Saturday, January 22, 2022

ኤርትራ፤ ከተራራው ጀርባ ጠልቃ የቀረችው ሰሜናዊት ኮኮብ

ራስን ማስተዳደር እራስን ወደመቻል መሸጋገር ለምን ተሳነው?

Must Read

ሰበር ዜና – ዛሬ ረፋድ ላይ አዲግራት ከተማ በትግራይ ሰራዊት እጅ ወድቃለች

ባለፉት አራት ቀናት ዘመቻ አሉላ አባነጋ በሚል ፀረ ማጥቃት የጀመረው በህወሃት የሚመራው የትግራይ ሰራዊት በርካታ ከተሞችን መቆጣጠሩን ከስፍራው የደረሰን...

“የትግራይን ሕዝብ እናጠፋዋለን ሲሉ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ቃል በቃል ነግረውኛል” የአውሮፓ ሕብረት ልዩ መልዕክተኛ

ባለፉት 6 ወራት ውስጥ ሁለት ጊዜ ወደ አዲስ አበባ ተጉዘው የነበሩት የፊንላንዱ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ፔካ ሃቪስቶ በትላንትናው እለት...

የኢትዮጵያ መንግስት ሃሰተኛ መረጃ ሲያሰራጭባቸው የነበሩ ከመቶ በላይ ገፆችን ዘግቻለው ሲል ፌስቡክ አስታወቀ

የማህበራዊ ድህረገፁ ፌስቡክ በትላንትናው እለት ባወጣው ዝርዝር ሪፖርት ከመቶ በላይ የሆኑ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ንክኪ ያላቸው ገፆችን እንደዘጋ አስታወቀ።...

 

ኤርትራ ከባህር በሯ በዘለለ፤ ምድሯ ጥቅም የለውም የሚለው አስተሳሰብ ከኢትዮጲያ ጋር ፍቺ ሳትፈጽም በፊት ገዢ ሃሳብ ሆኖ ነው የኖረው፡፡ በደርግ ጊዜ የኢትዮጲያ ፕሬዝዳንት የነበሩት ኮ/ል መንግሰቱ ሃይለማሪያም ከሻዕቢያ እና ህወሃት ወታደሮች ጋር ሲያደርጉት የነበረው የረዘመ ጦርነት አማሯቸው የተናገሩትም ይህ ገዢ አስተሳሰብ የነበረ ስለመሆኑ አንደኛው አመላካች ነው፡፡

ወርቅ አይወጣበት፤ ዳይመንድ አይታረስበት፤ ይሄ ፋንድያ የሆነ መሬት…

ብለው ነበር ፕሬዝዳንቱ በአስቂነታቸው ከሚታወቁት ንግግሮቻቸው መካከል በአንደኛው ላይ፡፡ ይህ ለዘለዐለም የተደረገ የሚመስለው የሻዕቢያ የትጥቅ ትግል፤ ኤርትራ ከአዲስ አበባ በሚሾሙ ሹማምነት መተዳደሯን በማስቀረት ለባላባቶች እና ለልጆቻቸው ብቻ የተወሰነውን ድሎት ለተራውም ዜጋ ማካፈል በሚል የተጀመረ ነበር፡፡ የሻቢያ ትግል ያስቀመጠውን እራስን በራስ የማስተዳደር እስከመገንጠል አላማ አሳክቶ፤ ኤርትራ ከኢትዮጲያ ተለይታ የራሷን ጎጆ ከመሰረተች ድፍን ሶስት አስርተ አመታትን ሊያስቆጥር ጥቂት ወራት ብቻ ይቀሩታል፡፡ እራስ በራስ ማስተዳደሩ የተሳካላቸው የኤርትራ ሹማምንት ብዙም ሳይቆዩ በቀድሞ የትግል አጋሮቻቸው ህውሃቶች፤ ከምትዘወረው ኢትዮጲያ ጋር በ1991 ዓ/ም እ.ኢ.አ. ደም ሊቃቡ ተቃጠሩ፡፡

በአዲስ አበባ ተወልዳ ያደገችውና ቤተሰቦቿ ከኤርትራ የሆኑት ሊዲያ ተክለማሪያም (ኢትዮኖሚክስ በግለሰቧ ጥያቄ መሰረት ለደህንነቷ ሲባል ስሟን ቀይሮታል) የጦርነቱ ማስጀመሪያ ነጋሪት የተጎሰመበትን ጊዜ የትላንትን ያክል ታስታውሰዋለች፡፡

