Saturday, January 22, 2022

ኢኮኖሚያዊ ህልሙ በፖለቲካ ይጨናገፍ ይሆን?

ጦርነት ህልም ያለውን በመንገድ አስቀርቶ፤ መጻኢ ህልምን የቅንጦት ያደርጋል

Must Read

ሰበር ዜና – ዛሬ ረፋድ ላይ አዲግራት ከተማ በትግራይ ሰራዊት እጅ ወድቃለች

ባለፉት አራት ቀናት ዘመቻ አሉላ አባነጋ በሚል ፀረ ማጥቃት የጀመረው በህወሃት የሚመራው የትግራይ ሰራዊት በርካታ ከተሞችን መቆጣጠሩን ከስፍራው የደረሰን...

“የትግራይን ሕዝብ እናጠፋዋለን ሲሉ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ቃል በቃል ነግረውኛል” የአውሮፓ ሕብረት ልዩ መልዕክተኛ

ባለፉት 6 ወራት ውስጥ ሁለት ጊዜ ወደ አዲስ አበባ ተጉዘው የነበሩት የፊንላንዱ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ፔካ ሃቪስቶ በትላንትናው እለት...

የኢትዮጵያ መንግስት ሃሰተኛ መረጃ ሲያሰራጭባቸው የነበሩ ከመቶ በላይ ገፆችን ዘግቻለው ሲል ፌስቡክ አስታወቀ

የማህበራዊ ድህረገፁ ፌስቡክ በትላንትናው እለት ባወጣው ዝርዝር ሪፖርት ከመቶ በላይ የሆኑ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ንክኪ ያላቸው ገፆችን እንደዘጋ አስታወቀ።...

 

በ2013 እ.ኤ.አ. የአዲስ አበባ መስፋፋት የኦሮሚያ ገበሪዎችን አፈናቅሏል በሚል የተጀመረው የጸጥታ አለመረጋጋት ሰባት አመታትን አስቆጥሯል፡፡ ይህ አመጽ አሁን ያሉትን ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ ስልጣን አምጥቶ የተለያዩ ለውጦችን ቢያስመዘግብም፤ አሁንም ስሙን፤ አካባቢውን እና ምዕራፉን እየቀያየረ ቀጥሏል፡፡ የዳር አገርን ሲለበልብ የከረመው የጸጥታ ችግር የመሃሉን ህዝብ አንዴ ተስፋ እየሰጠ ሌላ ጊዜ ተስፋን እያሳጣ መረጋጋት እንደተሳነው ከርሟል፡፡

ራሄል ጌትነት ከጥቂት ሳምንታት በፊት ህይወቷ አሁን ባለው መልኩ ይቀየራል ብላ አልገመተችም ነበር፡፡ ራሄል የዩኒቨርስቲ ትምህርቷ ሳይሳካ በመቅረቱ ወደትውልድ ከተማዋ አዲስ አበባ በመመለስ አንዲት ኪዮስክ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ከፍታ የውበት መጠበቂያ ቁሳቁሶችን በመሸጥ መተዳደር ከጀመረች ውላ አድራለች፡፡ በዚህ ስራዋ ላይ ከተዋወቀችውና ከሁለት አመታት በላይ እጮኛዋ ከነበረው ፍቅረኛዋ ጋር አብረው ሲኖሩ የነበረ ቢሆንም እንዳቅማቸው ትንሽ የምሳ ፕሮግራም በማዘጋጀት ቤተሰቦቻቸውን ለማስተዋወቅ ለህዳር አጋማሽ ቀጠሮም ተይዞ ነበር፡፡

እድሜዬን ሙሉ እናቴን ከስልክ እና ከአሸንዳ በዐል ውጪ አይቻትም አናግሪያትም አላውቅም ትላለች፡፡ አሸንዳም ከቅርብ አመታት ወዲህ ነው መሄድ የጀመርኩት፡፡ ለረጅም ጊዜ ስለእናቴ የነበረኝ ትውስታ በጣም ውስን ሆኖ ነበር የኖርኩት፡፡

