የአርቲስት ሃጫሉን መገደል ተከትሎ ከተቃዋሚ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች ጋር አብሮ የታሰረው ኬንያዊው ጋዜጠኛ ኮሊንስ ጁማ ከእስር እንዲፈታ የኬንያ መንግስት ለኢትዮጵያው የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በፃፈው ደብዳቤ ጠየቀ። ጋዜጠኛ ያሲን ለዓመታት የኦነግ እንቅስቃሴን እየተከታተለ ሲዘግብ የቆየ ሲሆን እስከ ታሰረበት ቀን ድረስም በጋዜጠኝነት ስራ ላይ ተሰማርቶ በኢትዮጵያ እየስራ ነበር። ያሲን ጁማ በመባል ይጠራ እንጂ ትክክለኛና ሕጋዊ ስሙ ኮሊንስ ጁማ የሆነው ጋዜጠኛ ሰኔ 26 ቀን በቁጥጥር ስር ሲውል በኦፌኮ አባል በሆኑት አቶ ጀዋር መሃመድ መኖርያ ቤት የነበረ ሲሆን እስካሁን 46 ቀናትን በእስር አሳልፏል።
የኬንያ መንግስት በፃፈው ደብዳቤም ጋዜጠኛ ኮሊንስ ጁማ ፍርድ ቤት በ3ሺ ብር ዋስ እንዲለቀቅ ወስኖበት ገንዘቡን የከፈለ ቢሆንም ፖሊስ ግን ሊለቀው ፍቃደኛ እንዳልሆነና የፍርድ ቤት ትእዛዙም መከበር እንዳለበት ይጠይቃል። በእስር ቤት ውስጥ በኮቪድ 19 ቫይረስ ከተያዙት እስረኞች አንዱ የሆነው ኮሊንስ በአሁኑ ወቅት በሶስተኛ ፖሊስ ጣብያ ለይቶ ማቆያ ውስጥ ሲሆን የጤናው ጉዳይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ነው ሲል ደብዳቤው ይገልፃል።
አመፅ ለማስነሳት ሰርተሃል የሚለውን ክስ እየተከላከሉለት ያሉት ጠበቆቹም በበኩላቸው ያለ ምንም ክፍያ ጥብቅና እንደቆሙለት የኬንያው ጋዜጣ ዴይሊ ኔሽን ዘግቧል።