በወቅቱ አዲስ አበባ ውስጥ አብዮት ፋና በሚባል ትምህርት ቤት የ8ኛ ክፍል ተማሪ ነበርኩኝ፡፡ የኢትዮጲያ መንግስት በየትምህር ቤቱ የሚገኙ አስተማሪዎችን ጦርነት ሊጀመር መሆኑን እና ጥፋቱም የኤርትራ መንግስት እንደሆነ አስረዱ እያለ ይልካቸው ነበር ይመስለኛል፡፡ የሂሳብና የህብረተሰብ አስተማሪዎቼ፤ አኔ ወደነበርኩበት ክፍል እየመጡ ገለጻ ያደርጉልን ነበር፡፡ በወቅቱ አይደለምና እኔ ላይ ችግር ያመጣል ብዬ ላስብ ይቅርና፤ ጦርነት እራሱ ምን ማለት እንደሆነ በቅጡ የምንገነዘብ አይመስለኝም፡፡

ትላለች ሊዲያ ከአሜሪካን አገር ኢትዮኖሚክስ በፌስቡክ ባናገራት ወቅት፡፡

ነገሩ ከረረ፤ የኢትዮጲያ መንግስትም አመረረ፡፡ ኢትዮጲያ ተቀምጣችሁ የኤርትራን መንግስት በገንዘብ የምትደግፉ ግለሰቦች ጓዜን ሳትሉ፤ ቤተሰባችሁን ጠቅልላችሁ ውጡልን አለ፡፡ ለሊዲያ እና ቤተሰቧ ጦርነቱ በራቸውን አንኳኳ፡፡

እኔ ህይወቴን በሙሉ ኤርትራዊ ነኝ የሚለው ስሜት ተሰምቶኝ እንደሚያውቅ አላስታውስም፡፡ ቤተሰቦቼም ሰለእንደዚህ አይነቱ ጉዳይ ሲወያዩም ትዝ አይለኝም፤ አይደለምና የኤርትራን መንግስት በገንዘብ ሊደግፉ ይቅርና፡፡ … የሆነው ሆኖ አንድ ቀን በጥዋት የመንግስት ወታደሮች መጥተው እኔን፤ ታናሽ ወንድሜን እና ሁለቱንም ወላጆቼ ለነገ ተዘጋጅተን እንድንጠብቅ ተነገረን፡፡ ታላቅ እህቴን ጎረቤት ደብቆ፤ ትተን የሄድነውን ቤታችንን እንድታስተዳድር በሚል አስቀሯት፡፡ 

ሊዲያ ታሪኳን ለማካፈል የምትሳሳ አትመስልም፡፡ ትቀጥላለች፡-

በንጋታው ጸሃይ ሳትወጣ መኪና ላይ ተጫንን፡፡ የስምንተኛ ክፍል ብሄራዊ ፈተናን ሳልፈተን ነበር አስመራ የሄድኩት፡፡ የትምህርቱ ነገር በዛው አከተመለት፡፡ ኤርትራ ሲዖል ሆነችብኝ፡፡ ከመጀመሪያ ደረጃ በላይ ትምህርት መቀጠል የቅንጦት ነው ተባለ፡፡ ከአገር መውጣት የመጀመሪያው ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ሆነ፡፡ 

ትላለች ሊዲያ፡፡

በወቅቱ የኤርትራውያን ከኢትዮጲያ መውጣት በአዲስ አበባ ኢኮኖሚዊ እንቅስቃሴ ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ ግልጽ ብሎ ይታይም ነበር፡፡ ኤርትራውያን በወቅቱ በዋናነት የመኪና ጥገናና መለዋወጫ ንግድ ውስጥ ዋና ተዋናይ እንደነበሩ ይታወሳል፡፡ መልቀቃቸውን ተከትሎ ጋራዦች፤ የመኪና መለዋወጫ ሱቆች እና መሰል እንቅስቃሴዎች ተቀዛቅዘው ቆይተው ነበር፡፡ ጦርነቱ የአዲስ አበባን ኢኮኖሚ ለተወሰነ ጊዜ ቢያቀዘቅዝም፤ የኤርትራን መላው ኢኮኖሚ ደግሞ አግቶት ነው የኖረው፡፡

