Saturday, January 22, 2022

የኮቪድ 19ኝ ክትባት ምን ደረጃ ላይ ደርሷል?

Must Read

ሰበር ዜና – ዛሬ ረፋድ ላይ አዲግራት ከተማ በትግራይ ሰራዊት እጅ ወድቃለች

ባለፉት አራት ቀናት ዘመቻ አሉላ አባነጋ በሚል ፀረ ማጥቃት የጀመረው በህወሃት የሚመራው የትግራይ ሰራዊት በርካታ ከተሞችን መቆጣጠሩን ከስፍራው የደረሰን...

“የትግራይን ሕዝብ እናጠፋዋለን ሲሉ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ቃል በቃል ነግረውኛል” የአውሮፓ ሕብረት ልዩ መልዕክተኛ

ባለፉት 6 ወራት ውስጥ ሁለት ጊዜ ወደ አዲስ አበባ ተጉዘው የነበሩት የፊንላንዱ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ፔካ ሃቪስቶ በትላንትናው እለት...

የኢትዮጵያ መንግስት ሃሰተኛ መረጃ ሲያሰራጭባቸው የነበሩ ከመቶ በላይ ገፆችን ዘግቻለው ሲል ፌስቡክ አስታወቀ

የማህበራዊ ድህረገፁ ፌስቡክ በትላንትናው እለት ባወጣው ዝርዝር ሪፖርት ከመቶ በላይ የሆኑ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ንክኪ ያላቸው ገፆችን እንደዘጋ አስታወቀ።...

ባልታሰበ ፍጥነት እየተሰራጨና የበርካቶችን ህይወት እየቀጠፈ ያለው ኮቪድ 19 የዓለማችንን አሉ የተባሉ ተመራማሪዎች ከጊዜ ጋር እሽቅድድም ውስጥ ከቷቸዋል። ላለፉት 8 ወራት በመላው ዓለም የሰዎችን እለታዊ እንቅስቃሴ ክፉኛ የገታው ይህ ቫይረስ እስካሁን በትንሹ 38 ሚልዮን የሚሆኑ ሰዎችን ያጠቃ ሲሆን ከ1 ሚልዮን በላይ የሚሆኑትን ለሞት ዳርጓል። ይባስ ብሎም ይህ አሃዝ ቫይረሱ እንዳጠቃቸው ሳይታወቅ የሞቱትንና ሳይመረመሩ ተይዘው የተለቀቁትን የማይጨምር በመሆኑ አጠቃላዩ የኮቪድ 19 ተጠቂዎች ቁጥር በይፋ ከሚታወቀው በ10 እጥፍ ሊበልጥ እንደሚችል ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ይህንን ተከትሎም የኮቪድ 19ኝን ክትባት ለማግኘት በርካታ መንግስታትና የግል ተቋማት በቢልዮኖች የሚቆጠር ዶላር በማውጣት የምርምሩን ሂደት እያጣደፉት ይገኛሉ። በተለያዩ አገራት ያሉ ቁጥራቸው በሺዎች የሚገመት ሰዎችም በሙከራ ላይ ያሉትን 40 ክትባቶች በፈቃደኝነት ወስደዋል። በሰዎች ላይ እየተሞከሩ ካሉት እነዚህ 40 አይነት ክትባቶች ውስጥ 9 የሚሆኑት በሶስተኛውና የመጨረሻው የሙከራ ዙር ላይ የደረሱ ሲሆን ግኝቶቹ 4 በአሜሪካ፣ 3 በቻይና፣ 1 በእንግሊዝና ሌላ 1 ደግሞ በሩስያ የተቀመሙ ናቸው።

