ያልተመረጠ መንግስት ገደብ የሌለው ስልጣንና ለትውልድ የሚተርፍ መዘዝ

0

ትላንት በውድቅት ለሊት አብዛኛው የኢትዮጵያ ነዋሪ እንቅልፍ ላይ ባለበትና አገሪቷ ከጫፍ እስከ ጫፍ በጨለማ በተዋጠችበት ሰዓት ከወደ ግብፅ እየተደለቀ ያለው የደስታ ከበሮና እልልታ መገናኛ ብዙሃንን አጨናንቋቸው ይገኛል፡፡ ምን ተገኝቶ ነው ሲባል ደግሞ ኢትዮጵያ ላለፉት 9 ዓመታት በአባይ ወንዝ ላይ ስትገነባ ቆይታ እያገባደደችው ባለው የህዳሴ ግድብ ላይ ሊደረግ የታቀደውን የውሃ ሙሌት “ከሱዳንና ግብፅ ጋር ስምምነት ላይ እስኪደረስ ላትሞላ ተስማምታለች” የሚል ዜና በካይሮና ካርቱም ካሉ ባለስልጣናት የምስራች ስለተበሰረ ነው፡፡ በዚህ ግራ የተጋቡት በርካታ የኢትዮጵያ የመብት ተሟጋቾች፣ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ገና ወደ መኝታ ያላመሩ የአገር ውስጥ ዜጎች በግብፅ መገናኛ ብዙሃን እየተራገበ ያለውን ዜና እውነተኛነት ለማረጋገጥ ቢሯሯጡም ከኢትዮጵያ መንግስት በኩል የተገኘው ብቸኛ መግለጫ ስለ ስብሰባው መካሄድ ብቻ ነው፡፡ በስብሰባው ላይ ምን እንደተወሰነ፣ ማን ምን እንዳለና በዘመናችን ትልቁ የሚባለው ኢትዮጵያዊ ፕሮጀክት እጣ ፈንታ ምን ላይ እንደደረሰ ለአገሪቷ ህዝብ የተገለፀ ነገር የለም፡፡ በዛሬው እለትም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ስለ ድርድሩ ሊሰጥ የነበረውን መግለጫ እንደሰረዘ አስታውቋል፡፡

በእርግጥ የግብፅ መገናኛ ብዙሃን በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ከስብሰባ በሁዋላ ያልተደረጉ ስምምነቶችን እንደተደረጉ አድርገው ለአገራቸው ሕዝብ ቢያበስሩ ይሄ የመጀመርያቸው አይሆንም፡፡ ከጥቂት አመታት በፊት ኢትዮጵያ ግድቡን ከግብፅ ጋር በጋራ ለማስተዳደር ተስማምታለች በሚል የተሳሳተ ዜና ግብፃውያን ከካይሮ እስከ ፓሪስ እንዲሁም እስከ ኒውዮርክ ጮቤ የረገጡበት ጊዜ ነበር፡፡ ስለዚህም የኢትዮጵያ መንግስት በትላንትናው እለት በትክክል ምን አይነት ስምምነት እንደፈፀመ በዝርዝር እስኪያስረዳ ድረስ ጣት መቀሰር ሚዛናዊነት የሚጎድለው የችኮላ ተግባር በመሆኑ ኢትዮኖሚክስ በዚህ ጉዳይ ላይ ወደ ዝርዝር ከመግባት ተቆጥቧል፡፡ ነገር ግን የዛሬው የኢትዮጵያ አመራር ውስብስብ በሆኑ የአገር ጉዳዮች ላይ ማለትም በኢኮኖሚው፣ በሕዳሴ ግድብና ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚገናኙ ጉዳዮች ላይ ከተቋማት እውቅና ውጪ እንዲሁም ለሕዝብ ግልፅ ባልሆነ መልኩ ስምምነቶችን መፈፀም ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ ለአብነት ያክል የኢትዮጵያ ሕዝብም ሆነ ተቋማት በውል የማያውቁት ከኤርትራ ጋር ያለው ድንበርን ማስከፈት እንኳን ያልቻለ ግንኙነት፣ ሕዝብንም ሆነ ሌሎች ባለ ድርሻ አካላትን ባላሳተፈ መልኩ የኢትዮጵያ ሃብት የሆኑ እንደ ቴሌ ያሉ ኩባንያዎችን ለውጭ አገራት ለመሸጥ መቻኮልም ሆነ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የመወሰን መብትን ለአሜሪካውያን አሳልፎ መስጠት፣ ብሎም በአዲስ አበባና በመሳሰሉት ከተሞች ላይ ሕዝብን ሳያማክሩ የከተሞችን ማንነት እስከ ወድያኛው ሊቀይሩ የሚችሉ ፕሮጀክቶችን በጥቂት ሰዎች ውሳኔ ብቻ እንዲተገበር ማድረግ ይገኙበታል፡፡ ከዚህም አልፎ ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ለመሆን በድርድር ላይ መሆኗ የጉዳዩን ክብደትና ውስብስብነት ለሚረዳው ምን ያህል አደገኛ ውሳኔዎች በችኮላ እየተደረጉ እንደሆነ ያሳያል፡፡

