Monday, April 12, 2021

ኮቪድ 19 የተጋባበት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በአሜሪካው የደረጃ መዳቢ ተቋም ሲገመገም

Must Read

በአክሱም ከተማ ስለተፈፀመው ጭፍጨፋ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ሙሉ ሪፖርቱን ይፋ አደረገ

  ተቀማጭነቱን በለንደን ከተማ ያደረገውና በሰብአዊ መብት ጉዳዮች ላይ በመላው አለም ክትትል የሚያደርገው አምነስቲ ኢንተርናሽናል ከሰአታት በፊት ባወጣው ባለ 25...

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከፊል ድርሻ ለቱርክ መንግስት ሊሸጥ ነው

ዛሬ ከዋሽንግተን ዲሲ አካባቢ የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው በጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የሚመራው የኢትዮጵያ መንግስት የኢትዮጵያ አየር መንገድን እስከ...

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ የሸጠችው ቦንድ ዋጋው እያሽቆለቆለ ነው

ከውጭ ባለሃብቶች 1 ቢልዮን ዶላር ለመበደር በ2007 እ.ኢ.አ ኢትዮጵያ የሸጠችው ቦንድ በአየርላንድ የቦንድ ገበያ ላይ ባለሃብቶቹ እርስ በርስ የሚገበያዩበት...

በኢትዮጵያ የመጀመርያው የኮቪድ 19 ቫይረስ ተጠቂ ይፋ ከሆነ ጀምሮ ዛሬ 5ኛውን ወር ይዟል፡፡ እስካሁን ቫይረሱ የተፈራውን ያህል ባይሰራጭም በኢኮኖሚው ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት ግን ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ ሰሞኑን ተቀማጭነቱን በኒውዮርክ ያደረገው የደረጃ መዳቢ ተቋም የኢትዮጵያን የብድር መክፈል ብቃት ደረጃ ዝቅ ማድረጉም የአገሪቱ ኢኮኖሚ ምን ያህል እንደተዳከመ ያሳያል፡፡ ወረርሽኙ ባደጉት አገራት ላይ ባስከተለው ጥፋት ምክንያት በአገር ውስጥ ቱሪዝምና እንደ የአበባ ንግድ የመሳሰሉ ዘርፎች ላይ ተፅዕኖን አሳድሯል። የዛሬ አመት ከ300 ሚልዮን ዶላር በላይ ለአውሮፓ ገበያ በማቅረብ ዳጎስ ያለ የውጭ ምንዛሬን አስገኝተው የነበሩት የአበባ እርሻዎች ዛሬ ስራ በማቆማቸው አገሪቱ ከአበባ ምርት የምታገኘው ገቢ ከመመናመኑም ባሻገር በርካታ ሰራተኞችን ለስራ እጦት ዳርጓል፡፡

በሌላ በኩል የኮቪድ 19ኝን በአውሮፓ፣ አሜሪካ፣ ደቡብ አፍሪካና አረብ አገራት መስፋፋት ተከትሎ የተፈጠረው የንግድና አጠቃላይ የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ከዚህ በፊት ወደ አገር ውስጥ ይልኩት የነበረውን የውጭ ምንዛሬ እንዲቀንሱ አስገድዷቸዋል፡፡  በዓመት በውጭ ተሰደው ከሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከ5 ቢልዮን ዶላር በላይ የምታገኘው ኢትዮጵያ የአገር ውስጥ ምርቶቿን ወደ ውጭ ልካ ከምታገኘው የውጭ ምንዛሬ በእጥፍ የሚበልጥ ነው። በተጨማሪም የውጭ ባለሃብቶች ወደ አገር ይዘውት የሚመጡት በቢልዮኖች ዶላር የሚተመን ኢንቨስትመንት በዚህ በመገባደድ ላይ ባለው ዓመት የ700 ሚልዮን ዶላር ቅናሽ አሳይቷል።

ሙዲስ በመባል የሚታወቀው የደረጃ መዳቢ ተቋም የአገራትንና ብሎም የኩባንያዎችን ገቢና ወጪ በማስላት እስካሁን ያለባቸውን ብድርና ለወደፊት ለሚበደሩት ገንዘብ ያላቸውን የመክፈል አቅም ገምግሞ ደረጃ የሚሰጥ ነው። ይህ የደረጃ ምድብ በግል የብድር ተቋማት ዘንድ የተበዳሪዎችን ተዓማኒነት ለመለካት ያገለግላል። ኢትዮጵያ በመጪው የበጀት ዓመት ከ600 ሚልዮን ዶላር በላይ ለውጭ ብድር ክፍያ የመደበች ቢሆንም እንደ ሙዲስ ግምገማ ግን የብድር ክፍያ የመፈፀም አቅሟ እየተዳከመ መምጣቱን ያሳስባል፡፡