ትላለች ኢትዮኖሚክስ በፌስቡክ ባደረገላት ቃለመጠይቅ፡፡

ራሄል ትግራይ የምትገኝ እናቷን ወደ አዲስ አበባ መጥታ የቤተሰብ ትውውቅ ምሳ ለማረግ የነበራት እቅድ መልሳ እንድታስብበት ያደረጋትን መርዶ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጥቅምት 24/ 2013 ዓ/ም ይዘው ብቅ አሉ፡፡ ጠቅላዩ መቀሌ በሚገኘው የመከላከያ ሰሜን እዝ ላይ የትግራይ ክልልን የሚያስተዳድረው ህወሃት ጥቃት ማድረሱን እና እሳቸውም በአጸፋው መከላከያ ምላሽ እንዲሰጥ ማዘዛቸውን ለኢትዮጲያውያን አረዱ፡፡

አሁን አይደለምና የቤተሰብ ትውውቅ እናቴ እራሷ በህይወት መኖሯን እና አለመኖሯን አላውቅም፡፡ እኔ መሄድ አልችል፤ እሷ መምጣት አትችል፡፡ ድምጽዋን እንኳን መስማት አልቻልኩም፡፡

ትላለች ራሄል፤ በፌደራል መንግስትና በህወሃት መካከል በዝግ እየተካሄደ ባለው ወታደራዊ ግብግብ ሁሉም የመገናኛ ዘዴዎች የተቋረጡ በመሆኑ የፌደራል መንግስቱን እያማረረች፡፡ ለራሄል ምሬት የሆነው ዜና ለሌሎች ደግሞ ህግን የማስከበር እርምጃ ሆኗል፡፡ ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ በማህበራዊ ድህረ ገጹ የፌደራል መንግስት እርምጃውን በመውሰዱ ሳይሆን እስካሁን ሳይወስድ በመዘግየቱ ሊጠየቅ ይገባል የሚል እንድምታ ያለው ጽሁፍ አሰራጭቷል፡፡ ይህ ስሜት ለኮሌጅ የቋንቋ መምህር ለሆነው አክሊሉ በቀለም ተመሳሳይ ነው፡፡

ለ27 አመታት ሲደረግ የነበረውን እስር፤ ከአገር ማባረር፤ ግድያ እና ተቋማትን በጥቂት ግለሰቦች ስር መቆጣጠር እና ዝርፊያ ሁሉ ይቅር በሉ ተብለን ይቅር ብለናል፡፡ የመከላከያ ልጆቻችንን በተኙበት ማጥቃት ግን የለየለት አሸባሪነት ነው፡፡

ይላል አክሊሉ ከኢትዮኖሚክስ ጋር ባደረገው አጭር ውይይት፡፡

ክስተቱ በዜጎች እና በአገር ላይ ስለሚኖረው አሉታዊ ተጽዕኖ ግን ተናጋሪ አያሻም፡፡ ለጊዜው የአለም አቀፉን ማህበረሰብ ያሳሰበው ክስተቱ በአካባቢው ላይ የሚኖረው የጸጥታ ተጽዕኖ ነው የሚመስለው፡፡ ከእንግሊዝ፤ ጀርመንና አሜሪካ፤ ከአውሮፓ ህብረት እስከ አፍሪካ ህብረት ግብግቡ በፍጥነት ቆሞ ወደ ድርድር እንዲኬድ ሲማጸኑ ቆይተዋል፡፡ እንደነዚህ አካላት እይታ ዋናው አደጋ የምስራቅ አፍሪካ ጸጥታ ነው፡፡ ጠቅላዩ ክስተቱ ምስራቅ አፍሪካን አያሰጋም፤ ዘመቻው ውስን፤ የተመጠነና በአጭር ጊዜ የሚጠናቀቅ ነው ሲሉ የአለም አቀፉ ማህበረሰብን ሙግት ጆሮ ዳባ ልበስ ያሉት ይመስላሉ፡፡

ጦርነትም ይሁን ህግን የማስከበር እርምጃ፤ በክስተቱ ምክኒያት የታገተው የዜጎች ህልም ብቻ አይደለም፡፡ በትግራይ እና በፉደራል መንግስቱ መካከል በተጀመረው ወታደራዊ ግብግብ ከሌሎች የጸጥታ ሰንኮፋዎች ጋር ተደምረው የጠቅላይ ሚኒሰትሩን መንግስት ኢኮኖሚያዊ ህልም በአጭር እንዳያስቀረውም ያሰጋል፡፡