እነዚህን እንቅስቃሴዎች ታድያ እጅግ አንገብጋቢ የሚያደርጋቸው ለዘመናት የሚመጣን ትውልድ በቀጥታ የሚመለከቱና ዘላቂ ተፅዕኖ በነገዋ ኢትዮጵያ ላይ የሚያሳድሩ ናቸው፡፡ ይባስ ብሎም ሕዝብን እንዲወክል በአግባቡ እውቅና ያልተሰጠው የሽግግር መንግስት እንደዚህ አይነት ውሳኔዎች በድብቅ ሲያደርግ በርካታ ኢትዮጵያውያን ተስፋ የጣሉበት ለውጥ መክሸፉንና አገሪቷን በአደራ ያስረከቡት አካል አቅጣጫ መሳቱን ያሳያል፡፡ ይህንንም ተከትሎ በአገሪቱ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እንዲሁም ምሁራን በአንድ ድምፅ የመንግስትን አካሄድ መቃወም ጀምረዋል፡፡ በተለይም እንደ ኢዜማ ያሉ ከዚህ በፊት የብልፅና ተለጣፊ ፓርቲ በሚል እስከ መወንጀል የደረሱ ልዝብ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ድምፃቸውን ማሰማት መጀመራቸው መንግስት ቀስ በቀስ ጠላቱን እያበዛ መምጣቱን ያሳያል፡፡ ኢዜማ ትላንት ባወጣው መግለጫ መንግስት በድብቅና የተቻኮለ አካሄድ ቴሌን በከፊል ለውጭ ባለሃብቶች ለመሸጥ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ በአስቸኳይ እንዲቆም አሳስቧል፡፡ ከወደ ሰሜን በኩልም ከዓለም ባንክና የዓለም የገንዘብ ድርጅት ጋር በመሟገት ከፍተኛ ልምድ ያላቸው የህወሃት አባላት በዶ/ር አብይ የሚመራው መንግስት ለዓለም ባንክና የዓለም የገንዘብ ተቋም በሩን በርግዶ መክፈቱ የአገሪቷን ሉአላዊነት እንደሚሸረሽረውና በቀላሉ ልትላቀቀው ወደማትችለው የምዕራብያን ተፅዕኖ ውስጥ እንደሚያስገባት በተደጋጋሚ እያስጠነቀቁ ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪም በኦፌኮ አመራር ውስጥ ያሉት አቶ ጃዋር መሃመድ በበኩላቸችው ዶ/ር አብይ ወዳጅ ጎረቤት አገራትንም ሆነ የአገር ውስጥ ባለ ድርሻ አካላትን ሳያማክሩ ወደ ዋሽንግተን ዲሲ ሄደው ከግብፅ ጋር ለመደራደር መስማማታቸው ትልቅ ጥፋት እንደሆነና አሁንም ቢሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሕዝብ እውቅና ውጪ ወደ ምንም አይነት ስምምነት እንዳይገቡ በመገናኛ ብዙሃን እሮሮውን ሲያቀርቡ ተሰምተዋል፡፡