የግጭቱ ምክኒያት በሁለቱ አገራት መንግስታት መሪዎች ፖለቲካዊ ነው የሚል ሙግት ቢቀርብበትም፤ አብዛኛው ምክኒያት ኢኮኖሚያዊ እንደሆነ የሚሞግቱ ጸሃፍት አሉ፡፡ ማር ማይክልሰን በተባለ አጥኚ በ1998 እ.ኤ.አ. የቀረበ አንድ ጥናት የግጭቱን ኢኮኖሚያዊ ምክኒያቶች ይዳስሳል፡፡ ከኤርትራ ጎጆ መውጣትም በኋላ፤ ሁለቱ አገራት በጋራ አኮኖሚያዊ ስምምነት የሚመራ የኢኮኖሚ ስርዐት መገንባት ችለው ነበር፡፡ ስምምነቱ  ኢትዮጲያ የአሰብ እና የምፅዋን የባህር በሮች እንድትጠቀም እና ኤርትራም የኢትዮጲያን የገንዘብ ኖት እንድትጠቀም የፈቀደም ነበር፡፡

ስምምነቱ ወደመሬት ወርዶ ከተተገበረ ጥቂት አመታት በኋላ፤ ከግጭቱ መቀስቀስ ቀደም ብሎ፤ የኢኮኖሚ ስምምነቱ የጋራ ጥቅምን መሰረት ያደረገ አልነበረም የሚሉ ወቀሳዎች ይቀርቡበት ጀመር፡፡ ብር ኢትዮጲያ ውስጥም ኤርትራ ውስጥም ዋጋው እኩል መሆን አለበት ተብሎ ቀድሞ የተወሰነው የምንዛሬ ህግ፤ ኢትዮጲያ የኤርትራ ኢኮኖሚ ላይ ምንም ቁጥጥር ስለሌለኝ ይጎዳኛል በሚል ማጉረምረም ጀመረች፡፡ ኢትዮጲያ ውስጥ የሚኖሩ ኤርትራውያን፤ ቡና እና ወርቅን የመሳሰሉ ምርቶችን እንደዜጋ በርካሽ እየገዙ እና ወደ ኤርትራ እየላኩ ኤርትራ እንደ አገር ለውጪ ንግድ እያዋለችው ነው፤ ይህም አኔ ለውጪ ንግድ ማዋል ያለብኝን ምርት እያሳጣኝ ነው፤ ከዚያም አልፎ የኢትዮጲያ መገለጫ የሆነው ቡና በአለም አቀፍ ገበያ ላይ የኤርትራ መገለጫ ሆኗል የሚሉ ክሶች ይቀርቡ ጀመር፡፡

መሰረታዊ ምክኒያቱን እነዚህ እና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ ምክኒያቶች ያደረገው አለመግባባት፤ በድንበር መወረር ቀስቃሽነት ወደጦርነት አመራ፡፡ ጦርነቱ ሁለት አመታትን እና ከ60 ሺህ በላይ ዜጎችን ቀጥፎ፤ በአልጄሪያ አደራዳሪነት ተጠናቀቀ፡፡ የአለም መገናኛ ብዙሃን ሁለት መላጦች በማበጠሪያ የተጣሉበት ብለው የተሳለቁበት ጦርነት ከተጠናቀቀም በኋላ፤ ለኤርትራ- ጎጆ መውጣት እራስን ወደ መቻል ሳይቀየር ቆየ፡፡

ከጦርነቱ መጠናቀቅም በኋላ ኢትዮጲያ ያልታመነች ማን ይታመናል ያሉ የሚመስሉት የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ፤ የአሜሪካን እና የአውሮፓ አገራትን ጨምሮ ሌሎችም ኤምባሲዎችን ዘግተው አስመራን እንዲለቁ አዘዙ፡፡ ኢትዮጲያን ማስቀየም ያልፈልጉት የአለም አገራት፤ ኤርትራ የመሳሪያ ግዢን እንዳትፈጽም ማዕቀብ ጣሉ፡፡ በግላጭም ባይሆን የኤምባሲዎቻቸው መዘጋት ያንገበገባቸው ሃያላን፤ ከኤርትራ ጋር መነገድ ነውር እንዲሆን፤ የባለስልጣናቶቿ የባንክ አካውንት እንዳይንቀሳቀስ፤ የአለም አቀፍ በረራንም እንዳያደርጉ በሚሉ እርምጃዎች ብስጭታቸውን ገለጹ፡፡