አንድ ክትባት በመንግስታዊ የጥራት መዳቢዎች ዘንድ ተቀባይነትን አግኝቶ ለሕዝብ ለመቅረብ 3 የሙከራ ዙሮችን ማለፍ ይኖርበታል። የእነዚህ ሙከራዎቹ አላማም የክትባቱን ቫይረስ የመከላከል አቅም መገምገምና እንዲሁም ተያይዞ የሚመጣ ተጓዳኝ የጤና መታወክ መኖሩንና አለመኖሩን ለመገምገም እንዲያስችል ነው። ለምሳሌ በአሜሪካ እየተሞከሩ ያሉት ክትባቶች የአገሪቱን የፌደራል መድሃኒት አስተዳደር ሙሉ ፈቃድ አግኝተው ወደ ገበያ ለመግባት ባለው ሂደት በመጀመሪያው ዙር ጥቂት ሰዎች ላይ ከቅርብ ክትትል ጋር በሚደረግ ሙከራ የጀመሩ ሲሆን በፈቃደኞቹ ላይ የተገኘው ውጤት ታይቶ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ወደሚያሳትፈው የሁለተኛ ዙር ሙከራ ይሸጋገራሉ። የሁለተኛው ዙር ሙከራ ለአንድ ሰው የሚያስፈልገውን የክትባት መጠን በአግባቡ ለመለካት እንዲያስችል በፈቃደኞች ላይ የተለያየ መጠን ያለው ክትባት ይሞከራል። በመቀጠልም የመጨረሻውና ሶስተኛው ዙር ሙከራ በ10ሺዎች የሚቆጠሩ ፈቃደኞችን ያሳትፋል። እነዚህ ፈቃደኞች በሁለት ቡድን ከተከፈሉ በኋላ አንዱ ቡድን ተለይቶ ክትባቱ የሚሰጠው ሲሆን ሁለተኛውን ቡድን ያለ ክትባት በማቆየት በሁለቱ መካከል ባለው የቫይረሱ ተጋላጭነት ልዩነት ላይ ጥናት ይደረጋል። ክትባቱ የሶስተኛውን ዙር አልፎ የጥራት ማረጋገጫን ለማግኘት በአጋግባቡ ተከትበው ሳለ ነገር ግን ቫይረሱ ያጠቃቸው ሰዎች ቁጥር ያለምንም ክትባት በቫይረሱ ከተጠቁት ሰዎች ቁጥር በግማሽ ያነሰ መሆን ይጠበቅበታል።

https://images.theconversation.com/files/345047/original/file-20200701-159820-hidget.jpg?ixlib=rb-1.1.0&q=45&auto=format&w=926&fit=clip
በሙከራ ላይ ያሉት ክትባቶች ለፈቃደኞች ከሚሰጡባቸው አገራት አንዷ ደቡብ አፍሪካ ነች

ታድያ የመጨረሻ ውጤታቸው በጉጉት እየተጠበቀ ያሉት እነዚህ 9 ክትባቶች ለዓለም ከፍተኛ ተስፋን የሰጡ ቢሆንም ገና ከአሁኑ ውዝግብ እየፈጠሩ ይገኛሉ። ምርምሩን ስፖንሰር አድርገው ባለቤትነታቸውን ያረጋገጡት 9ኙም ኩባንያዎች ክትባቶቹ ገና ለገና ውጤታማነታቸው ተረጋግጦና ለጅምላ ምርት ከመብቃታቸው በፊት ለተለያዩ አገራት ለመሸጥ መፈራረማቸውን በእንግሊዝ የሚታተመው ፋይናንሻል ታይምስ ጋዜጣ ዘግቧል። ይህ የገበያ ቅርምት ያሳሰበው በኢትዮጵያዊው ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም የሚመራው የዓለም የጤና ድርጅትም በበኩሉ ክትባቱ ለሁሉም የዓለም አህጉራት በአግባቡ እንዲዳረስ አገራት ተስማምተው በሕብረት እንዲሰሩ ተደጋጋሚ ጥያቄ ሲያቀርብ የቆየ ቢሆንም ጥቂት አገራት በቢልዮኖች የሚቆጠር ዶላር በማውጣት በየግላቸው ከክትባቱ አምራቾች ጋር ስምምነቶችን በማድረግ ላይ ይገኛሉ። በተለይም አሜሪካ ክትባቱን በትብብር ለዓለም ለማሰራጨት በተፈጠረው ማህበር ውስጥ እንደማትሳተፍና ከሁሉም ቅድምያ የምትሰጠው ለአገሯ ዜጎች መሆኑን በግልፅ አስታውቃለች።