በወቅቱ እጅግ አንገብጋቢ የሆኑት ጉዳዮች እነዚህ ይሁኑ እንጂ የሕዝብ ውክልናም ሆነ እውቅና ሳይሰጠው፣ ስልጣኑም ሳይገደብ አራት ኪሎን ተቆጣጥሮ የሚቆይ ሃይል ለወደፊት ኢትዮጵያን ሊከትበት የሚችለው አደጋ እጅጉን የከፋ ሊሆን ይችላል፡፡ በተለይም ዶ/ር አብይ የኮሮና ወረርሽኝ ኖረም አልኖረ ምርጫን የማካሄድ ምንም አይነት ፍላጎት እያሳዩ ባልሆነበት ሁኔታ ስልጣናቸውን ከመገደብ ይልቅ ተቋማትን እያፈራረሱ፣ የስልጣን ተቀናቃኞችን እያራቁ የሚሄዱበት አካሄድ ከብሔር ብሔረሰቦች እያየለ የመጣ ንቃትና የመብት ጥያቄ፣ እንዲሁም የስራ አጥነት በአገሪቱ መስፋፋት ጋር ሲጋጭ ኢትዮጵያን ወዳልታሰበና ድንገተኛ ነገር ግን በፍጥነት ሊቀጣጠል ወደምሚችል ትርምስ ውስጥ ያስገባታል የሚል ስጋት እያየለ መጥቷል፡፡

ወደ ስልጣን ከመጡ ሁለት ዓመታትን ያሳለፉት ዶ/ር አብይ ቀድሞ ከነበረው መንግስት በጣም የተሻለ አንፃራዊ ድጋፍን ከሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች አግኝተው የነበረ ቢሆንም ብዙም ሳይቆዩ መጀመርያ ከትግራይ ክልል፣ ቀጥሎም በአማራ በኦሮምያና ሱማሌ ክልል ነዋሪዎች ዘንድ ቁጣን አስነስተዋል፡፡ ይህ ሊሆን የቻለበት በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም ዋነኛውና አሳሳቢው ግን አገሪቱን ሲያስተዳድሩ የሚያደርጉት ሚስጥራዊ እንቅስቃሴ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚንስትሩ ስልጣን ከያዙ ጀምሮ ከአንድም የአገር ውስጥ የግል ጋዜጣም ሆነ ቴሌቪዥን ጋር ቃለ ምልልስ ያላደረጉ ሲሆን ይባስ ብለውም የኖቤል ሽልማታቸውን ለመቀበል ወደ ኖርዌይ ባቀኑበት ወቅት ከውጭ ጋዜጠኞች ምንም አይነት ጥያቄ መቀበልም ሆነ ቃለ ምልልስ በሚደረግበት ቦታ ላይ መገኘት አልፈልግም የሚል በኖቤል ተሸላሚዎች ዘንድ ያልተለመደ ድርጊት በመፈፀማቸው በወቅቱ በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ላይ ውዝግብን አስነስተው ነበር፡፡

በመጪው ነሓሴ ይደረጋል ተብሎ የነበረው ምርጫን ላልተሰወነ ጊዜ መራዘም ተከትሎ ከህወሃት እስከ ኦፌኮና ኢዜማ እየቀረበ ያለው ጥያቄ የኮሮና ወረርሽኝ ተወግዶ በአግባቡ ምርጫ እስኪካሄድና ሕዝብ መርጦ እውቅና የሚሰጠው መንግስት እስኪቋቋም ድረስ ቢቻል ጠቅላይ ሚንስትሩ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በማሳተፍ በጋራ ስምምነቶች ላይ ተመስርተው አገሪቱን እንዲያስተዳሩ ይህ የማይሆን ከሆነ ደግሞ በኢትዮጵያ ላይ ለዘመናትና ለትውልድ የሚተርፉ እንዲሁም ጫና የሚፈጥሩ ውሳኔዎችንና ማንኛውንም አይነት ከውጭ አካላት ጋር በግል የሚደረጉ ስምምነቶችን ከማድረግ እንዲቆጠቡ የሚል ነው፡፡ የዓለም ባንክና የዓለም የገንዘብ ድርጅት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ አድራጊ ፈጣሪ ሆነው እንደፈለጉ እንዲንቀሳቀሱ መፍቀድ፣ ከሱዳንና ከኤርትራ ድንበር የሚያያዙ ብሎም ንግድን የሚመለከቱ የሁለትዮሽ ስምምነቶችን ማድረግ፣ እንደ የህዳሴ ግድብ ባሉ ጉዳዮች ላይ ለሕዝብ ግልፅ ባልሆነ መልኩ መደራደርና ህገመንግስቱን የሚመለከቱ ማንኛቸውንም አይነት ለውጦች ማድረግ ይችሉ ዘንድ ሕዝብ ላልመረጣቸው ጠቅላይ ሚንስትር መፍቀድ ኢትዮጵያን ወደ ዘላቂ ኪሳራ የሚያስገባ ይሆናል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here