የኢትዮጲያ መጻይ ኢኮኖሚ ጠቅላዩ እንዳለሙት

ምንም አንኳን የአገሪቱ ፖለቲከኞች ፊት ለፊት በሚታየው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ተጠምደው እምብዛም ሲከራከሩበት ባይታዩም፤ ጠቅላዩ በቀጣይ አገሪቱን ሊወስዱበት ስላሰቡበት መንገድ ፍንጭ ሰጭ የሚሆኑ ውሳኔዎችን ሲያሳልፉ ቆይተዋል፡፡ መንበራቸውን በያዙ ገና በማለዳው የኢትዮጲያ አየር መንገድ ድርጅት ካለበት የእዳ ጫና አኳያ መሸጡ ያዋጣል ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ይሄኛው ሃሳብ የኢትዮጲያ አየር መንገድ ከአየር መንገድነቱ የዘለለ ዋጋ በኢትዮጲያውያን ዘንድ ስላለው በተነሳባቸው ተቃውሞ ወደኋላ ቢያፈገፍጉም የአለም ገበያው ውስጥ ዘው ብለው መግባት ስለመፈለጋቸው ግን ሌሎች ማስረጃዎችን ማግኘት ይቻላል፡፡

ከነዚህ ፍንጮች አንዱ የኢትዮ ቴሌኮምን 40 በመቶ ድርሻ ለአገር ውስጥ እና ለውጭ ባለሃብቶች ለመሸጥ የተወሰነው ውሳኔ ነው፡፡ ምንም እንኳን እንደ የኢትዮጲያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)፣ ህወሃትና ኦፌኮ ባሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከተሰነዘረው ወቀሳ የመሸጫ ጊዜውን ቢያራዝሙትም፤ የሽያጩ ጉዳይ ግን ያለቀለት እና በ2013 እ.ኢ.አ. እንዲጠናቀቅ አቅጣጫ የተቀመጠለት ነው፡፡ ጠቅላዩ በመጡ ሰሞን የልማት ባንክ የብድር ገንዘብን የግለሰቦች መጫወቻ በመሆናቸው ውጤታማ ሊሆኑ አልቻሉም የተባሉት የስኳር ፋብሪካዎችም ለሽያጭ ዝግጁ ሆነዋል፡፡

የአክሲዮን ድርሻ ሽያጭ ገበያ ለማስጀመር ያለመው የማዕከል ግንባታም እንደተጀመረ የብሔራዊ ባንክ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ከጥቂት ጊዜ ወዲህም የውጪ ምንዛሬ በገበያው እንዲወሰን፤ በእስልምና ህግ መሰረት ወለድ የለሽ ወይም ሀላል ባንኮች እንዲቋቋሙ፤ ጥቃቅን እና አነስተኛ የብድር ተቋማት ወደ ባንክነት እንዲያድጉ፤ የዳያስፖራው ማህበረሰብ በውጪ ምንዛሬ አካውንት መክፈት እንዲችል እና በፋይናንስ ዘርፉም በኢንቨስተርነት በቀጥታ መሳተፍ እንዲችል የሚፈቅዱ የህግ ማሻሻያዎች ተደርገዋል ወይም ለመተግበር በሂደት ላይ ይገኛሉ፡፡ አነዚህ ማሻሻያዎች ጠቅላዩ እና አማካሪዎቻቸው መንግስት በኢኮኖሚው ውስጥ ያለው አድራጊ ፈጣሪነት እየቀነሰ፤ ኢኮኖሚውም በአገር ውስጥ አና ከአገር ውጪ ባለው ገበያ እጣ ፋንታው እንዲወሰን መፈለጋቸውን አመላካቾች ናቸው፡፡

የኢትዮጲያ ኢኮኖሚ በገበያ መር ስርዐት- በጨረፍታ 

የኢትዮጲያ መንግስት በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በ2014 እ.ኤ.አ. ለአለም ገበያ ያቀረበው የቦንድ ሰነድ ለ10 አመት ቆይቶ በ2024 እ.ኤ.አ. ይጠናቀቃል ተብሎ የታቀደ ነው፡፡ የሰነዱ ሽያጭ መንግስት የአንድ ቢሊዮን ዶላር ብድር ያስገኝልኛል ብሎ ያቀደበትም ነበር፡፡ ኢትዮጲያ በቦንድ ሰነድ የሚገኝ ብድር በአገር ውስጥ በፌደራል እና በክልል ደረጃ ተጠቃሚ ብትሆንም በአለም አቀፍ ደረጃ ግን እንዲህ አይነቱ ይህ ነው የሚባል ብድር የለባቸውም ከሚባሉ የአፍሪካ አገራት መካከል አንዷ ናት ይላል ሴፍየስ የተባለ የጥናትና ትንተና ተቋም ስለቦንዱ በ2019 እ.ኤ.አ. ባቀረበው ትንተና ላይ፡፡