አሜሪካ፣ እንግሊዝና ካናዳ በቢልዮኖች ዶላር የሚገመት ገንዘብ በማፍሰስ እያንዳንዳቸው ለአጠቃላይ ዜጎቻቸው ከሚያስፈልገው የክትባት መጠን 5 እጥፍ ለመግዛት ከአምራቾች ጋር ቀድመው ተስማምተዋል። ባጠቃላይ የዓለምን 13 ፐርሰንት ብቻ የሚሆነውን የሕዝብ ብዛት የያዙት የበለፀጉ አገራት ለገበያ ይቀርባል ተብሎ ከታሰበው ክትባት ውስጥ ግማሽ የሚሆነውን ለመግዛት ቀድመው በማመቻቸታቸው ትችት እየተሰነዘረባቸው ይገኛል። በተለይም ለክትባቱ ምርምር የሚያስፈልገውን ወጪ ለመሸፈን የገንዘብ ልገሳ እያደረጉ ያሉት እንደ አሜሪካ፣ እንግሊዝና የአውሮፓ ሕብረት አገራት ክትባቱ ለገበያ በሚቀርብበት ጊዜ ቅድሚያ ለነሱ እንዲሸጥ የሚያስገድዱ ስምምነቶችን ከተመራማሪዎች ጋር አድርገዋል።

ክትባቶቹ ተጓዳኝ የጤና መቃወስ ሊያስከትሉ ይችላሉ? እስካሁን ባለው መረጃ የመጨረሻውን ዙር ምርምር አልፈው በይፋ ለሕዝብ ሊሰራጩ የተቃረቡት ክትባቶች በፈቃደኛ ተከታቢዎች ላይ በተወሰነ መልኩም ቢሆን ያልተፈለገ ተፅዕኖ አሳይተዋል። የህክምና ነክ ቁሳቁሶችንና መድሃኒቶችን በማምረት የሚታወቀው ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን የተባለው የአሜሪካው ግዙፍ ኩባንያ ትላንትና ባወጣው መግለጫ በሶስተኛ ዙር የሙከራ ደረጃ ላይ የደረሰውን ክትባቱን ለጊዜው ለፈቃደኞች መስጠት ማቆሙን አሳውቋል። ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ሙከራውን እንዲያቆም ያስገደደው ለሙከራ እየተከተቡ ካሉት ፈቃደኞች አንዱ ምንነቱ ለጊዜው ግልፅ ላልሆነ ህመም በመዳረጉ እንደሆነ ኩባንያው ይፋ አድርጓል። በተመሳሳይ መልኩ ኦክስፎርድ የሚል ስያሜ የተሰጠው እንግሊዝ ውስጥ የተሰራው ሌላ ክትባት ከወር በፊት በሶስተኛ ዙር ሙከራ ላይ ሳለ በአንድ ተከታቢ ላይ ባስከተለው የጭንቅላት ህመም ምክንያት ሙከራውን ለማቆም እስከ መገደድ ደርሶ ነበር። ሆኖም ብዙም ሳይቆይ የሙከራ ሂደቱን ዳግም እንዲጀምር ከአሜሪካ በስተቀር በሌሎች አገራት ፍቃድ አግኝቷል ።

በተጨማሪም ሌሎች ሙከራ ላይ ያሉ ክትባቶች በየፊናቸው ከራስ ምታት እስከ ትኩሳት እያስከተሉ እንደሆነ ተመዝግቧል። ሆኖም ልክ እንደ ሌሎች በርካታ ክትባቶች ሁሉ እነዚህ በኮቪድ 19 ክትባት የሚመጡ ተጓዳኝ የጤና መታወኮች ከበቂ ሙከራና የጥራት ምዘና በኋላ አስጊነታቸው ከፍቶ እስካልታየ ድረስ ፍቃድ ተሰጥቷቸው ለሕብረተሰቡ መቅረባቸው የማይቀር ነው።

ይሁን እንጂ የክትባቶቹ ኮቪድ 19ን የመከላከል ዘላቂነት እስከ ምን ያህል ጊዜ ይሆናል በሚለው ላይ ምናልባት በየዓመቱ መከተብ ግድ ሊሆን እንደሚችል ተመራማሪዎች ካሁኑ እያሳሰቡ ይገኛሉ። የጥራት ማረጋገጫን ለማሟላት ተቃርበዋል ከተባሉት ክትባቶች አብዛኛዎቹ በቀናት ልዩነት ውስጥ ሁለት ጊዜ የሚሰጡ ቢሆንም ኮቪድ 19ኝን የመከላከል አቅማቸው ከ1 ዓመት በኋላ እንደሚዳከም ተመራማሪዎች አስታውቀዋል። ይህም ክትባቱን በአግባቡ በመላው ዓለም የማሰራጨቱን ስራ የሚያወሳስበው ሲሆን ምናልባት ቋሚ የሆነ ክትባት ለወደፊት እስካልተገኘ ድረስ የኮቪድ 19 ቫይረስ በእለታዊ የማሕበረሰብ እንቅስቃሴዎች ላይ የፈጠረው ተፅዕኖ ለዓመታት እንደሚቀጥል ያመላክታል።