ለዚህም እንደ ዋና ምክንያት ከሚጠቅሳቸው ውስጥ ላለፉት 10 ዓመታት ባለ ሁለት አሃዝ እድገት ሲያስመዘግብ የቆየው ኢኮኖሚ የኮቪድ 19ኝን ወደ ኢትዮጵያ መግባት ተከትሎ እድገቱ በመገታቱ ነው። በዚህኛውና በሚቀጥለው ዓመት ይመዘገባል ተብሎ የሚጠበቀው እድገት ከ2 ፐርሰንት አይበልጥም የሚል ግምገማ ሙዲስ ቢያካፍልም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚስቶች ማህበር በበኩሉ ባሳለፍነው ወር ባወጣው ጥናት ኢኮኖሚው በዚህ ዓመት በ0.6 ፐርሰንት ብቻ ነው የሚያድገው ሲል ተናግሯል።

ሌላው የኢትዮጵያን የብድር መክፈል አቅም ደረጃ ዝቅ አድርጎታል የተባለው ምክንያት ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ጂ20 ለሚባለው ያደጉ አገራት ማህበር ከአራት ወራት በፊት ያቀረቡት የብድር ማቃለል ጥያቄ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚንስትሩ ፋይናንሻል ታይምስ ተብሎ በሚጠራው የእንግሊዝ ጋዜጣና እንዲሁም ዘ ኒውዮርክ ታይምስ በሚባለው የአሜሪካ ጋዜጣ ላይ ባሳተሙት ፅሁፍ ያደጉት አገራት ኮቪድ 19 አፍሪካ ላይ የሚያመጣውን አደጋ ችላ ማለት እንደሌለባቸውና ካልሆነ ግን መዘዙ ከአፍሪካውያንም አልፎ ለመላው ዓለም እንደሚተርፍ አስጠንቅቀው ነበር።

ጠቅላይ ሚንስትሩ በዚህ አፍሪካን ወክለው በፃፉት ፅሁፍ የጂ20 አገራት ለአፍሪካ የ150 ቢልዮን ዶላር ብድር ማቃለል እንዲያደረጉ ሲጠይቁ የአፍሪካ ሕብረትንም ሆነ ሌሎች መሪዎችን አለማማከራቸው በርካታ ዲፕሎማቶችንና የአፍሪካ መንግስታትን ግራ አጋብቶ ነበር።

ይህንንም ተከትሎ ኬንያ በብድር ቅነሳም ሆነ የክፍያ ሰንጠረዡን ለማራዘም ፍላጎት እንደሌላት አስታውቃለች። ኬንያ የብድር ማቃለል እንዲደረግላት ያልፈለገችው የብድር ክፍያ ካራዘመችም ሆነ ካቋረጠች በምዕራቡ ዓለም እንደ ሙዲስ ያሉ የደረጃ መዳቢ ተቋማት ደረጃዋን ዝቅ እንዳያደርጉባትና ተዓማኒነቷም እንዳይሸረሸር ይህም ለወደፊት ከግል የውጭ ተቋማት የመበደር እድሏ ላይ ተፅዕኖ እንዳያሳድርባት በሚል ስጋት ነበር። አብዛኛዎቹ የመዕራቡ ዓለም የግል አበዳሪ ተቋማት ለአገራትም ሆነ ለኩባንያዎች ሲያበድሩ ከሚገመግሟቸው ዝርዝሮች አንዱ ተበዳሪው ከዚህ በፊት የብድር ቅነሳ ወይም የክፍያ ጊዜን አራዝሞ ያውቃል ወይ የሚለውን ሲሆን ከዚህ በፊት የተበደሩትን በአግባቡና በወቅቱ አለመክፈል ተቋማቱ በአዲስ ብድር ላይ የሚጠይቁት ወለድ ከፍ እንዲል ያደርገዋል።

ታድያ ይህ የኬንያ ፍርሃት በኢትዮጵያ እውን የሆነ ይመስላል። ኢትዮጵያ የፓሪስ ክለብ ከሚባሉት የአበዳሪዎች ማሕበርም ሆነ ከጂ20 አገራት ጋር የምታደርገው ብድርን የማቃለል ድርድር ለወደፊት ለሚያበድሯት የግል ተቋማት እንደ ማስጠንቀቅያ ታይቷል፡፡ ይህን የማስጠንቀቅያ ደወል የደወለው ሙዲስም ደረጃዋን ቀድሞ ከነበረው ቢ1 ወደ ቢ2 ዝቅ በማድረጉ ለወደፊት የግል ተቋማት ለኢትዮጵያ ሲያበድሩ የሚጠይቁትን የወለድ መጠን ከፍ ያደርገዋል ማለት ነው፡፡