መገንጠል፤ ራስን ለመቻልና ለኢኮኖሚ ፍትሃዊነት በር ከፋች ነው የሚል ቃል የተገባላቸው ዜጎች፤ ቃል የተገባው ሳይሆን ቢቀር፤ የቻሉት በአየር፤ ያልቻሉት በባህር መሰደዱን ተያያዙት፡፡ ህይወታቸው ሳያልፍ አውሮፓ፤ አሜሪካን አሊያም እስራኤል የደረሱትም፤ ተሳክቶላቸዋል ለማለት በማያስደፍር ደረጃ የአለም አቀፍ መገናኛ ብዙኋን የሰቆቃ ታሪክ ምሳሌ ሲደረጉ ኖሩ፡፡ ሊዲያ ምንም እንኳን የውትድርና ስልጠናውን ፤ የባህር ስደቱን ብታመልጥም አሜሪካን ያን ያክል አስደሳች እንዳልሆነችላት ትመሰክራለች፡፡

በአባቷ በኩል በተገኘ በአሜሪካን አገር ኑሮውን ያደረገ እና በሁለት እጥፍ በእድሜ ለሚበልጣት ሰው አስመራ ላይ ተዳረች፡፡ ሊዲያም ወደ አሜሪካን አገር በረረች፡፡ አሜሪካም እንኳን መጣሽልኝ እንዳላለቻት ሊዲያ ለኢትዮኖሚክስ ታብራራለች፡፡

ወጣት ነህ ተብሎ ስለሚታሰብ ወንዶች እንድትማር፤ ስራ እንድትሰራ አይፈቅዱልህም፡፡ ዝም ብሎ ልጅ መውለድ፤ ልጅ ማሳደግ፡፡ አራት ልጆች ወልጄ እነሱን ሳሳድግ ነው የኖርኩት፡፡ መማር፤ ስራ መስራት፤ እራስን መቻል የነበረኝ ህልም ሁሉ ቅዠት ሆኖ ቀረ፡፡

የማር ማይክልሰን ጥናት እንደሚያሳየው፤ ኤርትራ ከመገንጠልም በኋላ የራሷን የኢኮኖሚ አቅም አስጠንታ ወደጥቅም ከመቀየር ይልቅ በቀጥታም በተዘዋዋሪም በኢትዮጲያ ኢኮኖሚ ላይ ጥገኝነት የተጠናወተው ነበር፡፡

ኤርትራ ከስደት የተረፉ ልጆቿን እንዴት ስታስተዳድር ከረመች?

ዊኪሊክስ የተባለው ሚስጥራዊ መረጃዎችን የሚያትመው ድህረ ገጽ በመጋቢት 2007 እ.ኤ.አ. በወቅቱ በኤርትራ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት ሮናልድ ማክሚዩለን ለዋሽንግተን የጻፉትን ደብዳቤ አውጥቶ ነበር፡፡ ማክሚዩለን በደብዳቤያቸው፤ በወቅቱ የኤርትራ የውጪ ንግድ የሚመጣላት የውጪ ምንዛሬ ከ20 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደማይዘል ይገልጻሉ፡፡ አምባሳደሩ ቀጥለውም፤ ከኤርትራ ውጪ የሚገኙ ኤርትራውያን ከሚያገኙት ገቢ ሁለት በመቶ ግብር ለመንግስት አንዲከፍሉ የማስገደድ እቅድም እንዳለ ያነሳሉ፡፡ በኤርትራ ኤምባሲዎች እና በሌሎች መንገዶች የሚሰበሰበው ይህ ግብር እና እርዳታ 80 ሺህ ከሚሆኑ ኤርትራውያን ወደ 35 ሚሊዮን ዶላር እያስገኘላቸው ሳይሆን እንዳልቀረ ግምታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡

አምባሳደሩ በተመሳሳይ አመት በጻፉት ደብዳቢያቸው ላይ ደግሞ ኤርትራ ከኳታር፤ ሳውዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤመሬቶች የገንዘብ ድጋፍ ሳያገኙ እንዳልቀሩ ይገምታሉ፡፡ ኢሳያስ ከኳታር በሚላክላቸው አውሮፕላን፤ ኳታር እንደሚመላለሱና ኢሳያስን መደገፍ ክርስቲያናዊት ኢትዮጲያን መጫን ከመሰላቸው አሚሮች ዶላር እንደሚሸጎጥላቸው ያነሳሉ፡፡ ያም ሆኖ በወቅቱ የአገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ክምችት ምናልባትም ከሁለት እና ሶስት ሳምንት ገቢን ከመሸፈን ሊያልፍ የሚችል እንዳልነበር ይገምታሉ፡፡