አገራት የተለያዩ የኢንቨስትመንት ፍላጎቶቻቸውን ለማሟላት የሚያስችል የብድር አቅርቦትን ለማግኘት በአለም አቀፍ ገበያ ላይ የሚሸጡ የቦንድ ሰነድ ያቀርባሉ፡፡ እነዚህ ሰነዶች መንግስታት ለትላልቅ ፕሮጀክቶቻቸው የገንዘብ አቅርቦት በብድር መልክ ለማግኘት ለገበያ የሚያቀርቧቸው ናቸው፡፡ በቀላል ቋንቋ መንግስታት ከግለሰቦች ብድርን ለማግኘት ለሽያጭ የሚያቀርቧቸው ሰነዶች ናቸው፡፡

ሰነድ ገዢዎች በመንግስታት ለሚሸጡ የቦንድ ሰነዶች ከሞላ ጎደል ጥሩ ፍላጎት አላቸው፡፡ ለግለሰብ ኢንቨስተሮች አሊያም ለድርጅቶች ከማበደር ለመንግስታት ማበደር የአበዳሪው ገንዘብ ስለመመለሱ ተጨማሪ ማስተማመኛ ይሰጣል፡፡ ሌላኛው ማስተማመኛ ተበዳሪ አሊያም ሰነድ ሻጭ መንግስታት በብድር ታሪካቸው መሰረት በግምገማ የሚሰጣቸው ነጥብ ነው፡፡ የብድር ገምጋሚ ገለልተኛ ድርጅቶች የተበዳሪውን በጊዜው ብድር የመመለስ ታሪክ ገምግመው ነጥብ ይሰጣሉ፡፡ ሰነድ ገዥዎች በዚህ ግምገማ ጥሩ ነጥብ ላላቸው አገራት ለማበደር ወይንም ሰነዶቻቸውን ለመግዛት የተሻለ ፍላጎት ሊኖራቸው እንደሚችል ይገመታል፡፡

የኢትዮጲያ የዩሮ ቦንድ በአለም አቀፍ ገበያው ላይ የነበረው አፈጻጸም ከሞላ ጎደል በተረጋጋ ሁኔታ ላይ እንደቆየ የሲፊዩስ ትንተና ያሳያል፡፡ ሰነዱን አሳልፈው በመሸጥ ለቦንዱ ባለቤቶች ሲያስገኝ የነበረው ገቢ በ2018 እ.ኤ.አ. ቀንሶ 5.47% የነበረ ሲሆን በ2016 እ.ኤ.አ. ደግሞ እጅግ ከፍ ብሎ 9.68% እነደነበረ የተደረገው ትንተና ያሳያል፡፡ ከ2019 እ.ኤ.አ. በፊት በነበሩት የኢትዮጲያ የቦንድ ሽያጭ ለአበዳሪዎቹ በየአመቱ በአማካኝ የ6.9 በመቶ ገቢን ሲያስገኝ ቆይቷል፡፡

ኢትዮጲያ በብድር ገምጋሚ ተቋማት ከዚህ በፊት በአለም አቀፍ የሰነድ ሽያጭ የመጣ ብድር ስለሌለባት “B” ወይም ጥሩ ሊባል የሚችል ውጤት ተሰጥቷታል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በውጪው ንግድ ላይ እየጠነከረ የመጣው የአገልግሎት ዘርፍ፤ ከዳይስፖራው ወደ አገር ቤት የሚላከው ገንዘብ እድገት እና ከቅርብ አመታት በፊት በመጣው ለውጥ ምክኒያት የአጋር አገራት ቀጥተኛ ድጋፍ እና የብድር አቅረቦትም ጨምሯል፡፡ በነዚህና በሌሎች ምክኒያቶች የኢትዮጲያ የሰነድ ዋጋ እየጨመረ እንደሚመጣ ተገምቶ የነበረ ቢሆንም በባበለፉት ጥቂት ቀናት ግን እየሆነ ያለው ይሄ አይመስልም፡፡

