Monday, April 12, 2021

ከፕሬዚደንት ኢሳያስ በኋላ በኤርትራ ሊፈጠር የሚችለው የስልጣን ሽኩቻና በአካባቢው ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ

Must Read

በአክሱም ከተማ ስለተፈፀመው ጭፍጨፋ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ሙሉ ሪፖርቱን ይፋ አደረገ

  ተቀማጭነቱን በለንደን ከተማ ያደረገውና በሰብአዊ መብት ጉዳዮች ላይ በመላው አለም ክትትል የሚያደርገው አምነስቲ ኢንተርናሽናል ከሰአታት በፊት ባወጣው ባለ 25...

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከፊል ድርሻ ለቱርክ መንግስት ሊሸጥ ነው

ዛሬ ከዋሽንግተን ዲሲ አካባቢ የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው በጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የሚመራው የኢትዮጵያ መንግስት የኢትዮጵያ አየር መንገድን እስከ...

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ የሸጠችው ቦንድ ዋጋው እያሽቆለቆለ ነው

ከውጭ ባለሃብቶች 1 ቢልዮን ዶላር ለመበደር በ2007 እ.ኢ.አ ኢትዮጵያ የሸጠችው ቦንድ በአየርላንድ የቦንድ ገበያ ላይ ባለሃብቶቹ እርስ በርስ የሚገበያዩበት...

የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ በአገራቸው ዘመናዊ ታሪክ የመጀመርያውና እስከ ዛሬ ብቸኛው መሪ ሆነው መቆየታቸው እሳቸውን ከኤርትራ ወይም ኤርትራን ከአቶ ኢሳያስ ለይቶ ማየት እስከማይቻል ድረስ የቀይ ባህሯ ሃገር ዋና ገፅታ ሆነው ኖረዋል፡፡ የደርግ ጦር ሙሉ በሙሉ ከኤርትራ ተሸንፎ ካፈገፈገበት ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ ኤርትራን በቁጥጥራቸው ስር አድርገው ለ29 ዓመታት የገዙት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ዕድሜያቸው በ70ዎቹ መጨረሻ ላይ እንደሆነ ይገመታል፡፡ ታድያ የሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ዕጣ ፈንታ አይቀሬ ነውና ዕድሜያቸው በገፋ ቁጥር ድንገተኛ ሞት ወይም ከፍተኛ ህመም ቢያጋጥማቸው የኤርትራ ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል የሚል ጥያቄ መነሳት ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡

ኤርትራ እስከ 6 ሚልየን የሚጠጋ ህዝብ ያላት ሲሆን ከነዚህ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የእስልምና ተከታይ ናቸው፡፡ ከዚህ የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ ሕብረተሰብ ደግሞ አብዛኛው የሚገኘው በሰሜን ኤርትራ ወይም ቆላማው የአገሪቱ ክፍል ሲሆን የተወሰኑት የአረብኛ ቋንቋ ተናጋሪ ናቸው፡፡ ሆኖም ይህ የኤርትራን ህዝብ አብዛኛ ቁጥር የያዘው የሙስሊሙ ሕብረተሰብ የትግርኛ ቋንቋ ተናሪ በሆኑት ክርስትያን ደገኞች ወይም የደቡባዊ ኤርትራ ነዋሪዎች ተፅዕኖ ስር ለረዥም ዓመታት በመቆየቱ በስልጣንም ሆነ በሌሎች ቁልፍ የሃገሪቷ ጉዳዮች ውስጥ የሚገባውን ድርሻ ሳያገኝ ቆይቷል፡፡ በእርግጥ ኤርትራውያን የነፃነት ትግልን ሀ ብለው ሲጀምሩ በቀዳሚነት ተደራጅተው የትግሉን እንቅስቃሴ የጀመሩት እንደ ጀብሀ ያሉ በእስልምና ተከታዮች የተመሰረቱ የአማፅያን ቡድኖች ቢሆኑም ቀስ በቀስ ግን በደገኞቹ የትግርኛ ተናጋሪ ኤርትራውያን እየተዋጡና ተፅዕኖ የመፍጠር አቅማቸው እየተመናመነ ሊሄድ ችሎ ነበር፡፡

https://upload.wikimedia.org/wikipedia/commons/c/cc/Rashaida_family.png
የራሼይዳ ብሔረሰብ አባላት በኤርትራ