ማክሚዩለን በ2009 እ.ኤ.አ. ደብዳቢያቸው ደግሞ የኤርትራ ኢኮኖሚ አውራ የነበሩትን ሃጎስ ገ/ሂዎትን ኮሚዩኒስት እንደሆኑ እንደጠይቅዋቸው እና “አይደለሁም፤ ከጦርነቱ በፊት የአገሪቱን የግል ዘርፍ ለማሳደግ እቅድ የነበረ ቢሆንም፤ ከጦርነቱ በኋላ ግን፤ የአገር ደህንነትና ጸጥታ ዋንኛው አላማ” እንደተደረገ ነግረውኛል ብለው እንደጻፉ ዊኪሊክስ ያስነብባል፡፡ አምባሳደሩ በኢሜይላቸው በ2010 እ.ኤ.አ. የወርቅ ምርት በመጀመር የአገሪቱንም የስርዐቱንም ህልውና ከአደጋ ለመጠበቅ የታሰበ ቢሆንም፤ ከዚህ ምርት ግን ከ2013 እ.ኤ.አ. በፊት ገቢ ሊገኝ እንደማይችል፤ የኤርትራንም ኢኮኖሚ ከውድቀት ሊታደግ የሚችል አፋጣኝ መፍትሄ ይኖራል ብለው እንደማይገምቱ ይገልጻሉ፡፡

በ2014 እ.ኤ.አ. በኖርዌይ ኦስሎ ዩኒቨርስቲ ለህግ ፋካልቲ የቀረበ አንድ ጥናት ኤርትራ ዜጎቿን ለማስተዳደር ስታደርግ ስለቆየችው ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የተወሰኑትን ያነሳል፡፡ ከነዚህ እንቅስቃሴዎች መካከል የተቀናጀ የውጪ ንግድ ማሳለጫ ወደብ አገልግሎት፤ የቅጠላ ቅጠል እና ፍራፍሬ ምርት፤ እንዲሁም በበግ፤ ፍየል፤ ግመል፤ አህያ፤ ፈረስ አና የመሳሰሉት የቁም ከብቶች እርባታም ቀና ደፋ እያለች የዜጎቿን ህይወት ለማቆየት ስትውተረተር እንደከረመች ያሳያል፡፡ ኤርትራን ከ1300 ኪሎ ሜትር በላይ በሆነ ርዝመት እየታከከ በሚያልፈው የቀይባህር ውስጥ ከ1000 በላይ ዝርያ ያላቸውን የአሳ ምርት ለጥቅም ሲያውሉም እንደነበር ይገልጻል፡፡

በባለፉት ስድስት አመታት ኤርትራን ለማሰስ ድፍረቱን ያገኙ የከርሰ ምድር ጥናት ተመራማሪዎች እንደሚሉት ከሆነ ደግሞ ኤርትራ የማዕድን ሃብቷም ገና ጫፉ አልተነካም፡፡ የአገሪቱ የወርቅ፤ ብር፤ መዳብ፤ ዚንክ፤ ብረት፤ ፖታሽ፤ እና ሌሎች መዐድናት የአለም ኢንቨስተሮችን ቀልብ መማረክ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ ከነዚህ ኢንቨስተሮች አንዱ በካናዳው ነቭሰን እና በኤርትራ መንግስት የጋራ ድርሻ ባለቤትነት የተመሰረተው ቢሻ የመዐድን ምርት ድርጅት ነው፡፡

የኤርትራ መንግስት 40 በመቶ አንዲሁም ነቭሰን 60 በመቶ በሆነ የድርሻ ባለቤትነት በ2008 እ.ኤ.አ. የተከፈተው ማምረቻ በ2011 እ.ኤ.አ. ስራውን ጀምሯል፡፡ እንደጅማሮ ትንሽ ዋጋ ያላቸውን የወርቅ እና የብር መዐድናትን በማምረት  የጀመረ ሲሆን፤ በ2013 እ.ኤ.አ.  ደግሞ ዋጋቸው ትንሽ፤ ጥራታቸው ግን ከፍተኛ የሆኑ መዳቦችን ወደማምረት እንደተሸጋገረ የኦስሎ ዩኒቨርስቲው ጥናት ያሳያል፡፡ የኤርትራን የመዐድን ምርት ወደጥቅም ለመቀየር፤ መንግስቷ ኢንቨስተሮችን ሲያሳድድ፤ ኮንትራቶችን ሲፈርም ነው የከረመው፡፡