በምዕራቡ ዓለም የሚገኙ የግል አበዳሪ ተቋማት የሚከተሉት ይህ አይነት አሰራር በተዘዋዋሪም ቢሆን በተበዳሪ አገራት ውስጥ ባሉ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችና እንቅስቃሴዎች ላይ ተፅዕኖን እንዲፈጥሩ መንገድ በመክፈት የተበዳሪ አገራትን ሉአላዊነት የሚፈታተን ነው። ለዚህም ነው ኢትዮጵያ ላለፉት 15 ዓመታት ከምዕራባውያን የግል አበዳሪ ተቋማት ጋር ያላትን ግንኙነት በመቆጠብ አብዛኛውን ብድሯን ከቻይና መንግስታዊ ተቋማት ስታገኝ የኖረችው።

ሙዲስ አክሎም የኢትዮጵያ መንግስት ከግብር እንዲሁም በይዞታ ከሚያስተዳድራቸው ድርጅቶች የሚያገኘው ገቢ ለዓመታዊ በጀቱ ከሚያወጣው ወጪ ያነሰ በመሆኑ የአጠቃላይ ኢኮኖሚውን 5 ፐርሰንት ያህል የሚደርስ የበጀት ክፍተት ያጋጥመዋል ብሏል፡፡ ለዚህም ምክንያቱ በመንግስት ስር ያሉ ግዙፍ ተቋማት ባላቸው ደካማ አሰራር ምክንያት በቂ ገቢ ማስገባት ባለመቻላቸውና እንዲሁም ኮቪድ 19 በፈጠረው የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ምክንያት መንግስት የሚሰበስበው የግብር መጠን መቀነሱ እንደሆነ አክሎ ገልጿል።

የኢትዮጵያ መንግስት በመጭው ዓመት የገቢና ወጪ አለመመጣጠንን ለማስተካከል ከ5 ቢልዮን ዶላር በላይ የሚያስፈልገው ቢሆንም አሁን ባለው ሁኔታ ግን እንደ በፊቱ ከውጭ የግል ተቋማት በቀላሉ መበደር እንደሚቸግረውና ይህም መንግስትን አጣብቂኝ ውስጥ ሊከተው እንደሚችል ተጠቅሷል። በተለይም አዲሱ የጠቅላይ ሚንስትር አብይ መንግስት ኢትዮጵያን ከቻይና ቀስ በቀስ እያራቀ ፊቱን ወደ ምዕራባውያን ማዞሩ ቻይናን ቅር አሰኝቶ ከዚህ በፊት የነበሩትን አማራጮች ያጠበበ በመሆኑ ኢትዮጵያ በምዕራባውያን አበዳሪ ተቋማት ላይ ያላትን ጥገኝነት እንዲጨምር አድርጎታል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ዛሬ አገር ውስጥ በአስርት ሺዎችን የበከለው ኮቪድ 19 ኢኮኖሚውን ይበልጥ ቁልቁል ይግፋው እንጂ የአገሪቱ ኢኮኖሚ መዋዠቅ የጀመረው ግን ወረርሽኙ ከመከሰቱ በፊት ነበር። ባለፉት ሁለት ዓመታት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የታየው አለመረጋጋት የውጭ ባለሃብቶች እጃቸውን እንዲሰበስቡ ያደረገ ሲሆን ባለሃብቶችን በመሳብ በሚታወቀው ግዙፉ የኦሮምያ ክልል ተደጋጋሚ ግጭት መከሰቱ ደግሞ ችግሩ እንዲጎላ አድርጎታል። ለምሳሌ ባሳለፍነው የፈረንጆች ዓመት የታየው የ2.5 ቢልዮን ዶላር ከውጭ የሚመጣ የሃብት ፍሰት ከ4 ዓመታት በፊት ከተገኘው 4.2 ቢልዮን ዶላር ጋር ሲነፃፀር እጅጉን ያነሰ ነው።

