌስቡክ አስታወቀ

የማህበራዊ ድህረገፁ ፌስቡክ በትላንትናው እለት ባወጣው ዝርዝር ሪፖርት ከመቶ በላይ የሆኑ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ንክኪ ያላቸው ገፆችን እንደዘጋ አስታወቀ። ፌስቡክ ባደረገው ውስጣዊ ምርመራ እነዚህ...

“ዳቦ ከጠፋ ለምን ኬክ አይበሉም?” አዲስ አበቤነትና የኢትዮጵያውያን ሰቆቃ

እንደ ኢትዮጵያውያን አቆጣጠር በ1965 ዓ.ም በወሎ ስለተከሰተው አስከፊ ረሃብ መረጃ የደረሰው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምናልባት አዲስ አበባ ላይ በቂ ግንዛቤ ላይኖር ይችላል በሚል ከኒውዮርክ...

ቢሮ እንኳን ሳይኖረው የ3.6 ቢልዮን ዶላር ፕሮጀክት የወሰደው የአሜሪካ ኩባንያና የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ትብብር

ባሳለፍነው ታህሳስ ተቀማጭነቱን በኒውዮርክ ከተማ ባደረገ አንድ ክዋርትዝ የተሰኘ የኢንተርኔት ጋዜጣ ላይ የታተመው ፅሁፍ የኢትዮጵያን መንግስት አንገት ያስደፋና በአንዳንድ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ቁጣን ያጫረ ነበር።...
- Advertisement -

More Articles Like This

- Advertisement -