የዛራ እና ድብርባ የወርቅ ማምረት እንቅስቃሴዎች ውጤታማ ቢሆኑ ለኤርትራ በየአመቱ በመቶ ቢሊዮን ዶላሮች ያሳፍሳሉ ተብለውም ታቅደው ነበር፡፡ በዳናክል ረባዳማ ስፍራ ሊካሄድ ታቅዶ የነበረው የፖታሽ ምርት ደግሞ፤ ለ200 አመታት የሊዝ ኪራይ ስምምነት የተፈረመበት ቢሆንም ለአገሪቱ ምንም ጠብ ሳያረግ ነው የኖረው፡፡ የዚህ ምክኒያቱ ደግሞ የምርት አንቅስቃሴዎችን በገንዘብ ለመደገፍ ፍቃደኛ የሆኑ አለም አቀፍ ኢንቨስተሮች ፍላጎት ማጣት ነው፡፡ ከመንግስት ጋር ውል የሚፈራረሙ ኮርፖሬሽኖች የፕሮጀክቶቹ አትራፊነት ምንም ያክል አሳማኝ ቢሆን የኤርትራ ፖለቲካዊ ሁኔታ መተማመንን ሳይፈጥር በመኖሩ ዜጎቿ ላም አለኝ በሰማይ ሲሉ ኖረዋል፡፡ ይህንን ሰንኮፋ ለመንቀል ተስፋ የተጣለበት ክስተት በ2018 እ.ኤ.አ. ተስምቷል፡፡

ከነዚህ እና ከሌሎች እንቅስቃሴዎች ኤርትራ በ2014 እ.ኤ.አ. ከ400 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንዳገኘች አምባሳደሩ የአለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅትን ጥቅሰው ያስቀምጣሉ፡፡ ሆኖም የአገሪቱ ከጠቅላላ ምርቷ ጋር ሲነጻጸር የነበረባት የበጀት እጥረት ከ20 በመቶ በላይ እንደሚሆን ግምታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡ አንደኛው ምክኒያት ደግሞ ከራሽያ እና ከዩክሬን የሚገዟቸው ውድ የጦር መሳሪያዎች ነበሩ፡፡ አምባሳደሩ ከራሺያው አቻቸው ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ የኤርትራ መንግስት 50 ሚሊዮን ዶላር ግምት ያለው መሳሪያ ከአገራቸው እንደገዛ ነግረውኝ ነበር ይላሉ፡፡ እንዲያ ከሆነ ደግሞ ኢሳያስ በውጭ ከሚገኙ ዜጎች በግብር መልክ የሚሰበስቡትን ገንዘብ መሳሪያ ላይ እንዳዋሉት ማሳያ ነው- እንደ ማክሚዪለን፡፡

ከተራሮቹ ጀርባ ብቅ ያለው የኢኮኖሚ ተስፋ ደምቆ ይወጣ ይሆን?

ወደነበረበት መመለስ የቻለውን የኢትዮጲያና ኤርትራ ግንኙነትን ተከትሎ፤ ኢትዮጲያ የተባበሩት መንግስታት ጊዜያዊ ሊቀመንበርነቷን ተጠቅማ አስፈጽማዋለች የተባለውና፤ ኤርትራን የማግለል ውሳኔ እንዲቀየር ሲደረግ የነበረው ጫና ተሳካ፡፡ የአገሪቱ ባልስልጣናት ከአገር ውጪ እንዲንሸራሸሩ፤ አገሪቱም የመሳሪያ ግዢን ባሻት ጊዜ እንደትፈጽም ተፈቅዷል ተባለ፡፡ የሁለቱ አገራት ዳግሞ ግንኙነት፤ ምንም እንኳን መርህ ላይ የተመሰረተ አይደለም፤ የህግ ማዕቀፍም ያጥረዋል ተብሎ ቢታማም፤ ለአብይ አህመድ የሰላም ኖቤል ሽልማትን ይዞ ከመምጣት ግን አላገደውም፡፡ በፊት በኤርትራ ለሚደረጉ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ገንዘባቸውን ለሰሰቱት የአለም አቀፍ ባንኮችና ኢንቨስተሮች አዲስ ተስፋን በጆሯቸው ሹክ ያለ መሰለ፡፡