በተለይም ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ክትባቱን ለማግኘት እየተሄደበት ያለው እጅጉን የተጣደፈ አሰራር ጥቂት በማይባሉ ሰዎች ላይ ስጋትና ጥርጣሬን እየፈጠረ ይገኛል። ሲ ኤን ኤን የተባለው የአሜሪካው የሚድያ አውታር ሰሞኑን በድህረ ገፁ ላይ በሰበሰበው ድምፅ በግምት እስከ 40 ፐርሰንት የሚሆኑት አሜሪካውያን በቅርቡ ለአቅርቦት ይውላሉ የተባሉትን ማንኛቸውንም ክትባቶች የመውሰድ ፍላጎት እንደሌላቸው ለመረዳት ተችሏል። እነዚህ በጥድፍያ የቀረቡ ክትባቶች በጤና ላይ የሚያመጡት ተጓዳኝ ችግር በአግባቡ አይታወቅም የሚል አመለካከት ባለበት ወቅት ሕብረተሰቡን በየዓመቱ እንዲከተብ ማሳመን እራሱን የቻለ ፈተና እንደሚሆንም ይጠበቃል።

ክትባቱ ለመቼ ይደርሳል? እንደ ተመራማሪዎች ግምት በሚቀጥሉት 10 ወራት ውስጥ የመጨረሻውን የሶስተኛ ዙር ሙከራ አልፎ ቢያንስ አንድ ክትባት ለሕዝብ ይቀርባል። መቀመጫነቱን በኒውዮርክ ከተማ ያደረገው ፋይዘር የተባለ የመድሃኒት አምራች በሚቀጥሉት 15 ቀናት ውስጥ በሶስተኛ ዙር ሙከራ ላይ ያለውን ክትባቱን ለመገምገም የሚያስችል በቂ አሃዝ እንደሚኖረው አስታውቋል። ከ25ሺ በላይ በሚሆኑ ተሳታፊዎች ላይ ግኝቱን እየሞከረ ያለው ሌላኛው የአሜሪካ ኩባንያ ሞደርና በበኩሉ በመጪዎቹ ከ30 እስከ 60 ቀናት ውስጥ የመጨረሻ ዙር ሙከራ ውጤቱን መገምገም እንደሚጀምር ይፋ አድርጓል።

እንዲሁም በእንግሊዝ አገር አስትራዜነካ የተባለው መድሃኒት አምራች ያለንበት የፈረንጆች ዓመት ከመገባደዱ በፊት ኦክስፎርድ የሚል ስያሜ ለተሰጠው ክትባቱ የጥራት ማረጋገጫ ለማግኘት ለአገሪቱ ባለስልጣን አመለክታለው የሚል መግለጫ የዛሬ ወር ሰጥቶ ነበር። ኦክስፎርድ ከእንግሊዝም አልፎ በአሜሪካ፣ ደቡብ አፍሪካና እንግሊዝ ወደ 18ሺ በሚጠጉ ሰዎች ላይ ሲሞከር የቆየ ክትባት ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኮቪድ 19 ክትባት ገና ካሁኑ ዓለማችን ያለችበት መልክዐ ምድራዊ የፖለቲካ ፉክክር ሰለባ እየሆነ መጥቷል። ከ20 ቀናት በኋላ አገራዊ ምርጫ በምታካሂደው አሜሪካ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ክትባቱ ምርጫው ከመካሄዱ በፊት እንደምንም ለህዝብ መቅረብ አለበት በሚለው አወዛጋቢ አቋማቸው ምክንያት ከጤና ባለሙያዎችና ተመራማሪዎች ጋር አተካራ ውስጥ ገብተዋል ። በኮቪድ 19 ምክንያት በትንሹ 216 ሺ ሰዎችን ባጣችው አሜሪካ የፕሬዝዳንቱ ቸልተኝነትን እንደ አንድ ምክንያት የማየቱ ሁኔታ እየተስፋፋ በመምጣቱ የፕሬዝዳንት ትራምፕን ምርጫ የማሻነፍ እድል አጣብቂኝ ውስጥ ከቶታል።