የአቶ ኢሳያስ አፈወርቂን ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎ ኤርትራን አንድ ወጥ የሆነ ብሔራዊ ማንነት የመስጠት ዓላማ በደንብ የተሰራበት ቢሆንም የተለያዩ የኤርትራ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የመብት ጥያቄ ለጊዜው ይዳፈን እንጂ ለወደፊት ማንሰራራቱ አይቀርም፡፡
በተለይም በምስራቃዊ የኤርትራ ክፍል በደቡባዊ ቀይ ባህር ዳርቻ የሚገኘው የአፋር ሕዝብ በፕሬዝዳንት ኢሳያስ ከሚመራው የአስመራ መንግስት ጋር በተደጋጋሚ እሰጣ ገባ ውስጥ ሊገባና እስከ የትጥቅ ትግል የሚደርስ እንቅስቃሴ ወደ መግባት ሊደርስ ችሏል፡፡ በቀድሞው የህወሃት መራሹ መንግስት ወቅት ከኢትዮጵያ ድጋፍ ይደረግላቸው የነበሩ የተለያዩ ታጣቂ አማፅያን ቡድኖች ዛሬም ድረስ የኤርትራ መንግስት በስጋት እየተመለከታቸው ይገኛል።

አቶ ኢሳያስ አገራቸው ከኢትዮጵያ ነፃነታቸውን ከተጎናፀፈችበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ዛሬ እንቅልፍ ነስቷቸው የኖረ አንድ ነገር አለ፡፡ ይህም የኤርትራ ዘላቂ ሉአላዊነት ነው፡፡ በእርግጥ ኤርትራ ከ28 ዓመታት በፊት ሁሉንም የአለም አቀፍ መስፈርቶች አሟልታ ሉአላዊነቷን አስከብራለች፡፡ ይባስ ብሎም በ1985 ዓ.ም የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ በአስመራ ከተማ ለተሰበሰበው ሕዝብ ኢትዮጵያ የአዲሷ ጎረቤቷን ነፃነት ሙሉ በሙሉ እንደምትቀበል አውጀው የእንኳን ደስ አላቹ መልዕክት ለኤርትራውያን አስተላልፈው ነበር፡፡ ነገር ግን አገራዊ የዓመት ገቢዋ (ጂዲፒ) 7 ቢልዮን ዶላር የማይበልጠው ኤርትራ ኢኮኖሚዋ የኢትዮጵያን አንድ አስረኛ እንኳን አይሞላም፡፡

በተለይም ከቀይ ባሕር የሚያገናኛትን በር ያጣችው ኢትዮጵያ አንድ ቀን በእጅ አዙር የኤርትራ ፖለቲካ ላይ ጣልቃ መግባት መጀመሯ አይቀርም ብለው የሚሰጉት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ሁለቱን ሕዝቦች የሚያስተሳስሩና በኤርትራ ሕዝብ ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድሩ ይችሏሉ የሚሏቸውን እንደ ቋንቋ ባህልና ሃይማኖት የመሳሰሉትን በኤርትራ ለማዳከም ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡

ለምሳሌ የኤርትራ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ላለፉት 5 ዓመታት ያለ ሊቀ ጳጳስ ሲመራ የቆየ ሲሆን በርካታ የሃይማኖት አባቶችና ተከታዮች በእስር ቤት ይገኛሉ፡፡ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ጋር ከፍተኛ ትስስር ከነበረው ይኤርትራ ካቶሊክ ቤተክርስትያን ጋር የአስመራው መንግስት በአይነ ቁራኛ ሲተያይ ቆይቶ በቅርቡ በካቶሊክ ቤተክርስትያኗ ስር ይተዳደሩ የነበሩ የህክምና ማዕከላትን ወርሶ ብዙ አባላትንም አስሯል፡፡ ከዚህም አልፎ ከሁለት ወራት በፊት የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስትያን ጳጳሳት ከኤርትራውያን አቻዎቻቸው ጋር ለመገናኘት በኢትዮጵያ አየር መንገድ ተሳፍረው አስመራ ቢደርሱም የኤርትራ የደህንነት አባላት ኢትዮጵያውያን ጳጳሳቱን ከአስመራ ኤርፖርት መመለሳቸው የሚታወስ ነው፡፡

ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በሃይማኖት ብቻ አላበቁም፡፡ ኤርትራን ከኢትዮጵያ ጋር ከሚያቆቅራኟት ነገሮች አንዱ የትግርኛ ቋንቋ ቢሆንም ግማሽ የሚሆነው የኤርትራ ሕዝብ ሌሎች የብሔር ብሔረሰቦች ቋንቋዎችን የሚናገር በመሆኑ ለወደፊት በኤርትራ ሊፈጠር በሚችል የፖለቲካ ክፍፍል ወቅት ኢትዮጵያ ከትግርኛ ተናጋሪው ሕብረተሰብ ጎን በመቆም ጣልቃ መግብያ በር ታገኛለች በሚል ፍርሃት አገራቸው ኤርትራ አንድ ወጥ የሆነ ብሔራዊ ቋንቋ እንዲኖራት ሌት ከቀን ሲተጉ ቆይተዋል፡፡ ይህንን አላማቸውን ለማሳካት ሲሉም በኤርትራ እጅግ ጥቂት ተናጋሪ ብቻ ያለውን የአረብኛ ቋንቋ ከትግርኛ እኩል የአገሪቱ ብሔራዊ ቋንቋ ያደረጉት ቀስ በቀስ አረብኛ ትግርኛን እየዋጠና በሕዝቡ ዘንድ እንዲስፋፋ ለማድረግ በሚል እቅድ እንደሆነ አንዳንዶች ይገምታሉ፡፡

እጃቸው ረዥም እንደሆነ በተደጋጋሚ በመግለፅ የሚታወቁት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ ስራ ላይ በዋለው ህገመንግስት የተደነገገውን የፌደራል ስርዐት አወቃቀር አምርረው ይጠላሉ፡፡ እንደሳቸው አባባል ከሆነ ፌደራሊዝም ኢትዮጵያን የሚከፋፍልና ዘላቂ ሰላምን የማያመጣ ሲሉ ይወቅሱታል፡፡ ሆኖም የአቶ ኢሳያስን ታሪክና አስተሳሰብ ለሚያውቅ ሰው ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ፌደራሊዝም ላይ ያላቸው ስጋት ከምን የመነጨ መሆኑን ለመረዳት ይችላል፡፡ አሁን በስራ ላይ ያለው የፌደራል ስርዐት 9 ክልሎችን በብሔር ላይ መስርቶ ያካለለ ሲሆን ከነዚህ ክልሎች ውስጥ ሁለቱ ማለትም አፋር ክልልና የትግራይ ክልል ኤርትራን በቀጥታ ያዋስናሉ፡፡

