በሰመናዊ የመቀሌ ክፍለ ከተማ እየተሞከረ የነበረው የመሬት አስተዳደር ግልጋሎቶችን በኢንተርኔት የመስጠት አሰራር ወደ አዲግራት፣ ሽረ፣ አክሱምና አድዋ ተስፋፍቷል። በመቀሌ ዩንቨርስቲ የተሰራው ሶፍትዌር ተጠቃሚዎች በአካል ወደ መንግስት ቢሮዎች መሄድ ሳያስፈልጋቸው በአቅራብያቸው ያለን ኢንተርኔት በመጠቀም የተለያዩ ማመልከቻዎችን እንዲያስገቡ የሚያስችል ነው። አዲስ ፎርቹን የተባለው የእንግሊዘኛ ጋዜጣ እንደዘገበው ይህ አሰራር በሚቀጥሉት አራት ወራት በ30 የትግራይ ክልል ከተማዎች ውስጥ በስራ ላይ የሚውል ይሆናል።
ለከተማዎች ልማት እንደ አንድ ትልቅ መሰናክል ሆኖ የቆየው የመሬት አስተዳደር አሰራር ግልፅነት ያልተሞላበትና ኋላ ቀር አወቃቀር ስለነበረው የተለያዩ የክልሉ መንግስት ቢሮዎች እርስ በርስ የሚቃረን መረጃ እንዲኖራቸውና ሰነዶች እንዲጠፉ እንዲሁም በተለያየ ጊዜ በመሬት ባለቤቶች መካከል ውዝግብ እንዲፈጠር አድርጓል።
በአዲሱ አሰራር መሰረት የክልሉ ነዋሪዎች ለካርታ ይዞታ፣ ለመሬት ሊዝ፣ የወሰን ጥያቄ፣ የመሬት ማካፈልና ማዋሃድ ለመሳሰሉት ባጠቃላይ 16 የሚሆኑ አገልግሎቶች በኢንተርኔት ማመልከት ይችላሉ። የትግራይ ክልል በ2012 የአስተዳደር አወቃቀር ለውጥ አድርጎ የስልጣን ክፍፍልን ያጠናከረ ሲሆን ወረዳዎችና ቀበሌዎች ከቀድሞው የበለጠ ስልጣን እንዲኖራቸው ተደርጓል። የመሬት አስተዳደርን ወደ ዲጂታል የመቀየሩ ሂደትም ለነዋሪዎች አገልግሎት ከመስጠትም አልፎ በመስርያ ቤቶች የውስጥ አሰራር ላይም የተተገበረ በመሆኑ ከቀበሌና ከወረዳ ጀምሮ እስከ የክልል ባለስልጣናት ድረስ የተቀናጀ የመሬት ይዞታ መረጃ እንዲኖራቸው ይረዳል።