መቀመጫውን ኒው ዮርክ ያደረገውና አለም አቀፍ የንግድና ኢንቨስትመንት መረጃዎችን የሚያዘዋውረው ብሉምበርግ፤ የመጀመሪያውን የውጪ ኢንቨስትመንት ተስፋ ይዞ ብቅ አለ፡፡ ብሉምበርግ በነሃሴ 2019 እ.ኤ.አ. ባወጣው ዘገባ፤ የአፍሪካ የፋይናንስ ትብብር እና የአፍሪካ የወጪ-ገቢ ንግድ ባንክ ተቋማት፤ መቀመጫውን አውስትራሊያ ላደረገው ደናካሊ የማዕድን ማምረቻ ድርጅት ኤርትራ ውስጥ ለሚያከናውነውና በ2014 እ.ኤ.አ. የ200 አመት የሊዝ ኪራይ ስምምነት ለተፈራረመበት የፖታሽ ማምረቻ ፕሮጀክት፤ የ200 ሚሊዮን ዶላር ብድር ማጽደቃቸውን አበሰረ፡፡

በኤርትራ ብሔራዊ የመዐድን ማምረቻ እና በደናካሊ እያንዳንዳቸው 50 በመቶ ድርሻ ኖሯቸው ያንቀሳቅሱታል የተባለውና በዳናክል ረባዳማ ስፍራ ለሚካሄደው የፖታሽ ምርት ፕሮጀክት ዋና ስራ አስፈጻሚ ደስታቸውን ገልጸው፤ ብድሩ ለማምረቻ ፋብሪካ ግንባታውና ለምርት እንቅስቃሴው ከሚያስፈልገው የገንዘብ ፍጆታ አብዛኛውን ይሸፍናል አሉ፡፡ ፕሮጀክቱ በህጋዊ ድህረገጹ፤ የዳናክል ፕረጀክት በአለም ግምባር ቀደሙ ጥራት ያለው የፖታሽ ማዕድንን በርካሽ ዋጋ የሚያቀርብ እንደሚሆን ገለጸ፡፡

ማምረቻው ስራ ሲጀምር በሁለት ዙር የፖታሽ ምርትን ለገበያ የሚያቀርብ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ በመጀመሪያዎቹ አምስት አመታት 472ሺህ ቶን፤ ከስድስተኛው አመት በኋላ ደግሞ 944 ሺህ ቶን የፖታሽ ምርትን ለገበያ እንደሚያቀርብ እቅድ ተይዟል፡፡ ከውትድርና ሌላ ቅጥር ለማያውቁት ኤርትራውያን፤ ከ450 በላይ ቀጥተኛ የሆነ የስራ እድልን ይፈጥራልም ተብሏል፡፡ ፕሮጀክቱን ለማቀላጠፍ ከሚገነቡ መሰረተ ልማቶች እና ከፕሮጀክቱ ጋር በተያያዘ ከሚጀመሩ የንግድ እንቅስቃሴዎች በ10ሺዎች ይጠቀማሉ የሚል ተስፋን ሰንቋል፡፡

ኤርትራ ፕሮጀክቱ ለስኬት ከበቃ እንደ አገር በአመት ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ በግብር መልክ እሰበስባለው ብላ ተስፋ ሰንቃለች፡፡ በአመት ከ10 ሚሊዮን ዶላር በላይ ደግሞ በወርሃዊ ደሞዝ መልክ ለዜጎቿ ይከፈላቸዋልም ተብሏል፡፡ ይህን ተከትሎም በአካባቢው የሚገኙ ኤርትራውያን ንጹህ ገቢ ከ20 እጥፍ በላይ ይጨምራልም እየተባለ ይገኛል፡፡ የማህበራዊ ግዴታን ለመወጣት የሚደረጉ ኢንቨስትመንቶችም- ኤርትራ ከተራሮቿ ጀርባ ከባህር በሮቿ በዘለለ ያላትን ኢኮኖሚያዊ አቅም፤ በተስፋ መልክ በጨረፍታ እንድታሳይ ሊረዳት የሚችል ይመስላል፡፡

በኤርትራ የፖታሽ ማዕድን ለማውጣት እየሰራ ያለው ደናካሊ ኩባንያ ከሁለት አመት በፊት በለንደን የአክስዮን ገበያን ሲቀላቀል

ከምድሯ በላይ የቀይ ባህርን፤ ከምድሯ በታች ዝቀው የማይጨርሱት መዐድኖቿን ተሸክማ፤ ዜጎቿን ለውትድርና፤ አለፍ ሲልም ለስደት መገበሩን ይብቃ ለማለት ጊዜው አሁን ይመስላል፡፡ ከማህጸኗ ተፈጥረው ከገጸ በረከቷ ሊቃመሱ ይቅርና የእናትነት ጣዕሟንም ሳያዩ ለተሰደዱ ልጆቿ፤ ምቹ አገር መፍጠርን ሹማምንቶቿ ተቀዳሚ አላማቸው ሊያርጉት ጊዜው አሁን ይመስላል፡፡