ሌላው ደግሞ ከእለት ወደ እለት እየጨመረ የመጣው የዋጋ ግሽበት ነው። ባለፉት 12 ወራት ውስጥ ብቻ የተመዘገበው የዋጋ መጨመር ከሰባት ዓመታት በኋላ ከፍተኛው ሆኖ ተመዝግቧል። በተለይም በምግብ ነክ ምርቶች ላይ የታየው የዋጋ ግሽበት በተወሰነ መልኩ አገር ውስጥ ከነበረው አለመረጋጋት ጋር የተያያዘ ቢሆንም ዋነኛ ምክንያቱ ግን ሌሎች መሠረታዊ ከሆኑ ችግሮች ጋር የሚያያዝ ነው። ከነዚህ ውስጥም ለውጡን ተከትሎ እየተቀየረ ያለው የኢኮኖሚ መዋቅር ለአርሶ አደሩ ብዙም ትኩረት የሰጠ ባለመሆኑ፣ ከገጠር ወደ ከተማ የሚደረገው የሕዝብ ፍልሰት መጨመሩ፣ እንዲሁም መንግስት የበጀት ክፍተቱን ለመሙላት የሚያትመው ከመጠን ያለፈ ገንዘብ ይገኙበታል።

የዋጋ ግሽበት እየተባባሰ መሄድም ብርን ዋጋ እያሳጣው በመሄዱ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ እቃዎችን ሲያስወድድ ይህም ተመልሶ የዋጋ ግሽበት ላይ የባሰ ተፅዕኖ እንዲፈጥር አድርጎታል። በተለምዶ የአንድ አገር ገንዘብ ዋጋውን እያጣ በሚሄድበት ወቅት አገሪቱ ወደ ውጭ የምትልካቸውን ምርቶች ስለሚያረክሳቸውና ገበያን የሚያጧጡፍ ቢሆንም እንደ ኢትዮጵያ ያሉ የአቅርቦት እንጂ የፍላጎት እጥረት በሌለባቸው አገራት ግን በብር ዋጋ ማጣት ከመጠቀም ይልቅ የሚደርስባቸው ጉዳት ያመዝናል።

ሆኖም ብሔራዊ ባንክ ከዓለም የገንዘብ ተቋምና ከዓለም ባንክ እየደረሰበት ባለው ጫና ምክንያት የብርን የመግዛት አቅም በየእለቱ እያወረደው ይገኛል። ብሔራዊ ባንክ በሚያወጣው ተመን የዶላር ዋጋ ላለፉት አራት ወራት በአማካይ የ3 ሳንቲም እለታዊ ጭማሪ በተከታታይ ያሳየ ሲሆን ይህም የሚያመላክተው መንግስት የሕዝቡን ትኩረት ብዙም ላለመሳብ በመጠንቀቅ የብርን ዋጋ ቀስ በቀስ እያወረደው እንደሆነ ነው።

እንደዚህም ሆኖ ታድያ በዓለም ባንክም ሆነ በዓለም የገንዘብ ተቋም አመለካከት የብር ዋጋ በተፈለገው ፍጥነት እየወረደ አይደለም። ባሳለፍነው ሰኔ የዓለም ባንክ ፕሬዝዳንት የሆኑት አሜሪካዊው ዴቪድ ማላፓስ ከጠቅላይ ሚንስትር አብይ ጋር ባደረጉት የስልክ ውይይት የኢትዮጵያ ብር አሁንም መውረድ እንዳለበት አሳስበው ነበር። እነዚህ ተቋማት የጠቅላይ ሚንስትር አብይን ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎ በብድርና በበጀት ድጋፍ መልክ ለኢትዮጵያ ለመስጠት ቃል የገቡት ገንዘብ አገሪቷ ማሟላት ካለባት ቅድመ ሆኑታዎች ጋር የተያያዘ ሲሆን ከነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች አንዱ ብርን የማዳከሙ ጉዳይ ነው።

የኢዜማ ፓርቲ መሪ የሆኑት ኢኮኖሚስቱ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ከወራት በፊት ከፋና ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት የእንግሊዘኛ ቃለ ምልልስ ላይም እነዚህ የምዕራቡ ዓለም ተቋማት የራሳቸውን ጥቅም የሚያስቀድሙ እንደሆነና የኢትዮጵያ መንግስትም አርግ የሚሉትን ሁሉ ተቀብሎ መተግበሩ አደጋ አለው ሲሉ አስጠንቅቀዋል። ሆኖም የብር ዋጋ እየተዳከመ መሄዱ አሁንም እንደቀጠለ ነው። ብሔራዊ ባንክ በቅርቡ ይፋ እንዳረገው በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት ውስጥ የብር መዘርዘርያ ዋጋን መቆጣጠር እንደሚያቆምና በገበያ ወይም በአቅርቦትና ፍላጎት ላይ የተመሰረተ የዝርዝር ዋጋ እንደሚኖር አስታውቋል። ይህም በብር የመግዛት አቅም ላይ ከፍተኛ ጫና የሚያሳድር ሲሆን አሁን ያለውን የዋጋ ግሽበት እጅጉን ሊያባብስ የሚችል ነው።

