ላለፉት ሁለት አመታት በተባበሩት መንግስታት የፀጥታ ምክር ቤት ጊዜያዊ አባል ሆና ለመመረጥ ከጅቡቲ ጋር አንገት ለአንገት ተናንቃ የቆየችው ኬንያ በመጨረሻም ማሸነፏን አረጋግጣለች፡፡ በምክር ቤቱ አፍሪካን ለመወከል ከፍተኛ ፍላጎት የነበራት ጅቡቲ በአካባቢው ትልቅ ቅስቀሳ ስታደርግ ከመቆየትም አልፎ ለኬንያ ቦታውን በፈቃደኝነት አልለቅም የሚለው ውሳኔዋ በርካታ የአፍሪካ አገራት ከሁለቱ ለየትኛቸው ድምፅ እንደሚሰጡ ግራ አጋብቷቸው ቆይቷል፡፡ የፀጥታ ምክር ቤቱ 5 ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ያላቸው ቋሚ አባላት ያሉት ሲሆን ሌሎች 10 ጊዜያዊ አባላት ደሞ በየ2 አመቱ እየተፈራረቁ ቦታ ይይዛሉ፡፡
ከነዚህ 10 ጊዜያዊ መቀመጫዎች አንዱ ለአፍሪካ የሚሰጥ ሲሆን በተለምዶ የአፍሪካ አገራት ከውስጣቸው አንድ አገር ተስማምተው ለምርጫ ይልኩና ድምፅ በሚሰጥበት ሰዓት ያቺ የአፍሪካ ተወካይ ከአህጉሩ ሌላ ተቀናቃኝ ስለማይኖራት በሙሉ ድምፅ በማለፍ ቦታዋን ትረከባለች፡፡ ሆኖም በዚህ አመት በርካታ የአፍሪካ አገራት ቦታው ለኬንያ እንዲሰጥ ቢስማሙም ጅቡቲ አሻፈረኝ በማለቷ ባልተለመደ መልኩ በኒው ዮርክ ምርጫ በሚደረግበት ቀን ሁለት የአፍሪካ አገራት ለውድድር ሊቀርቡ ችለዋል፡፡ በፀጥታው ምክር ቤት ውስጥ ቦታ መያዝ ለአንድ አገር ከፍተኛ ጥቅም የሚኖረው ሲሆን የምክር ቤቱ አባላት የተለያዩ ጉዳዮችን አንስተው ለውይይት ማቅረብና እንዲሁም ውሳኔ እንዲደረግባቸው የድምፅ መስጠት እንዲከናወን ማስተባበር ይችላሉ፡፡