ልጆች ከፈለጉ ከአባታቸው ጋር እዚሁ ይቀመጡ፡፡ እኔ ቢሆንልኝ አስመራ ተመልሼ አንድ ንግድ ጀምሬ፤ ትንሽ ከፍ ካለ ደግሞ አዲስ አበባም ሌላ ከፍቼ እዚህና አዚያ እየተመላለስኩ መኖር ነው የምፈልገው፡፡

ትላለች ሊዲያ ቢሆንልሽ ብለሽ የምትመኚው ብሎ ኢትዮኖሚክስ ላቀረበላት ጥያቄ፡፡

ለእራሷ እና ለዜጎቿ ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካ የኢንቨስትመንት ፍሰት መግቢያ በር መሆን የምትችልን አገር መገንባት፤ ከኢሳያስ ፖለቲካዊ ፍላጎት በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል፡፡ የኤርትራን የኢኮኖሚ ተስፋ እንደተራሮቿ አግዝፎ መገንባት፤ እራሳቸውን እንዲፈትኑ የቀረበላቸው አዲሱ ግብግብ መሆኑን መረዳት፤ አገራቸውን እንደ አንድ ሰሞኑ ቅጽል ሰሟ ሰሜናዊት ኮከብ እንድትሆን ለማስቻል የመጀመሪያ እርምጃ ሊሆን ይችላል፡፡ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ራስን ለማስተዳደር የጀመሩት ትግል፤ እርሳቸውን ፕሬዝዳንት ከማረግ በዘለለ፤ እራስን ወደ መቻል እንዲሸጋገር ትግሉን የማስጀመሪያ ጊዜው አሁን ነው ቢባል ከእውነት የራቀ አይሆንም፡፡

- Advertisement -

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisement -

Latest News

ሰበር ዜና – ዛሬ ረፋድ ላይ አዲግራት ከተማ በትግራይ ሰራዊት እጅ ወድቃለች

ባለፉት አራት ቀናት ዘመቻ አሉላ አባነጋ በሚል ፀረ ማጥቃት የጀመረው በህወሃት የሚመራው የትግራይ ሰራዊት በርካታ ከተሞችን መቆጣጠሩን ከስፍራው የደረሰን...

“የትግራይን ሕዝብ እናጠፋዋለን ሲሉ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ቃል በቃል ነግረውኛል” የአውሮፓ ሕብረት ልዩ መልዕክተኛ

ባለፉት 6 ወራት ውስጥ ሁለት ጊዜ ወደ አዲስ አበባ ተጉዘው የነበሩት የፊንላንዱ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ፔካ ሃቪስቶ በትላንትናው እለት አስደንጋጭ የሆነ ንግግር በአውሮፓ ሕብረት...

የኢትዮጵያ መንግስት ሃሰተኛ መረጃ ሲያሰራጭባቸው የነበሩ ከመቶ በላይ ገፆችን ዘግቻለው ሲል ፌስቡክ አስታወቀ

የማህበራዊ ድህረገፁ ፌስቡክ በትላንትናው እለት ባወጣው ዝርዝር ሪፖርት ከመቶ በላይ የሆኑ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ንክኪ ያላቸው ገፆችን እንደዘጋ አስታወቀ። ፌስቡክ ባደረገው ውስጣዊ ምርመራ እነዚህ...

“ዳቦ ከጠፋ ለምን ኬክ አይበሉም?” አዲስ አበቤነትና የኢትዮጵያውያን ሰቆቃ

እንደ ኢትዮጵያውያን አቆጣጠር በ1965 ዓ.ም በወሎ ስለተከሰተው አስከፊ ረሃብ መረጃ የደረሰው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምናልባት አዲስ አበባ ላይ በቂ ግንዛቤ ላይኖር ይችላል በሚል ከኒውዮርክ...

ቢሮ እንኳን ሳይኖረው የ3.6 ቢልዮን ዶላር ፕሮጀክት የወሰደው የአሜሪካ ኩባንያና የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ትብብር

ባሳለፍነው ታህሳስ ተቀማጭነቱን በኒውዮርክ ከተማ ባደረገ አንድ ክዋርትዝ የተሰኘ የኢንተርኔት ጋዜጣ ላይ የታተመው ፅሁፍ የኢትዮጵያን መንግስት አንገት ያስደፋና በአንዳንድ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ቁጣን ያጫረ ነበር።...
- Advertisement -

More Articles Like This

- Advertisement -