ግብፅ ወደ ጎረቤት አገር ሊብያ “ጦር እልካለው” ስትል አስጠነቀቀች

0

የግብፁ ፕሬዝዳንት ባሳለፍነው ቅዳሜ በምዕራባዊ ግብፅ በሊብያ ድንበር አቅራብያ የሚገኘውን የአየር ሃይል ካምፕ በጎበኙበት ሰዓት የጦር መኮንኖቻቸውን በተጠንቀቅ እንዲቆሙ ያዘዙ ሲሆን ጦሩ በአገር ውስጥም ሆነ ድንበርን ተሻግሮ ለሚፈፀም ግዳጅ እንዲዘጋጅ ትእዛዝ አስተላልፈዋል፡፡ በተባበሩት መንግስታት እውቅና ያለውን የሊብያ መንግስት በኃይል ለመጣል ከ1 ዓመት በፊት ጦርነት የከፈተው የአማፂ ቡድን ከግብፅ፣ አረብ ኤመሬትና ሩስያ ከፍተኛ ድጋፍን በማግኘት በርካታ ግዛቶችን መቆጣጠር ጀምሮ የነበረ ቢሆንም መቀመጫነቱን በምዕራብዋ ከተማ ትሪፖሊ ያደረገው ማዕከላዊ መንግስት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከቱርክ እያገኘ ባለው ጠንካራ የአየር ኃይልና ወታደራዊ ድጋፍ ከበውት የነበሩትን አማፅያን ወደኋላ እንዲያፈገፍጉ አስገድዷቸዋል፡፡ የግብፅ ወዳጅ የሆኑት አማፅያን ከዚህ በፊት አብዛኛውን የምስራቃዊ ሊብያ ክፍል የተቆጣጠሩ ቢሆንም የመንግስት ጦር ጥቃቱን በመጨመሩ የወደቧን ሲርት ከተማ ለመቆጣጠር አፋፍ ላይ ደርሷል፡፡ የሊብያ ትላልቅ የሚባሉ የነዳጅ ጉድጓዶች የሚገኙት በዚሁ ምስራቃዊ የአገሪቱ ክፍል ሲሆን በሲርት ከተማ ያለው ወደብም ወደ ውጭ የሚላክ ነዳጅን የማስተናገድ አቅም ያለው ከመሆኑ አኳያ እነዚህን ቦታዎች መቆጣጠር ለሊብያ መንግስት ትልቅ የኢኮኖሚ አቅምን ሲጨምር በተቃራኒው ደሞ አማፅያኑን ሊያዳክም ይችላል፡፡

ይህ ያሳሰባቸው የግብፁ አል ሲሲም የሊብያ መንግስት ወደ ሲርት ከተማ ከገባ ለሳቸው ቀይ መስመርን እንደመጣስ ነው በማለት የግብፅ ጦር ድንበር ተሻግሮ እርምጃ ይወስዳል ሲሉ አስጠንቅቀዋል፡፡ ይህንን ተከትሎ የሊብያን መንግስት በቁሳቁስና በወታደር በምትረዳው ቱርክና የአማፅያኑ ወዳጅ በሆነችው ግብፅ መካከል ግጭት እንዳይፈጠር በአካባቢው ስጋትን ፈጥሯል፡፡ የቱርክና የግብፅ ግንኙነት የሻከረው ከ7 አመታት በፊት አልሲሲ የቀድሞውን የግብፅ ፕሬዝደንት መሃመድ ሙርሲ በመፈንቅለ መንግስት ገልብጠው ስልጣን ከያዙ ጊዜ ጀምሮ ሲሆን ቱርክ የቀድሞው ፕሬዝዳንት መሃመድ ሙርሲ የነበሩበትን የእስልምና ወንድማማቾች ፓርቲ ትደግፋለች፡፡ ይህ ወቅታዊውን የግብፅ መንግስት እጅጉን ከማበሳጨቱም አልፎ የቱርክ ተፅዕኖ ፈጣሪነት በጎረቤት ሊብያ በጨመረ ቁጥር ከመፈንቅለ መንግስቱ በፊት በምርጫ አሸንፎ ካይሮ ላይ ስልጣን ይዞ ለነበረው ተቃዋሚው የእስልምና ወንድማማቾች ፓርቲ ዋና መጠለያ እንዳይፈጠር ፕሬዝዳንቱን አሳስቧቸዋል፡፡ የእስልምና ወንድማማቾች ፓርቲ በተለያዩ የአረብ አገራት ሕዝቦች ተቀባይነት ያለው በሰላማዊ ትግልና በዲሞክራሲ የሚያምን ቢሆንም ከግብፅ በተጨማሪ በሳውዲና በአረብ ኤመሬት የንጉሳውያን ቤተሰቦች ዘንድ በጠላትነት የሚታይ ነው፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here