ባለፉት 10 ቀናት በዓለም ገበያ ላይ እየተገበያየ ያለው የኢትዮጵያ ቦንድ ዋጋው እየረከሰ መጥቷል

ከጥቅምት 25/ 2013 ዓ/ም እ.ኢ.አ. ጀምሮ ባሉት ቀናት የአገሪቱ ዬሮ ቦንድ ሰነድ ሽያጭ ዋጋው እየቀነሰ እንደመጣ የሚያሳዩ ምልክቶች አሉ፡፡ በግልጽ ቋንቋ የኢትዮጲያን የቦንድ ሰነድ ገዝቼ ብይዘው ላተርፍበት እችላለው ለሚለው መላምት ያለው የይሆናል እድል እየጠበበ ነው እንደማለት ነው፡፡ እውነት ነው፤ ጠባብ የሆነ የአትራፊነት እድል ያላቸውን ነገሮች በርካሽ መግዛት ልምዱ ላላቸው ደፋር ኢንቨስተሮች ዜናው ጥሩ ሊሆን ይችላል፡፡ ይሀ ግን ለደፋር ኢንቨስተሮች ጊዚያዊ ጥቅም ከማምጣቱ በዘለለ አገሪቱ ብድሯን የምትከፍል ታማኝ ተበዳሪ መሆኗን ለማመላከት ምንም ድርሻ አይኖረውም፡፡

በፌደራል መንግስቱና በህውሃት መካከል እየቀጠለ ያለው ወታደራዊ ግብግብ ለዚህ አመኔታ ማጣት ላለው ቀጥተኛ አስተዋጽኦ ማስረጃ ማግኘት አይቻልም፡፡ ሆኖም ወታደራዊም ሆነ ፖለቲካዊ ግብግብ፤ አሊያም ሌሎች ቀላል የሚመስሉ የመንግስት ውሳኔዎችን ጨምሮ በገበያ የሚወሰን ኢኮኖሚ ላይ ስላላቸው ቀጥተኛ ተጽዕኖ ጥናቶችን ማግኘት ይቻላል፡፡ የሴፍየስ ትንተና አገሪቱ ውስጥ ያለው የፖለቲካ አለመግባባት፤ የቦንድ ሰነዱ ዋጋ የሚገዛው ጠፍቶ እንዳይቀንስ እንዲሁም ከቅርብ አመታት በኋላ ካስመዘገበቻቸው ለውጦችም ተጠቃሚ እንዳትሆን እንቅፋት ሊሆንባት እንደሚችል በ2019 እ.ኤ.አ. ትንበያውን አስቀምጦ ነበር፡

ክርስቶፍ ሞዜር በ2007 እ.ኤ.አ. ጥናቱ የ1981 እ.ኤ.አ. የተደረገን ሌላ ጥናት ጠቅሶ የፖለቲካ አደጋዎች ከአገር ውጪ በሚሸጡ የቦንድ ሰነዶች ላይ ቀጥተኛ የሆነ ተጽዕኖ አላቸው ይላል፡፡ ክርስቶፍ በጥናቱ አገራት ብድርን የመክፈል ፍላጎት እና ብድርን የመክፈል አቅም ተለያይተው መታየት ያለባቸው ጉዳዮች እንደሆኑ ማስረጃዎች አሉ ይላል፡፡ ብድርን የመክፈል አቅም ቢኖርም ብድርን የመክፈል ፍላጎት ግን ፖለቲካዊ ውሳኔ መሆኑን ያነሳል፡፡ ይህን ፖለቲካዊ ውሳኔ በአገር ውስጥ የሚፈታተኑ ሁኔታዎች መኖራቸው በአለም አቀፍ ገበያ ውስጥ ለሚኖረው አፈጻጸም ቀጥተኛ ድርሻ ይኖራቸዋል ይላል፡፡