ይባስ ብሎም በገበያ የሚተመን የዝርዝር ዋጋ የአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ የመጡ ባለሃብቶች ገንዘብ ለማሸሽ በሚሞክሩበት ወቅት መንገድ የሚያመቻችላቸው ሲሆን የውጭ ምንዛሬ ወደ ውጭ በሸሸ ቁጥርም የብርን ዋጋ ይበልጥ እንዲወርድ ይገፋዋል። የአገሪቱ ተቀማጭ የመጠባበቅያ የውጭ ምንዛሬ መጠን ከ3 ቢልዮን ዶላር በታች መሆኖ ደግሞ ብሔራዊ ባንክ ዶላርን ለገበያ በማቅረብ የብርን ዋጋ ቁልቁል ከመውረድ ለመታደግ እንዳያስችለው እጁን የሚያስር ይሆናል።

ታድያ ደረጃ መዳቢው ሙዲስ የኢትዮጵያን ደረጃ መልሶ ከፍ ለማድረግ መሻሻል አለባቸው የሚላቸውን የተለያዩ ነጥቦች ጠቁሟል። የአጠቃላይ ብድር እዳ መቃለል፣ የመንግስት ወጪ (በጀት) እያደገ የመጣበትን ፍጥነት መቀነስ፣ ቢሮክራሲን ማሻሻልና ተቋማትን ማጠናከር ኢኮኖሚውን ለማሻሻል ይረዳሉ ብሏል።

በአንፃሩ ደግሞ የብድር እዳ መጨመር፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት መባባስ፣ ከውጭ የሚገኝ እርዳታ መቀነስ፣ እንዲሁም በብሔራዊ ባንክ ያለው ተቀማጭ የውጭ ምንዛሬ አሁን ካለበት ዝቅተኛ መጠን የባሰ ማሽቆልቆል የኢትዮጵያን ደረጃ ድጋሚ ለማውረድ እንደሚያስገድዱት አስጠንቅቋል።

- Advertisement -

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisement -

Latest News

በአክሱም ከተማ ስለተፈፀመው ጭፍጨፋ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ሙሉ ሪፖርቱን ይፋ አደረገ

  ተቀማጭነቱን በለንደን ከተማ ያደረገውና በሰብአዊ መብት ጉዳዮች ላይ በመላው አለም ክትትል የሚያደርገው አምነስቲ ኢንተርናሽናል ከሰአታት በፊት ባወጣው ባለ 25...

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከፊል ድርሻ ለቱርክ መንግስት ሊሸጥ ነው

ዛሬ ከዋሽንግተን ዲሲ አካባቢ የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው በጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የሚመራው የኢትዮጵያ መንግስት የኢትዮጵያ አየር መንገድን እስከ ግማሽ የሚጠጋ የባለቤትነት ድርሻ ለቱርክ...

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ የሸጠችው ቦንድ ዋጋው እያሽቆለቆለ ነው

ከውጭ ባለሃብቶች 1 ቢልዮን ዶላር ለመበደር በ2007 እ.ኢ.አ ኢትዮጵያ የሸጠችው ቦንድ በአየርላንድ የቦንድ ገበያ ላይ ባለሃብቶቹ እርስ በርስ የሚገበያዩበት ዋጋ ማሽቆልቆሉን ቀጥሏል። ከሶስት ሳምንታት...

ኤርትራ፤ ከተራራው ጀርባ ጠልቃ የቀረችው ሰሜናዊት ኮኮብ

  ኤርትራ ከባህር በሯ በዘለለ፤ ምድሯ ጥቅም የለውም የሚለው አስተሳሰብ ከኢትዮጲያ ጋር ፍቺ ሳትፈጽም በፊት ገዢ ሃሳብ ሆኖ ነው የኖረው፡፡ በደርግ ጊዜ የኢትዮጲያ ፕሬዝዳንት የነበሩት...

ኢኮኖሚያዊ ህልሙ በፖለቲካ ይጨናገፍ ይሆን?

  በ2013 እ.ኤ.አ. የአዲስ አበባ መስፋፋት የኦሮሚያ ገበሪዎችን አፈናቅሏል በሚል የተጀመረው የጸጥታ አለመረጋጋት ሰባት አመታትን አስቆጥሯል፡፡ ይህ አመጽ አሁን ያሉትን ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ ስልጣን አምጥቶ...
- Advertisement -

More Articles Like This

- Advertisement -