የአፋር ክልል በኢትዮጵያ በኩል ሁለት ሚልየን የሚጠጋ ሕዝብ ያለው ሲሆን በኤርትራ በኩል ካሉት የአፋር ወንድሞቹ ጋርም በድንበር ይዋሰናል፡፡ ታድያ በጎረቤት ሃገር የራሳቸው ክልል ተሰጥቷቸው እራሳቸውን በራሳቸው ሲያስተዳድሩ የሚያዩ የኤርትራ አፋሮች እነሱም ተመሳሳይ የሆነ መብት እንዲሰጣቸው በተደጋጋሚ ሲጠይቁ ኖረዋል፡፡ የፕሬዝዳንት ኢሳያስ ፍራቻ በኢትዮጵያ ያሉ ክልሎች ከተጠናከሩ በኤርትራውያን ዘንድ ሊያመጣ የሚችለውን የተመሳሳይ መብት ጥያቄ ሲሆን ብሎም እንደ አፋር ያሉ የኤርትራ ብሔር ብሔረሰቦች ከአስመራ ይልቅ በጎረቤት አገር ካለው የአፋር ክልል ጋር የበለጠ ግንኙነት እንዳይፈጥሩ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ከሁለት ዓመታት በፊት የታየውን የመንግስት ለውጥ ተከትሎ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ከአዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ጋር ጠንካራ ወዳጅነትን ፈጥረዋል፡፡ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ በብዙዎች ዘንድ የፌደራል ስርዓቱን ቀስ በቀስ የማጥፋት ዕቅድ አላቸው ተብለው ይታማሉ፡፡ ፕሬዝዳንት ኢሳያስም በተደጋጋሚ ከጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ጎን እንደሚቆሙና ኢትዮጵያ በብሔር ከተከፋፈለ የፌደራል ስርዐት ወጥታ ወደ አንድ ማዕከላዊ እዝ መግባት እንዳለባት ሲያሳስቡ ታይተዋል፡፡
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ እቅዳቸው እስከምን ድረስ ተሳክቶላቸዋል? ከሳቸው በሁዋላስ የኤርትራ እጣ ፋንታና የሀያላን ሃገራት ሚና እንዲሁም በኢትዮጵያና በአካባቢው የፖለቲካ አሰላለፍ የሚያመጣው ለውጥ ምን ይሆናል የሚለውን ኢትዮኖሚክስ በዚህ ትንታኔ ያብራራል
ክፍል ሁለት ይቀጥላል

- Advertisement -

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisement -

Latest News

በአክሱም ከተማ ስለተፈፀመው ጭፍጨፋ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ሙሉ ሪፖርቱን ይፋ አደረገ

  ተቀማጭነቱን በለንደን ከተማ ያደረገውና በሰብአዊ መብት ጉዳዮች ላይ በመላው አለም ክትትል የሚያደርገው አምነስቲ ኢንተርናሽናል ከሰአታት በፊት ባወጣው ባለ 25...

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከፊል ድርሻ ለቱርክ መንግስት ሊሸጥ ነው

ዛሬ ከዋሽንግተን ዲሲ አካባቢ የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው በጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የሚመራው የኢትዮጵያ መንግስት የኢትዮጵያ አየር መንገድን እስከ ግማሽ የሚጠጋ የባለቤትነት ድርሻ ለቱርክ...

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ የሸጠችው ቦንድ ዋጋው እያሽቆለቆለ ነው

ከውጭ ባለሃብቶች 1 ቢልዮን ዶላር ለመበደር በ2007 እ.ኢ.አ ኢትዮጵያ የሸጠችው ቦንድ በአየርላንድ የቦንድ ገበያ ላይ ባለሃብቶቹ እርስ በርስ የሚገበያዩበት ዋጋ ማሽቆልቆሉን ቀጥሏል። ከሶስት ሳምንታት...

ኤርትራ፤ ከተራራው ጀርባ ጠልቃ የቀረችው ሰሜናዊት ኮኮብ

  ኤርትራ ከባህር በሯ በዘለለ፤ ምድሯ ጥቅም የለውም የሚለው አስተሳሰብ ከኢትዮጲያ ጋር ፍቺ ሳትፈጽም በፊት ገዢ ሃሳብ ሆኖ ነው የኖረው፡፡ በደርግ ጊዜ የኢትዮጲያ ፕሬዝዳንት የነበሩት...

ኢኮኖሚያዊ ህልሙ በፖለቲካ ይጨናገፍ ይሆን?

  በ2013 እ.ኤ.አ. የአዲስ አበባ መስፋፋት የኦሮሚያ ገበሪዎችን አፈናቅሏል በሚል የተጀመረው የጸጥታ አለመረጋጋት ሰባት አመታትን አስቆጥሯል፡፡ ይህ አመጽ አሁን ያሉትን ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ ስልጣን አምጥቶ...
- Advertisement -

More Articles Like This

- Advertisement -