ሞሃመድ ቡዋዚዝ በታህሳስ ወር በ2010 እ.ኤ.አ እራሱን በጋዝ አርከፍክፎ በማቃጠል አመርቅዞ የሰነበተውን ፖለቲካዊ ቅያሜ ቀስቅሶ በቱኒዚያና በአረቡ አለም በፖለቲካ ንቅናቄ መልክ ለኮሰ፡፡ ይህ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በቱኒዚያ ኢኮኖሚ ላይ ጥሎ ያለፈውን ጥቁር ጠባሳ በ2018 እ.ኤ.አ. ያጠናው ሰላማ ዛይኒ የፖለቲካ ግብግብ ገበያ መር የሆነ ኢኮኖሚ ላይ ስላለው ተጽዕኖ የሚስማማ ይመስላል፡፡ የ2011 እ.ኤ.አ. የፖለቲካ አብዮት ተከትሎ የቱኒዚያ የአክሲዮን ድርሻ ገበያ በ21 በመቶ ቀንሶ እንደነበር፤ አብዮቱን ተከትሎ የታዩት የጸጥታ ችግሮችም አገሪቱን ለዘገምተኛ ኢኮኖሚያዊ እድገት ከመዳረጉም በላይ አገሪቱ የአለም አቀፍ ኢንቨስተሮችን ፍላጎት እንዳትማርክ አድርጓታል ይላል ሰላማ፡፡

በባለፉት ጥቂት አመታት በአለም ላይ የታዩ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ እውነታዎች በካፒታል ገበያው ላይ ከፍተና ተጽዕኖ እንዳላቸው ያሳዩ ሆነው አልፈዋል የሚሉት ደግሞ ዶ/ር ማውሪቺዮ ቫርጋስ እና ፍሎሪያን ሶመር ናቸው፡፡ በግንቦት 2015 እ.ኤ.አ.  ባቀረቡት ጥናት የአረብ አለሙ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ በፖለቲካ እና በኢኮኖሚው ዘንድ ያለን ግንኙነት ምንያክል ጠንቃራ እንደሆነ የተማርንበት ነው ይላል፡፡ እንዳውም ከነዚህ አመታት በኋላ ኢንቨስተሮች ገንዘባቸውን ከማውጣታቸው በፊት ከፋይናንስ ዘርፍ አማካሪዎች በተጨማሪ የፖለቲካ ሁኔታ ተንታኞችም እየፈለጉ ይገኛሉ ይላሉ፡፡

ኢዜማ መንግስት የኢትዮትሌኮም 40 በመቶ ድርሻ ለመሸጥ ስለመወሰኑ በነሃሴ 2012 እ.ኢ.አ. ባዘጋጀው ውይይት የገበያ መር ኢኮኖሚ ውሳኔ ኢኮኖሚያዊ ብቻ አለመሆኑን ያሳየ ነበር፡፡ የፓርቲው መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በውይይቱ መጨረሻ ባደረጉት ንግግር ድርሻውን በዚህ ጊዜ መሸጡ ኪሳራ ነው ሲሉ ተደምጠው ነበር፡፡ የኢኮኖሚክስ ፕሮፌሰሩ ምክኒያታቸውን ሲያስረዱም፤ የኮሮና በሽታ አለም ላይ ባመጣው ሁኔታ የኢንቨስተሮች ፍላጎት በመቀነሱ በርካሽ ዋጋ እንዳንሸጠው ያሰጋኛል የሚል ነበር፡፡ ይህም በገበያ መር ኢኮኖሚ ውጤታማ መሆን ኢኮኖሚያዊ ውሳኔ ብቻ ሳይሆን ፖለቲካዊም፤ ማህበራዊም ከመሆኑ ባሻገር አስተማማኝ ጸጥታን እና ምቹ ሁኔታን አንደሚፈልግ ማሳያ ነው፡፡

እጣ ፋንታው በገበያው የሚወሰን ኢኮኖሚን መገንባት ጠንካራና ዘመን ተሻጋሪ መተማመንን የሚሰጡ ፖለቲካዊ፤ ማህበራዊና ህጋዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን ይጠይቃል፡፡ የፖለቲካ ግብግብን በጊዜ እና በቅጡ ማስተዳደር ያቃተው መንግስት ለወጠነው “ብልጽግና” ስልጣን ባለው የፖለቲካ ፓርቲ አሊያም በሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ቅዠት ሆኖ ይቀር ወይ የሚል ጥያቄ እንድናነሳ አስገዳጅ ይሆናል፡፡ ዜጎች በመንግስት የታለመላቸው “ብልጽግና” ቢዘገይ ወይ ቢቀር እንኳን በግል ጥረታቸው የገነቡት ህልማቸው የቅንጦት እንዳይሆንባቸው መጣር ሁሉም ተዋናይ ሊያሟሉት የሚገባ ትንሹ መስፈርት ነው፡፡ ለራሄል እና ለእጮኛዋ ለጊዜው የቤተሰብ ትውውቅ ማካሄድ የቅንጦት ሆኖባቸዋል፡፡ ለጊዜው በግምት እና በቁዘማ በትንሿ ሱቅ ውስጥ ማሳለፍ ግዴታ ሆኗል፡፡