በሌላ በኩል ክትባቱን ለማግኘት ተቃርበናል በሚሉ የአውሮፓና የአሜሪካ ኩባንያዎች ላይ ከወራት በፊት የተቃጣው የሳይበር ጥቃት ጣቶች ወደ ሩስያና ቻይና እንዲቀሰሩ አድርጓል። በሐምሌ ወር የአሜሪካ መንግስት በቻይና በሚደገፉ አካላት መረጃን ለመስረቅ በተመራማሪዎች ኮምፒተርና በዩንቨርስቲዎች ላይ የሳይበር ጥቃት እንደተደረገ ደርሼበታለው ሲል አስታውቋል። የሩስያ ሰላዮች በበኩላቸው በአሜሪካ፣ ካናዳና እንግሊዝ እየተደረጉ ካሉ ምርምሮች ጋር የተያያዙ ሰነዶችን ለመስረቅ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ እንደነበር የእንግሊዙ ፀረ ስለላ ተቋም ውቅያኖስ ስር ከተቀበሩ የኢንተርኔት ኬብሎች ያገኛቸው መረጃዎች ያመለክታሉ።

- Advertisement -

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisement -

Latest News

ሰበር ዜና – ዛሬ ረፋድ ላይ አዲግራት ከተማ በትግራይ ሰራዊት እጅ ወድቃለች

ባለፉት አራት ቀናት ዘመቻ አሉላ አባነጋ በሚል ፀረ ማጥቃት የጀመረው በህወሃት የሚመራው የትግራይ ሰራዊት በርካታ ከተሞችን መቆጣጠሩን ከስፍራው የደረሰን...

“የትግራይን ሕዝብ እናጠፋዋለን ሲሉ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ቃል በቃል ነግረውኛል” የአውሮፓ ሕብረት ልዩ መልዕክተኛ

ባለፉት 6 ወራት ውስጥ ሁለት ጊዜ ወደ አዲስ አበባ ተጉዘው የነበሩት የፊንላንዱ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ፔካ ሃቪስቶ በትላንትናው እለት አስደንጋጭ የሆነ ንግግር በአውሮፓ ሕብረት...

የኢትዮጵያ መንግስት ሃሰተኛ መረጃ ሲያሰራጭባቸው የነበሩ ከመቶ በላይ ገፆችን ዘግቻለው ሲል ፌስቡክ አስታወቀ

የማህበራዊ ድህረገፁ ፌስቡክ በትላንትናው እለት ባወጣው ዝርዝር ሪፖርት ከመቶ በላይ የሆኑ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ንክኪ ያላቸው ገፆችን እንደዘጋ አስታወቀ። ፌስቡክ ባደረገው ውስጣዊ ምርመራ እነዚህ...

“ዳቦ ከጠፋ ለምን ኬክ አይበሉም?” አዲስ አበቤነትና የኢትዮጵያውያን ሰቆቃ

እንደ ኢትዮጵያውያን አቆጣጠር በ1965 ዓ.ም በወሎ ስለተከሰተው አስከፊ ረሃብ መረጃ የደረሰው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምናልባት አዲስ አበባ ላይ በቂ ግንዛቤ ላይኖር ይችላል በሚል ከኒውዮርክ...

ቢሮ እንኳን ሳይኖረው የ3.6 ቢልዮን ዶላር ፕሮጀክት የወሰደው የአሜሪካ ኩባንያና የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ትብብር

ባሳለፍነው ታህሳስ ተቀማጭነቱን በኒውዮርክ ከተማ ባደረገ አንድ ክዋርትዝ የተሰኘ የኢንተርኔት ጋዜጣ ላይ የታተመው ፅሁፍ የኢትዮጵያን መንግስት አንገት ያስደፋና በአንዳንድ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ቁጣን ያጫረ ነበር።...
- Advertisement -

More Articles Like This

- Advertisement -