አረ ሁሉም ነገር ቀርቶብኝ በመጣችና ከኔው ጋር እዚሁ በኖረች፡፡

ትላለች ራሄል የቤተሰብ ትውውቁ በአሁኑ ወቅት ቢቀርም ቅር እንደማይላት ስታብራራ፡፡ እጣ ፋንታው በገበያው በሚወሰንበት ኢኮኖሚ ይዞት በሚመጣው የፉክክር አለም ውስጥ ያልተራመደ ህይወት ወደኋላ እንደሄደ ይቆጠራል፡፡ የጸጥታ ችግርና የፖለቲካ ግብግብ ዜጎችን ከትዳር፤ አገርን ከአም አቀፍ ተወዳዳሪነት ማዘግየቱን ባህል አድርጎ ከተያያዘው፤ ምህረት የለሽ የገበያው ዳኝነት ሲታከልበት ውድድሩ ንበረትን በርካሽ ከመሸጥ የዘለለ ውጤት ሳያመጣ እንዳይቀር ያሰጋል፡፡

- Advertisement -

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisement -

Latest News

ሰበር ዜና – ዛሬ ረፋድ ላይ አዲግራት ከተማ በትግራይ ሰራዊት እጅ ወድቃለች

ባለፉት አራት ቀናት ዘመቻ አሉላ አባነጋ በሚል ፀረ ማጥቃት የጀመረው በህወሃት የሚመራው የትግራይ ሰራዊት በርካታ ከተሞችን መቆጣጠሩን ከስፍራው የደረሰን...

“የትግራይን ሕዝብ እናጠፋዋለን ሲሉ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ቃል በቃል ነግረውኛል” የአውሮፓ ሕብረት ልዩ መልዕክተኛ

ባለፉት 6 ወራት ውስጥ ሁለት ጊዜ ወደ አዲስ አበባ ተጉዘው የነበሩት የፊንላንዱ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ፔካ ሃቪስቶ በትላንትናው እለት አስደንጋጭ የሆነ ንግግር በአውሮፓ ሕብረት...

የኢትዮጵያ መንግስት ሃሰተኛ መረጃ ሲያሰራጭባቸው የነበሩ ከመቶ በላይ ገፆችን ዘግቻለው ሲል ፌስቡክ አስታወቀ

የማህበራዊ ድህረገፁ ፌስቡክ በትላንትናው እለት ባወጣው ዝርዝር ሪፖርት ከመቶ በላይ የሆኑ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ንክኪ ያላቸው ገፆችን እንደዘጋ አስታወቀ። ፌስቡክ ባደረገው ውስጣዊ ምርመራ እነዚህ...

“ዳቦ ከጠፋ ለምን ኬክ አይበሉም?” አዲስ አበቤነትና የኢትዮጵያውያን ሰቆቃ

እንደ ኢትዮጵያውያን አቆጣጠር በ1965 ዓ.ም በወሎ ስለተከሰተው አስከፊ ረሃብ መረጃ የደረሰው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምናልባት አዲስ አበባ ላይ በቂ ግንዛቤ ላይኖር ይችላል በሚል ከኒውዮርክ...

ቢሮ እንኳን ሳይኖረው የ3.6 ቢልዮን ዶላር ፕሮጀክት የወሰደው የአሜሪካ ኩባንያና የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ትብብር

ባሳለፍነው ታህሳስ ተቀማጭነቱን በኒውዮርክ ከተማ ባደረገ አንድ ክዋርትዝ የተሰኘ የኢንተርኔት ጋዜጣ ላይ የታተመው ፅሁፍ የኢትዮጵያን መንግስት አንገት ያስደፋና በአንዳንድ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ቁጣን ያጫረ ነበር።...
- Advertisement -

More Articles Like This

- Advertisement -